የአስም በሽታ እንዴት ይከሰታል?

0
349

ኢትዮ ጤና በድረ ገጹ እንዳስነበበው በአሜሪካ ከአጠቃላይ የሀገሪቷ ሕዝብ ውስጥ ሰባት በመቶው በአስም  የተጠቁ ናቸው፡፡

በሀገራችን  ደግሞ መስከረም እና ጥቅምት ወራት የአስም በሽታ ይከሰታል ፡፡ ለዚህ ደግሞ አባባሽ  የሆነው የአበቦች ሽታ  በስፋት መኖሩ ነው፡፡

አስም አየርን ወደ ሳምባ የሚወስድ የአየር ቧምቧን እና በሳምባ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ የአየር ቱቦዎችን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው የእነዚህ የአየር ቧምቧዎች ስፋት (ዲያሜትር) ሲቀንስ እና አየርን በትክክል ማመላለስ ሲያቅታቸው ነው፡፡ የአየር ቧምቧዎች ስፋት የሚቀንሰውም በአለርጂ (allergy) ሲጠቃ እና ጤናማ ሰው ከሚያመነጨው ወፍራም ፈሳሽ (Mucus)በላይ ሲያመነጭ ነው፡፡

የአየር ቧምቧ ሲጠብ እና በወፍራም ፈሳሽ (Mucus) ሲሞላ አየር ወደ ውስጥ መግባት እና መውጣት አይችልም። ከዚህም የተነሳ በዚህ ችግር የተያዙ ሰዎች የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ፡፡

ለአስም በሽታ አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ወላጆቻቸው በበሽታው የተያዙ (እንደ ቆዳ እና የሳይነስ አለርጂዎች) የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስ እና ሲጋራ በሚያጨሱ ሰዎች አጠገብ በመገኘት ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ (Passive Smokers) በሥራ ላይም ሆነ በሌላ ምክንያት ከተለያዩ ፋብሪካዎች ለሚመነጩ ኬሚካሎች መጋለጥ …ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የአየር ቧምቧዎችም ከሰውነታችን አካላት ውስጥ አንዱ በመሆናቸው ወደ ሰውነታችን ባዕድ ነገሮች ሲገቡ የመቆጣት ባህሪ ያሳያሉ፡፡ በተለይም ደግሞ የአስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች ወደ ሰውነታቸው ባዕድ ነገሮች ሲገቡ የአየር ቧምቧቸው ይቆጣል፤ የመተንፈሻ አካል ይጠባል፤ አክታ መሳይ ነገር ይፈጠራል።

የጤናማ ሰዎች የአየር ቧምቧ አለርጂ ቢያጋጥመውም ምንም አይነት የቁጣ ወይም የመለወጥ ሁኔታ አያሳይም፡፡ የአስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች አካል ግን ይቆጣል፤ በበሽተኛው ላይም ህመም ያስከትላል፡፡

ሰውነታችንን ከሚያስቆጡ ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ ቀዝቃዛ እና ደረቃማ የአየር ፀባይ፣ ልዩ ልዩ የአበባ ብናኞች እና በአየር ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ብናኞች፣ ከባድ ሽታ (መጥፎ ጠረን ወይም ጥሩ መዓዛ) ፣ ሲጋራ ማጨስ ወይም ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ፣ አቧራ እንዲሁም እንደ ሳል እና የሳምባ ኢንፌክሽን ያሉ የአየር ቧምቧን የሚያጠቁ በሽታዎች፣ የአእምሮ ጭንቀት (stress)፣ የማገዶ ጭስ፣ የቤት እንስሳት ጠረን፣ ለሌሎች በሽታዎች የሚሰጡ አንዳንድ መድኃኒቶች እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ከዚህ በሽታ ምልክቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ሳል (በተለይ ማታ ማታ እና በብርድ ወይም በቅዝቃዜ ጊዜ)፣ የማንኮራፋት ድምፅ ማሰማት፣ መተንፈስ አለመቻል ወይም የአተነፋፈስ መቆራረጥ / እንደ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት መወጠር/  እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ከባድ የአስም በሽታ ለመንቀሳቀስ እና ለማውራት እስከመቸገር ያደርሳል፡፡ የአስም በሽታ ጥሩ የሚባል ህክምና ቢኖረውም አደገኛና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በሽታ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን በትክክል ህክምናውን በመከታተል ጤናማ ሆኖ መኖር ይቻላል፡፡  በሽታው ከሰው ሰው ይለያያል፤ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ቀላል ሆኖ ትናንሽ ምልክቶችን ብቻ የሚያሳይ ሲሆን በሌሎች ላይ ደግሞ መተንፈስ አቅቷቸው ከመደበኛ ሥራቸው እስከ መቅረትና ሕይወት እስከመቅጠፍ የሚያደርስ ነው። ይህ የአስም በሽታ የሚያሳየው ምልክት ብዙውን ጊዜ ቀጣይነት ያለው ሳይሆን በመሀል ረፍት እየሰጠ ሌላ ጊዜ እየባሰ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ምልክቱ እየቀነሰ የሚታይ ነው፡፡ የአስም በሽታ የተለያዩ ሦስት ገጽታዎች አሉት ፡፡

 

የአየር ቧንቧ መዝጋት

በጤናማ የአተነፋፈስ ስርዓት የአየር ቧንቧዎችን የከበቡት ጡንቻዎች ዘና ይላሉ፤ ይህም የአየር ቧንቧ ያለምንም መጨናነቅ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን የአስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች አለርጂ፣ ጉንፋን እና የአካባቢያቸው ሁኔታ የአየር ቧንቧዎችን የከበቡትን ጡንቻዎች እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም  አየር በትክክል እንዳይተላለፍ ያደርገዋል፡፡ ወደ ውስጥ የሚገባው አየር ሲያንስ ሰውየው የትንፋሽ እጥረት ያጋጥመዋል፣ በጣም በጠበቡት የአየር ቧንቧዎች የሚወጣው አየር ትንፋሹን ድምጽ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡

 

የቧንቧዎች መቆጣት

አስም ያለባቸው ሰዎች የመተንፈሻ ቧንቧዎቻቸው ያብጡና ቀይ ይሆናሉ፡፡ ይህ  የቧንቧዎች መቆጣት ከብዙ ጊዜ ቆይታዎች በኋላ በአስም ምክንያት ለሳንባ መጎዳት ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያደርጋል፡፡ ይህን የቧንቧዎች መቆጣት ማከም የአስም በሽታን ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

 

የአየር ቧንቧዎች ማሳከክ/መቆጣት

በአስም በሽታ የተያዙ ሰዎች የአየር ቧንቧቸው ከመጠን  በላይ  ቁጡና ቶሎ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የአየር ቧንቧዎች በጣም በትንሽ ሽታ ለምሳሌ የአበባ ዱቄት፣ የእንሰሳት ሽታ፣ አቧራ…በቀላሉ እንዲቆጡ እና እንዲጠቡ ያደርጋቸዋል፡፡

በአስም የተያዘ የቤተሰብ አባል ያለው ሰው በበሽታው የመያዝ አጋጣሚው ከፍተኛ ነው፡፡ አለርጂ እና አስም አብረው የመከሰት እድል አላቸው፡፡ አስም ማንኛውንም ሰው በማንኛውም ጊዜ ሊይዝ ይችላል፤ ስለዚህ የአስም ምልክቶች ከታዩ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው። የአስም በሽታ በማንኛውም የእድሜ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል። በተለይ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የተለመደ ነው፡፡

 

አስም በሕፃናት ላይ

አስም በአብዛኛው ሕፃናትን ያጠቃል፡፡ ለአብነት በአሜሪካ ከሚገኙ 10 ሕፃናት አንዱ በአሰም በሽታ ይያዛል፡፡ ምልክቶችም በአንድ ሕፃን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለያይ ይችላል፡፡ መሳል፣ በሚጫወቱበት፣ በሚስቁበት እና ማታ ላይ ማሳል በሕጻናት ላይ በአብዛኛው የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ለአስም በሽታ ሳል ብቸኛ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡

በአስም በሽታ የተያዙ ሕጻናት በጨዋታ ጊዜ የአቅም ማነስ ወይም ትንፋሽ ለመሰብሰብ መቆም፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ የደረት መታፈን፣ አየር ሲያስወጡ እና ሲያስገቡ ለየት ያለ ድምጽ መኖር፣ የትንፋሽ መጨመር እና መቀነስ/የተዘበራረቀ አተነፋፈስ/ የትንፋሽ ማጠር፣ የአንገት፣ ደረት እና ጡንቻዎች መጠንከር፣ የድካም ስሜት ይታይባቸዋል፡፡

የአስም በሽታ መነሻ እና የሚያባብሱት ነገሮች  የአስም በሽታ መከላከሉ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፡፡ ዋነኛው ምክንያት  ደግሞ በ ሽታውን የሚፈውስ ፍቱን  መድኃኒት ባለመገኘቱ ነው፡፡ ነገር ግን በሽታው እንዳይነሳ እና እንዳይጎዳ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሽታው ከመቀስቀሱ በፊት ከሚደረግ ጥንቃቄ ባሻገር ከተነሳም በኋላ ለአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ የአስም ምልክቶችን የሚቆጣጠሩ መድኃኒቶች (controllers) አሉ፡፡

 

የአስም በሽታ መከላከያዎች

ለአስም በሽታ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉትን ኢንፉሌንዛ እና ኒሞኒያ ክትባቶችን በጊዜ በመውሰድ መከላከል ይቻላል፡፡  ከቤት ውስጥ ለአስም በሽታ ሊያጋልጡ ከሚችሉ እንደ አበባ ዱቄት፣ ቀዝቃዛ እና የተበከለ አየር… መራቅ ተገቢ ነው፡፡ ለአስም በሽታ  በየቀኑ የምንወስዳቸው መድሃኒቶች ውጤታማ ለመሆናቸው ትንፋሻችንን መከታተል ተገቢ ነው፡፡

መድኃኒቶች በዓይነታቸው እና በአወሳሰዳቸው  እንደ በሽታው ክብደት ይለያያሉ፡፡ ስለሆነም የአስም በሽተኛ ከጤና ባለሙያ የሚታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድ በሽታውን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከእነዚህ መድኃኒቶች በተጨማሪ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች በሽታውን የሚያስነሱባቸውን  ነገሮች ካወቁ ማስወገድ ወይም በዛ አካባቢ መገኘት የለባቸውም፡፡ ለአብነት በሽታው ቀዝቃዛ አየር የሚጠላ ከሆነ በአፍ ላይ ሻሽ ወይም ሌላ አድርጎ መጓዝ በጣም ይረዳል።

 

የአስም በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ይተላለፋል?

በማህበረሰቡ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የአስም በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በሳል ይተላለፋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ ስህተት ነው፤  የአስም   በሽታ  ከአንድ  ህመምተኛ   ወደ ሌላ  ሰው   በማንኛውም  መንገድ  አይተላለፍም፡፡ በደም ስር (Genetics) ግን በተወሰነ ያህሉ ከወላጅ  ወደ  ልጅ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን አባት እና እናት የአስም በሽታ ሲኖርባቸው ልጃቸው በበሽታው ይያዛል ማለት ሳይሆን የመጋለጡ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ማለት ነው፡፡

 

ከአስም በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምንድን ናቸው?

የአስም በሽታ ለሌለባቸው ሰዎች እንደ ቀላል ሊታዩ የሚችሉ እንደ ሳል (ጉንፋን) ያሉ የአየር ቧንቧ ኢንፌክሽኖች የአስም በሽታ ያለበትን ሰው የያዙ እንደሆነ በጣም ጠንተውበት  አስጊ  ደረጃ ላይ ማድረስ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነውም የአስም በሽታ የሚቀሰቅስ/ እንዲከፋ የሚያደርግ ችግር ስላለባቸው ነው፡፡

የአስም በሽታ በህክምና ባለሙያ የተሰጠውን  መድኃኒት በአግባቡ አለመውሰድ ወይም ሐኪም ቤት ሄዶ አለመታከም በደቂቃዎች ወይም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የአተነፋፈስ ሥርዓት እንዲዳከምና ታማሚው በበሽታው እንዲሰቃይ ያደርጋል፡፡አልፎ ተርፎም ለህልፈተ ሕይወት ይዳርጋል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here