የአሳል ኃይቅ በጅቡቲ ታጁራ ሰላጤ ከምድር ወለል በታች 153 ሜትር ጥልቀት ላይ የሚገኝ ጨዋማ ኃይቅ ነው:: ጨዋማው ኃይቅ ከጅቡቲ ከተማ በስተምዕራብ 120 ኪሎ ሜትር ይርቃል::
የአሳል ጨዋማ ኃይቅ 19 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ስድስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ስፋት ተለክቷል:: የኃይቁ የመጨረሻው ጥልቀት 40 ሜትር አማካይ ጥልቀቱ ደግሞ ሰባት ነጥብ አራት ሜትር ነው።
በጨዋማው ኃይቅ ዕፅዋትም ሆነ እንስሳት አይገኙበትም:: ደረቁ የኃይቁ ክፍል ከመገኛው ጥልቀት የተነሳ በሙቀት ውኃው በመትነኑ የተፈጠረ ነው:: በመሆኑም በሰሜናዊ ምዕራብ የኃይቁ ክፍል የጨው ግግር በላይኛው ገፅ እንዲታይ አድርጐታል::
የአሳል ኃይቅን በዙሪያው ያሉ የመሬት ውስጥ ምንጮች በውኃ ያረሰርሱታል:: በጥልቀቱ በዓለም ከሙት ባህር እና ከጋሊሊ ባህር ቀጥሎ በሦስተኛነት ተቀምጧል:: የኃይቁ መገኛ በሙቀቱ የማይመች፤ በተዳፈኑ እሳት ገሞራ የተከበበም ነው::
በኃይቁ ውስጥ መዋኘት አይመከርም፣ ለዚህ ደግሞ ጨዋማነቱ የበዛ በመሆኑ በገላ ላይ የማይለቅ አሻራ ወይም ጠባሳ የሚያሳርፍ መሆኑ ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው:: የኃይቁ የጨዋማነት መጠኑ ከ34 ነጥብ ስምንት እስከ 40 በመቶ ተለክቷል:: በዓለም በአንታርክቲክ ከሚገኘው 47 በመቶ የጨዋማ መጠኑ ከተለካው ዶንጁዋን ኩሬ በመቀጠል በሁለተኛነትም ተቀምጧል::
ከጨዋማው ኃይቅ ጅቡቲ ጨው በስፋት በማምረት ወደ ኢትዮጵያ ከመላክ ባሻገር ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክም የምጦኔ ሀብቷን እንደምትደጉም ተብራርቷል::
የአሳል ጨዋማ ኃይቅ ለጉብኝት የሚመከር ቦታ ነው:: ነገር ግን የሚጠይቀው ወጪ ውድ መሆኑ ብዙዎችን ወደ ስፍራው ከማቅናት እንደሚገታ ነው የተገለፀው:: የዓየር ንብረቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ በመሆኑም በዕግር አይሞከርም፤ በታክሲ ለመጓጓዝ ደግሞ ለአንድ ሰው 35 ዶላር አካባቢ ይጠይቃል::
ለዘገባችን ወርልድ አትላስ፣ ናሽናል ፓርክ ወርልድዋይድ እና ብሪሊያንት ኢትዮጵያ ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም