የጠፋዉ ሰይፍ

0
152

በፈረንሳይ ሮካማንዱር በተሰኘች ጥንታዊ አነስተኛ ከተማ  ከመሬት ሰላሳ ሦስት ሜትር ከፍታ ካለው አለት ስንጥቅ ውስጥ ተጣብቆ 1,300 ዓመታት ያስቆጠረ፣ የከተማዋ መለያ መስህብ የነበረ ሰይፍ ባልታወቀ መልኩ መጥፋቱን ፈርስት ፖስት ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል::

የሰይፉን ጥንተ መሰረት አስመልክቶ በአስራ አንደኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ገዢ አነስተኛዋን ከተማ ለመከላከል ባደረገው ጥረት ሰይፉ በአለቱ መካከል ተጣብቆ መቅረቱን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው።

ሰይፉ በክፍለ ዘመኑ በነበረው ንጉሥ አርተር ከተማዋን ከጠላት ለመከላከል መወርወሩ እና ተጣብቆ መቅረቱ ነው በአፈ ታሪክ የሚታወቀው::  ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ለትንሿ ጥንታዊ ከተማ መለያ፣ መስህቧ- መታወቂያዋ ሆኖ ቆይቷል::

የከተማዋ ባለስልጣናት ወይም አስተዳዳሪዎች ጥንታዊውን ቅርስ  ለማግኘት ፍለጋቸውን ቢያያዙትም ፍንጭ ማግኘት አለመቻላቸውን ነው ያስታወቁት::

የጥንታዊዋ አነስተኛ ከተማ ኗሪዎች የከተማቸው መስህብ፣ መታወቂያ ባልታወቀ መልኩ መጥፋቱ የዕግር እሳት እንደሆነባቸው በቁጭት ተናግረዋል – ለባለስልጣናት::  ቀጥ ያለውን የዓለት ግድግዳ ሰራቂው ሽቅብ እንዴት መወጣት ቻለ ? ዕንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል::

የትንሿ ከተማ ኗሪዎች የራሳቸው የአካል ክፍል የተሰረቀ ያህልም አንገብግቧቸዋል:: ለዘመናት ከሰይፉ ጋር ተጋምዶና ተዛምዶ የኖረ ታሪካቸው መጥፋቱን በምሬት አውስተዋል::

የከተማዋን ጥንታዊ መለያ ለሌሎች ማስተዋወቂያው መስህብ ከኗሪዎች አንዱ ወስዶት ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም- ኗሪዎች:: ምነው ቢሉ? ሰው እንዴት የአካል ክፍሉን ይሰርቃል? ከራሱ ራሱ እንዴት? ሲሉም ይሞግታሉ:: ለማንኛውም “ዕውነት እና ንጋት እያደረ ነው” የሚለውን ብሂል መቋጫ አድርገነዋል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here