የኮሪያዎች ታሪክ

0
221

ጸጥ ያለው ማለዳ ምድር  የምትባለው ኮሪያ ከጃፓን በስተ ምእራብ ትገኛለች፤፤ ሶስት ስርዎ መንግሥታት ውህደት በመፍጠር ለሺዎቹ ዓመታት ራሳቸውን አስከብረው ዘልቀዋል፤፤ በክፍል አንድም ይህን የተመለከተ ጥንታዊ ኮሪያን ታሪክ አይተን ነበር ቀጣዩን እነሆ፦

በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የጃፓናውያኑን ወረራ ተከትሎ የ200 ዓመታት ሰላም አከተመለት:: የኮሪያው ኮሶን ስርወ መንግሥት እና የቻይናው ሚንግ መሪዎች በመጨረሻ ጃፓናውያንን ድል ነሱ፣ ነገር ግን የቀድሞ ብልጽግናቸውን መልሰው ማግኘት አልቻሉም:: በ1636 ዓ.ም የማንቹሪያውያን ወራሪዎች የሚደግፉ ዳይናስቲን አስወገዱ እና አዲስ ስርወ መንግሥት መሰረቱ ፣ የቂንግ ስርዎ መንግሥትን:: የቂንግ ስርወ መንግሥት የኮሪያውያኑን እንደ ገባር የመሆን ህብረት ጠየቀ እና አገኘ::

በቀጣዮቹ 200 ዓመታት ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ እና የአሜሪካ መርከቦች ባህታዊዋን ስርወ መንግሥት፣ ኮሪያን ለንግድ ግንኙነት ክፍት ሊያደርጉ ሞክረው አልተሳካላቸውም:: በ1868 ዓ.ም ጃፓን የንግድ መብት የሚሰጣትን የካንግህዋን ስምምነት እንድትፈርም ኮሪያን አስገድዳ አስፈረመች:: ይህን ተከትሎም ሌሎች ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በኮሪያ ላይ ስምምነቶችን አካሂደዋል::

በ1800 ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ጃፓን በእስያ ወታደራዊ ኃይሏን እያስፋፋች ነበር:: በምስራቅ እስያ የአውሮፓውያኑ ኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት ጫፍ በደረሰበት በ1890ዎቹ የጃፓን መሪዎች የሀገሪቱ ስትራቴጅያዊ የመከላከል አድማስ ኮሪያን በማካተት መስፋት እንዳለበት ወሰኑ:: በመሆኑም ጃፓን በኮሪያ ጉዳይ የመሳተፍ እና ጣልቃ የመግባት አዲስ ምእራፍ ጀመረች ዋና አላማው በኮሪያ ላይ ተፅዕኖ የነበራቸውን የቻይና እና የሩሲያን ተፅዕኖ ማጥፋት የሚል ነበር:: የቻይናውያን ተፅዕኖ በኮሪያ ያበቃው  ከ1886 ዓ.ም እስከ 1887 ዓ.ም ድረስ ከዘለቀው የቻይና እና የጃፓን ጦርነት በኋላ ነበር:: እንዲሁም በተመሳሳይ ከ1896 እስከ 1897 ዓ.ም ድረስ በሩሲያ እና በጃፓን መካከል የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ የሩሲያ ተፅዕኖ በኮሪያ ላይ አብቅቶለታል::

በመሆኑም በ1897 ዓ.ም ከሩሲያ ጃፓን ጦርነት ማግስት የጃፓን መንግሥት የኮሪያ የበላይ ጠባቂ መሆኗን በብቸኝነት አወጀች:: በነሐሴ ወር 1902 ዓ.ም ደግሞ ይህ ስልጣኗ ተለወጠ እና ኮሪያ የጃፓን ኢምፓየር አንዷ ሕጋዊ ቅኝ ግዛት ሆነች:: ይህ በኮሪያ ረጅም ታሪክ ውስጥ መላ ሀገሪቱ እና ሕዝቧ በባእዳን አገዛዝ ስር ሲወድቅ የመጀመሪያው ነበር::

ጃፓን በዚህ ወቅት የኮሪያን አስተዳደር የማዳከም ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ኮሪያን በእጇ የማስገባት ጥርጊያውን አመቻቸች:: ኮሪያውያን ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ስለተዳከሙ የጃፓንን ተግዳሮቶች መቋቋም አልቻሉም:: በመሆኑም በወርሀ ነሀሴ 1902 ዓ.ም ላይ ለ518 ዓመታት ያህል የገዛው የኮሪያውያኑ የኮሶም ስርወ መንግሥት ለጃፓን ተንበረከከ፣ እናም ከዚያን እለት ጀምሮ ኮሪያ በጃፓን ቅኝ ግዛት ስር ወደቀች:: ጃፓንም በኮሪያውያኑ ባህረገብ ምድር ላይ አስከፊውን የ35 ዓመታት አገዛዝ  ጀመረች::

የጃፓናውያኑ የቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ከ1902 እስከ 1937 ዓ.ም ድረስ ዘለቀ:: ጃፓን ወታደራዊ ኃይሎቿን ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ለሚያደርጉት ጦርነት ማገዝ እንዲችል የባቡር መጓጓዢያ መስመር አስፋፍታ ነበር:: የኮሪያውያን ንብረት የሆኑ ኩባንያዎች ወደ ጃፓን የሚላክ ሩዝ እንዲያመርቱ ተገደዱ ይህም ኮሪያውያንን ለከፋ ችግር ዳርጓቸዋል:: ኮሪያውያን አስገዳጅ በሆነ የጉልበት ሥራ ውስጥ አደገኛ ሥራዎችን እንዲሠሩ ይገደዱ ነበር:: ኮሪያውያን በተጨማሪም በባህል ረገድ ትልቅ ተፅዕኖ ደርሶባቸው ነበር:: የኮሪያውያን ቋንቋ በትምህርት ቤቶች የተከለከለበት እና ኮሪያውያንም ጃፓናዊ ሥም እንዲኖራቸው ይገደዳሉ:: በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኮሪያውያን ልጃገረዶች እና ወይዛዝርት ለጃፓን ወታደሮች የወሲብ ባሪያዎች ይደረጉ ነበር::

ወቅቱን ያልጠበቀው የጃፓናውያኑ ወረራ የኮሪያውያኑን የዘመናዊነት ሂደት አደናቅፏል፤ ምክንያቱም ሀገሪቱ በራሷ አነሳሽነት የጀመረቻቸው የለውጥ ሥራዎች በመተግበር ረገድ  እርምጃዎችን እየወሰደች ነበር:: አንዳንድ ጃፓን በኮሪያ ያላትን ፖሊሲ በቸልታ የሚያልፉ የታሪክ ባለሙያዎች በቅኝ ግዛቱ ወቅት በኮሪያ አኮኖሚያዊ እና የትምህርት ስርአት ላይ ቀላል የማይባል እመርታ መደረጉን ይናገራሉ:: የጃፓናውያኑ ወረራ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለኮሪያ ዘመናዊነት ጠቃሚ እንደሚሆን ይሞግታሉ:: ምንም እንኳ በ1902 ዓ.ም እና በ1937 ዓ.ም መካከል በተወሰነ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ እድገት መኖሩ ላይካድ ቢችልም  ዋነኛ ተጠቃሚዎች ጃፓናውያን እና ጥቂት ኮሪያውያን ባንዳዎች ነበሩ:: ብዙኃኑን የኮሪያ ሕዝብ ለከፋ ድህነት እና ማይምነት ተዳርጓል::

ኮሪያውያን ከዚህ አስከፊ የጃፓናውያኑ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን ለማስመለስ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ይታገሉ ነበር :: በመሆኑም  ኮሪያውያን በጀመሩት ትግል የካቲት 22 ቀን 1911 ዓ.ም (March 1, 1919)  በጃፓናውያን ላይ መጠነ ሰፊ ሀገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ ነፃነት አውጀው ነበር::

የጃፓናውያኑ የወረራ ዘመን የጃፓንን  የበላይ ጠባቂነት እና ቅኝ ገዥነት ኮሪያውያን ለመቀበል እምቢ ማለታቸው ይታወቃል:: መጠነ ሰፊውን የማርች አንድ ንቅናቄ ሕዝቡን ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለነፃነት እንዲፋለም አነሳስቷል:: የንቅናቄው መጠን እና የጋለ ስሜት የሚከተሉት ጨካኝ ፖሊሲ በስተመጨረሻ የኮሪያውያኑን ብሔራዊ መንፈስ እንደሰበረው ያምኑ የነበሩትን ጃፓናውያኑን አስደንግጧል::

 

የኮሪያ መከፈል

በመጨረሻም ኮሪያ ነፃነቷን ያወጀችው ነሐሴ 9 ቀን 1937 ዓ.ም ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ መሸነፏ እውን በሆነበት ወቅት ነበር::

በጃፓን መሸነፍ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነሐሴ 9 ቀን 1937 ዓ.ም በተጠናቀቀበት ጊዜ ነበር የኮሪያ ሕዝብ ነፃ የመውጣታቸውን ዜና በከፍተኛ ደስታ እና ግራ መጋባት የተቀበሉት:: ከጃፓናውያኑ ቀንበር በመላቀቃቸው ወሰን በሌለው ደስታ ሲጨፍሩ ነበር፡፡ ነገርግን ሀገራቸው   ለሁለት ወታደራዊ ዞኖች ልትከፍል መሆኑ ሲሰሙ ደስታቸው ላይ ውሃ ቸለሰበት:: አሜሪካ በሄሮሽማ ላይ የመጀመሪያውን አቶሚክ ቦምብ ከጣለች አንድ ቀን በኋላ ነሐሴ 2 ቀን 1937 ዓ.ም ሶቭየት ኅብረት በጃፓን ላይ ጦርነት አወጀች:: አሜሪካ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኮሪያን በጋራ ለመውረር ከሶቭየቶች ጋር ተስማሙ:: 38ኛው ፓራለል የተሰኘው ሰሜንን እና ደቡብን በሚከፍለው የሃሳብ መስመር ተለይቶ ለሁለቱ ኃያላን ተሸነሸነ::

ነሐሴ 18 ቀን 1937 ዓ.ም ሶቭየቶች ፒዮንግያንግ ገቡ እና ራሳቸውን የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ መንግሥት አድርገው አደራጁ:: ከ38ኛው ፓራለል በታች ደግሞ፣ ደቡብ ኮሪያ በአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች በመስከረም 1938 ዓ.ም ላይ ተወረረች:: ይህም የሶቭየት ወታደራዊ ኃይሎች ሰሜኑን መውረር ከጀመረበት አንድ ወር በኋላ መሆኑ ነው:: እናም አሜሪካኖችም ሴኡልን በመቆጣጠር የአሜሪካ ወታደራዊ መንግሥትን በደቡብ ኮሪያ መሰረቱ:: አሜሪካኖች በዚህ መንገድ ሶቭየቶችን ሙሉ ለሙሉ ኮሪያን እንዳይቆጣጠሩ አድርገዋል:: ኮሪያ ወደ ሁለት የወረራ ዞኖች ተከፈለች፣ እና የወደፊት ራስን የመቻል ውሳኔው በሁለቱ ኃያላን እጅ እንደወደቀ አድሪያን ቡዞ፣ ዘ ሜኪንግ ኦፍ ሞደርን ኮሪያ፣ መፅሐፍ ላይ ፅፎታል::

ቴልስ ኦፍ ቱ ኮሪያንስ፣ በተሰኘ ጆርናል፣ ዶ/ር ማርክ ቢ ኤም ሱህ እንደፃፉት በነሐሴ 1940 ዓ.ም ላይ በደቡብ ኮሚኒስት ያልሆነች የኮሪያ ሪፐብሊክ ተወለደች:: የመጀመሪያ ፕሬዝደንቷ ዶ/ር ሲንግማን ርሂ ሆኑ:: በመስከረም 1940 ዓ.ም ደግሞ ኮሚኒስት የሆነችው ሰሜን ኮሪያ ዲሞክራቲክ ፒፕልስ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮሪያ በይፋ ታወጀች:: ኪም ኢል ሱንግ የመጀመሪያው መሪ ሆኑ:: ለጊዜው ሀገሪቱ ለሁለት ወታደራዊ ዞኖች ትከፈል እንጅ በሂደት በአንድ መንግሥት ስር እንደሚዋሃዱ ነበር በኮሪያውያኑ ልብ ውስጥ ይመላለስ የነበረው ተስፋ:: ሁለቱ የወረራ ዞኖች በኋላ እንደሚዋሃዱ ታስቦ ነበር:: በዚህ ፋንታ ግን የቀዝቃዛው ጦርነት ክፍፍሉን አጠናከረው::

የሰሜን ኮሪያ ኃይሎች ደቡብ ኮሪያን በወረሩበት ሰኔ 18 ቀን 1942 ዓ.ም ላይ የቀዝቃዛው ጦርነት ውጥረት በኮሪያ ላይ ጦርነት አፈነዳ:: የሰሜን ኮሪያ ኃይሎች በሶቭየት ኅብረት እና በቻይና በመታገዝ ወደ ደቡብ ኮሪያ ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈጸሙ::

ይህን ጉዳይ በዝምታ ያላዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ወራሪው ተኩስ እንዲያቆም እና የያዘውን ስፍራ ለቆ ከሰኔ 18 በፊት ወደነበረበት ስፍራ እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጠ:: ይሁን እንጂ ይህን ትዕዛዝ በመጣስ ወራሪው ኃይል በአጭር ቀናት ውስጥ ወራሪዎቹ የአንጅን የባህር ሰርጥ ደረሱ:: በመሆኑም በጄኔራል ዳግላስ ማካርተር መሪነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአሜሪካ መንግሥት ኃይሎች ደቡብ ኮሪያ ወራሪዎቿን ወደ መጡበት እንድታስመልስ ድጋፍ አደረጉላት:: የኮሪያውያን ጦርነት የተኩስ አቁም እስከተፈረመበት 1946 ዓ.ም ድረስ ተራዝሞ ነበር:: የሦስት ሚሊዮን ኮሪያውያንን፣ 900,000 ቻይናውያንን እና የ54,000 አሜሪካውያንን ሕይወት ቀጥፏል:: የኮሪያ ሕዝብ በዋናነት የተከፋፈለች ሀገሩን እንደገና ለማዋሃድ ነበር ጦርነት አድርጎ ዋጋ የከፈለው:: ግን አልሆነም፣ ጦርነቱ ኮሪያ ለሁለት ከፍሏት አለፈ:: በሰሜን ኮሪያ እና በደቡብ ኮሪያ የሚፎካከሩት ሁለቱ አገዛዞች ከባድ የጦር መሳሪያ የታጠቁ መንግሥታት ሆኑ እና ኮሪያ ዛሬ የተከፋፈለች ምድር ሆናለች::

 

ቃኘው በኮሪያ

ሲሞን ስኮርዲለስ እንደፃፈው፣ በጋሻው ድረሴ ወልደ ሰማያት ‘ቃኘው’ ብሎ በተረጎመው መፅሀፍ ላይ እንደተገለፀው፣ በዚህ ከባድ ዓለማቀፍ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት እና የአሜሪካ ሠራዊት እውቅና የተሰጠው ታላቅ የጀግንነት ተሳትፎ አድርጋለች:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል እንደመሆኗ ኮሪያ ጭንቅ ውስጥ  በገባችበት ወሳኝ ወቅት ላይ የመንግሥታቱን ድርጅት ጥሪ ቀድመው ከተቀበሉት እና ምላሽ ከሰጡት ትመደባለች::

“ኢትዮጵያ የቃኘው ዘማች ወታደሮቿን ወደ ኮሪያ በመላክ የነፃው እና የዲሞክራሲው ዓለም አጋር መሆኗን ለተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ተገዥነቷን ብቻ አይደለም ያረጋገጠችው:: ኢትዮጵያ በእነዚህ ዘማች ጀግና ወታደሮቿ አማካይነት አቻ የሌለውን የሕዝቧን የውጊያ ጥበብ ለዓለም አሳይታበታለች:: መኮንኖቹ በዓለም እጅግ ሰልጥነዋል ከተባሉት ወታደራዊ መኮንኖች ባልተናነሰ ዘመናዊ ጦር ማደራጀት እና መምራት መቻላቸውን አሳይተዋል:: በኮሪያው የጦርነት ፈተና የኅብረቱ አባል ሀገሮች ሁሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፈተናውን አልፈዋል:: ከአላፊዎቹ መሀል ደረጃ ይውጣ ከተባለ ግን ኢትዮጵያውያን አንደኛ ናቸው” ብሏል::

በአምስት ዓመታቱ የኮሪያ ጦርነት በሦስት ዙር ወደ ኮሪያ ዘምቶ ግዳጁን በሚደንቅ ጀግንነት የተወጣው የቃኘው ሰራዊት 253 ውጊያዎችን አድርጓል፣ 120 ተሰውተውበታል፣ እንዲሁም 563 ቆስለውበታል:: ለኮሪያ ሕዝብ በቃኘው ለከፈለው መስዋእትነት ምስጋና ይሆን ዘንድ ደቡብ ኮሪያ እስካሁን በሕይወት ያሉ የጀግኖቹን ቤተሰቦች በመርዳት ውለታ እየከፈለች ትገኛለች:: በኮሪያ ሕያው መታሰቢያ አቁማላቸዋለች::

ከ1300 ዓመታት በላይ በአንድነት የዘለቀችው ኮሪያ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ሕዝቧ ዘወትር የሚመኘውን አንድነት እውን ሳያደርግላቸው ለሁለት ሃገርነት ከፍሏት አልፏል:: ዛሬ ሁለቱም ኮሪያውያን አንድነትን ከሩቅ አየናፈቁ የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነው አርፈውታል:: አንድ ቤተሰብ ሁለት ሀገር ሆነው በርዕዮተዓለም ልዩነት የአንድነት ተስፋቸው ጨለም ያለ ይመስላል፣ ዘወትር ለመጠፋፋት የሚከጃጀሉ ባላንጣዎች ሆነው በአይነ ቁራኛ የሚተያዩ ሆነዋል::

ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ በየራሳቸው መንገድ ለማደግ ጉዞ ከጀመሩ ቆይተዋል:: ደቡብ ኮሪያ ከምዕራባውያኑ ጋር ተወዳጅታ ከዓለም በኢኮኖሚ ከተመነደጉ ጥቂት ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች:: ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በተቃራኒው ከኮሚኒስቱ ዓለም ጋር የመወገን አዝማሚያ ይታይባታል:: በኢኮኖሚ እድገቷ ከጎረቤቷ በእጅጉ ብታንስም በወታደራዊ ሳይንሱ ብዙ ርቀት ሂዳለች:: አህጉር አቋራጭ ዘመናዊ ባልስቲክ የኒኩሌር ተሸካሚ ሚሳኤሎች ባለቤት ናት የሕዝቡ ሕይወትስ ? ውስጡን ለቄስ::

ይህም ሆኖ የደቡብ እና የሰሜን ኮሪያ ውህደት ሀገሪቱ ያለፍላጎቷ በባእዳን ኃይሎች ፍላጎት ከተከፋፈለችበት ከ1937 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ የኮሪያ ሕዝቦች የመጨረሻ ግብ እንደሆነ ቀጥሏል:: የመዋሃድ እድሉ በሁለቱ የፖለቲካ ልሂቃን እጅ ነው:: አንዳንድ የመዋሃድ ምልክቶች ታይተው የጠፉ አጋጣሚዎች ነበሩ:: አንድ መንግሥት አንድ ሀገር የመመስረት ፍላጎት ለመኖሩ የመሪዎች የተለያዩ የምክክር መድረኮች ተዘጋጅተው እርቅ የማድረግ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ:: በ2018ቱ የዓለም ዋንጫን ሁለቱ ኮሪያዎች በጋራ ያዘጋጁበት የጋራ ብሔራዊ ቡድን ያሰለፉበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው::

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here