የጣና ሐይቅ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውኃ አካላት በስፋት ትልቁ ሐይቅ እንደሆነ እሸቴ ደጀን (ዶ/ር) የጣና ሐይቅ ዓሳ ኃብትና ዘላቂ ልማት በሚል መጽሐፋቸው አስፍረዋል:: በጥልቀቱም በአማካኝ ዘጠኝ ሜትር እንደሆነ ይነገርለታል:: ሐይቁ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው:: በውስጡ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችን በመያዝ ብዙዎች የዕለት እንጀራ የሚያገኙበት እና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ነው:: የተለያዩ ገዳማትን እና ደሴቶችን በውስጡ በመያዙ ለቱሪስቶች መዳረሻም ነው:: በቱሪዝሙ ዘርፍ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ገቢ በማስገኘት አበርክቶው የላቀ ነው::
ጣና ሐይቅ ለመስኖ ልማት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምንጭ በመሆን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ድርሻው ከፍተኛ ነው:: ሐይቁ የአማራ ክልል ሀብት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያንም እየሰጠ ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ታሪክም፣ ውበትም በሆነው ጣና ሐይቅ ከ500 ሺህ በላይ አባወራዎች በዙሪያው እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ::
ጣና ሐይቅ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በብዝኃ ሕይወት (ባዮስፌር ሪዘርቭ) በ2007 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጣና ሐይቅ ዋነኛ ጠላቱ እና ሕመሙ የእንቦጭ አረም ሆኖ ቀጥሏል:: ከከተማዋ እና ከዙሪያዋ ወደ ሐይቁ የሚገባው ተረፈ ምርት፣ በሐይቁ ዳርቻ የሚጣሉ ፕላስቲኮች እና መሰል ቁሶች ለሐይቁ መበከል ተጨማሪ ፈተና ናቸው:: ችግሩ በፍጥነት ካልተገታ ሕልውናው አደጋ ውስጥ ይገባል:: የእንቦጭ አረም ለመጀመሪያ ጊዜ በሐይቁ መከሰቱ የታወቀው በ2004 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ምሁራን አማካኝነት በመገጭ ወንዝ መግቢያ አካባቢ እንደሆነ የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጄንሲ ዓመታዊ መጽሔት ያስነብባል::
እንቦጭ በጣና ሐይቅ ተከሰተ ከተባለበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ የሐይቁን ህልውና ለመታደግ ከሀገር ቤት እስከ ዲያስፖራ፣ ከሀገር በቀል ዕውቀት እስከ ውጭ ቴክኖሎጂ ማሻገር፣ ከተማሪ እስከ ከፍተኛው ምሁራን፣ ከቀበሌ እስከ ፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፤ ዳሩ ግን እንቦጭን በማስወገድ ጣና ሐይቅ ከገጠመው ፈተና ማላቀቅ አልተቻለም::
የጣና ሐይቅ ከእንቦጭ አረም ባሻገር በደለል እየተሞላ የውኃ መጠኑ እየቀነሰ ለእርሻ ሥራ እየዋለ ነው:: ደለሉ ሐይቁን ወደ መሬትነት እየቀየረው ይገኛል:: ደለሉ ለመጤ አረሞች መስፋፋት ምቹ ሁኔታንም ፈጥሯል:: ይህም ሐይቁን ለተደራራቢ ችግሮች ዳርጎታል:: የጣና ሐይቅ እና አካባቢው በደለል መሞላት፣ በከተሞች በሚለቀቅ ፈሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ መበከሉ፣ የውኃ አዘል መሬቶች ወደ እርሻ ሥራ መቀየሩ፣ በመጤ አረም መወረሩ እና የነባር ተክሎች መመናመን … የጣና ሐይቅን ህልውና አደጋ ላይ ጥለውታል:: ደለሉን ተከትለው ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ የእርሻ ሥራን ያከናውናሉ:: በአጠቃላይ ሐይቁን በርካታ ችግሮች እየተፈታተኑት ነው:: ለዚህም ነው ታዋቂው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ያዜመዉ፤
“ጣና የአገር አድባር የሁላችን ግርማ፣
ቆየን ሰነበትን ህመሙን ስንሰማ!
ቢዋኙበት ምቹ ቢያጠምዱበት ቸር ነው፣
አይተን እንዳላየን ዝምታው ምንድን ነው፣
አባይን በሆዱ ችሎ ያሳለፈው፣
ዛሬ ቀን ከፍቶበት አረም አሸነፈው!”
የጣና ሐይቅ ቀድሞ ከነበረበት 6602 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት በግማሽ ቀንሶ 3200 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እንደደረሰ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ አሚኮ በ2013 ዓ.ም በዘጋቢ ዶክመንተሪው አሳይቷል:: ወደ ጣና ሐይቅ በሚገቡ ገባር ወንዞች አማካኝነት በየዓመቱ 37 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን በላይ ደለል አፈር ሐይቁን ይቀላቀላል:: በየዓመቱም ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊ ሜትር ጥልቀት ይቀንሳል:: ይህን ችግር ለመከላከልም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ፣ የእርከን ሥራ፣ ችግኝ መትከል (የአረንጓዴ አሻራ)፣ ልቅ ግጦሽን መከላከል … በትኩረት መሠራት አለባቸው ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ::
አቶ እያዩ ብርሃኔ የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተባባሪ ናቸው:: በ2016 ዓ.ም በጣና ሐይቅ ላይ የእንቦጭ አረም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን ለበኩር ጋዜጣ በስልክ አስታውቀዋል:: በአማራ ክልል የተፈጠረው የሠላም እጦት የእንቦጭ ነቀላ ሥራዎችን ተዘዋውሮ ለመሥራት አስቸጋሪ እንዳደረገው አብራርተዋል::
አስተባባሪው እንዳሉት በሐይቁ ዳርቻ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በራሳቸው ተነሳሽነት አረሙን እያስወገዱ ነው:: ነገር ግን ሕዝቡን አስተባብሮ ለመሥራት እንቅፋት መፍጠሩን ነው የተናገሩት:: ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲሠራ የቆየ መሆኑን የተናገሩት አስተባባሪው በዚህ ዓመት ግን በግጭቱ ምክንያት ሥራዎችን ለማከናውን ፈተና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በምሥራቅ ደንቢያ የእንቦጭ አረምን በመንቀል እንቅስቃሴዎች እንዳሉ አቶ እያዩ አስረድተዋል:: በጎንደር ዙሪያ ከ930 በላይ ሔክታር በእንቦጭ አረም መወረሩን በማንሳት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ዘጠኝ ነጥብ 7 ሔክታር ብቻ መነቀሉን አክለዋል:: የእንቦጭ አረም እየተስፋፋ መሆኑን ያመላከቱት አስተባባሪው በዚህ ከቀጠለ “ጣናን እንዳናጣው” ሲሉ ነው ስጋታቸውን የተናገሩት::
በእንቦጭ የተወረረው ጣና ሐይቅ የዓሳ እርባታ ሥራን አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው የገለፁት:: በመሆኑም በጎ አድራጊዎች፣ ረጂ ድርጅቶች፣ አጋር አካላት እና መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው ጣናን መታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል:: ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ሠላም በመሆኑ ሰላም ተፈጥሮ ወደ ሥራ መግባት አለብን ብለዋል:: ስለዚህ ሁሉም አካል ለሰላም መሥራት ይኖርበታል::
የደቡብ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃ አካላት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ እማሙሽ ንጉሴ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በነበረው እንቅስቃሴ አረሙን መቆጣጠር ተችሎ ነበር:: ይሁን እንጂ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተፈጠረው የሠላም እጦት ምክንያት በሐይቁ የተስፋፋውን የእንቦጭ የአረም መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል:: በዐሥር ቀበሌዎች ችግሩ በስፋት ተከስቷል:: በተለይ ሊቦከምከም ወረዳ ላይ በስፋት መከሰቱን ተናግረዋል:: ችግሩ ሰፊ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይጠይቃል:: በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ሙያተኞች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉም ተናግረዋል:: የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችንም ማከናወን እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት:: አርሶ አደሮች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጭ ሥራዎችን ማከናወን አልተቻለም ነው ያሉት::
ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ያስፈልጋል ያሉት ቡድን መሪው ውኃ አዘል መሬቶች በሙሉ ለእርሻ ሥራ እየዋሉ በመሆኑ ለሐይቁ አደጋ ደቅኖበታል ብለዋል:: በዚህ ምክንያት ደግሞ የሚረጩ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች እና የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሐይቁ በመግባቱ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል::
በመሆኑም የተቀመጠው ሕግ እና አሠራር መተግበር እንዳለበት አመላክተዋል:: ከፌደራል እና ከክልሉ መንግሥት ጀምሮ ትኩረት እንደተነፈገው በመግለጽ ችግሩ የተለየ ትኩረትን ይጠይቃል ብለዋል::
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ ዋና ሥራው ያለው ቀበሌ እና ወረዳ ላይ በመሆኑ በቂ ሀብት ሊመደብ ይገባል:: አጋር እና ባለድርሻ አካላትም በቅንጅት መሥራት አለባቸው::
ክልሉ በገጠመው የሠላም እጦት ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የእንቦጭ አረም እጅግ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ተስፋፍቶ ባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ባለው የሐይቁ አካባቢ ድረስ ተስፋፍቷል፤ በመሆኑም ከአጭር ጊዜ አኳያ የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይም በክልል ቢሮ የሚገኘውን የመንግስት ሠራተኛ በማስተባበር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጄንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋሲል ድልነሳ ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል::
ሐይቁ ያለበትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ ታሳቢ በማድረግ በሚገባን ልክ ሠርተናል ብሎ ማሰብ አይቻልም ብለዋል:: በክልሉ የተከሰተው ግጭት ሥራዎችን ለማከናወን አስቸጋሪ አድርጎታል:: ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ አሠራር ተዘርግቶለት መሠራት ነበረበት ብለዋል:: በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ብዝኃ ህይወት እንዳይጠፍ ከወዲሁ መሠራት ይጠይቃል ብለዋል::
ስለሆነም ስነ ምህዳራዊ ተግዳሮቱን ከመፍታት ጀምሮ የሐይቁን ሁለንተናዊ ጤንነቱን ለማረጋገጥ ከዘመቻ ሥራ በመውጣት ዘላቂ የሆነ ስርዓት ሊዘረጋለት ይገባል ነው ያሉት፡፡
አረሙን በእጅ ከመንቀል ባለፈ ስነ ህይወታዊ የማስወገጃ ስልትን ተጠቅሞ በዚህ ዙሪያ የላቀ መረዳት እና የመፈጸም አቅም ያላቸውን ወገኖች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቆርቋሪ ወገኖችን በማሳተፍ ተጨባጭ ሥራዎችን በመሥራት የጣና ሐይቅን ዘላቂነት በማረጋገጥ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል:: እንቦጭን ለማስወገድ ቅንጅታዊ አሠራር በተገቢው መንገድ መከናወን እንዳለበትም አስረድተዋል:: የተቀዛቀዘውን የእንቦጭ አረም ነቀላ ለማካሔድ በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል:: ከዚህ ትውልድ ብዙ ይጠበቃል:: ካለንበት የዝምታ እና የቸልታ ልጓም ልንፈታ ይገባል::
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም