“በአማራ ራዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘፈን ምርጫን በቀጥታ እንዲሄድ አድርጌያለሁ”

0
172

የተወለዱት ባሕር ዳር ከተማ በቀድሞው አጠራር ቀበሌ 12 ነው:: አፈር ፈጭተው ያደጉት ደግሞ በቀበሌ 03 ነው::የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐጼ ሠርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በተለምዶ የቀበሌ 03 ልጆች በአብዛኛው በስፖርት ክንዋኔዎች ቀልባቸው ይሳባል፤ እሳቸው ግን በተቃራኒው ወደ ትያትር እና የቴክኒክ ቁጥጥር ተስበዋል:: በአማራ ራዲዮ እና በሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ጉልህ ሚናዎችን ተጫውተዋል:: አርቲስት፣ መምህር እና የቴክኒክ ባለሙያ በለጠ ወንዴ::አቶ በለጠ ወንዴ ከበኩር ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ፡፡

እንዴት ወደ ቲያትር እና የሬዲዮ ቴክኒክ ቁጥጥር ሊሳቡ ቻሉ?

በመጀመሪያ ወደ ትያትር የተሳብኩት እና የገባሁት በጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገባሁ በኋላ ነው:: በተለይ ታላቅ ፍላጎት እንዲያደርብኝ ያደረጉት የአማረኛ ቋንቋ መምህሬ አቶ ጥላሁን ደግፌ ናቸው:: እሳቸው ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ እንደ ትረካ ነበር የሚሆንልን::  በተለይ ለእኔ በግሌ ስሜቴን ይገዙኝ ነበር:: የትምህርት ቤቱ የትያትር ክበብ ደግሞ ዋና ሰብሳቢ ናቸው፤ አንድ ቀን ለትያትር ክበቡ አዳዲስ አባላትን ሲመዘግቡ ሳይ እኔም አባል ሆንኩ፡፡

ጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት እያለሁ ከአዲስ አበባ ታዋቂ የትያትር ተዋንያን ይመጡ ነበር::እነሱ ሲመጡ እንደምንም ብየ ተዋንያኑን እተዋወቃቸዋለሁ፤ ከዚያ በተለያየ ሥራ አግዛቸዋለሁ፤ ትያትሩንም በነጻ አይ ነበር፤ የከፈልኩበትን ጊዜ አላስታውስም:: ከዚያ ባለፈ የመብራት እና የድምጽ መሣሪያዎችን እንዴት እንደሚገጥሙ እና እንደሚቆጣጠሩ በደንብ እከታተል እና እማር ነበር::

ከጣና ሐይቅ ከወጣሁ በኋላ በባህል እና ቱሪዝም ስር አልፋ የሚባል የአማተር ትያትር ክበብ መሠረትን:: ባህል እና ቱሪዝም ያን ያክል አያግዘንም ነበር::ለትያትር ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረን ራሳችን ከምናገኛት ትንሽ ሳንቲም እየቆጠብን በዞኖች እና ወረዳዎች እየሄድን ብዙ ትያትሮችን ለመድረክ አብቅተናል::ለመጥቀስ ያክል፤ አራት የደም ጥሪዎች፣ መረብ እና የመጨረሻው መንገደኛ የሚሉትን ለሕዝብ አድርሰናል፡፡

 

ወደ ሬዲዮስ እንዴት መጡ?

በወቅቱ የማስታወቂያ ቢሮ ነበር የሚባለው፤ አቶ ታቦር ገ/መድህን የሚባሉ ኃላፊ ነበሩ፤ እሳቸው አማተር እያለን ትያትር ያሰሩን ነበር:: እንደሚታወቀው ትያትር ውስጥ ብዙ ግብዓቶች አሉ:: ከትወናው ባሻገር የመብራት እና የድምጽ ቁጥጥር ሥራዎችን ስከውን ስለሚያዩኝ በእኔ ፍላጎት አድሮባቸው ወይም ፈልገውኝ ይሆናል በሬዲዮ ረዳት ቴክኒሻያንነት ቀጠሩኝ፤ ጊዜው 1989 ዓ.ም ነበር:: በወቅቱ የነበሩ ባለሙያዎች ከሥራው ጋር ቶሎ እንድላመድ አደረጉኝ::  እኔም ፈጣን ነበርኩ መሰለኝ በፍጥነት ከሙያው ጋር ተለማምጄ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ቻልኩ:: ብዙ ፕሮዳክሽኖችን ኤዲት አድርጌያለሁ

 

ከወቅቱ ቴክኖሎጂ አንጻር እንዴት ነበር የምትሠሩት?

በስቱዲዮ ውስጥ በአብዛኛው ይሠሩ የነበሩት በክር ካሴት ሲሆን በከፊል ሲዲ አለ፤ ሪል ቴፕ እና ደግሞ የሲዲ ማጫወቻ ነበረ፤ ሪል ቴፕ እንደ ሼልፍ መደርደሪያ የሚመስል ክር የሚያጠነጥን መሳሪያ ነው:: ጋዜጠኛው ስቱዲዮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ያነባል( ይናገራል) ሪል ቴፑ ይቀርጻል፤ ጋዜጠኛው ቢሳሳት ቴክኒሻኑ ወደ ኋላ አጠንጥኖ ይመልስ እና እንደገና ከቆመበት አጫውቶ ጋዜጠኛው ዳግም እንዲያነብ ያደርገዋል::እንደ አሁኑ ኮምፒውተሮች ስላልነበሩ ድምጽ ተቀርጾ እና ታርሞ የሚተላለፈው በዚህ መንገድ ነበር፡፡

እንዳሁኑ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስላልነበረ ዝግጅቶችን ቀርጸን ስንሰራ የነበረው በካሴት ነበር:: ልክ በየቤታችን ሙዚቃዎችን በምናዳምጥበት በነበረው ካሴት ወደ ፊት ወደ ኋላ እያደረግን የተቀረጸው ባለጉዳይ ምናለ የሚለውን እና ቁልፍ ነጥቦች ወጥተው ፕሮግራሙ ይዘጋጃል:: ከዚያም ያዘጋጀነው ካሴት ወደ ሪል ቴፑ ይገለበጥና በሬዲዮው ይተላለፋል:: በጊዜው ከዚህ ውጪ በቀጥታ የሚተላለፍ ዝግጅት አልነበረም፡፡

 

በቀጥታ ሥርጭት የሙዚቃ ምርጫን እንዲሁም  ጭውውትን  (አጭር ድራማን) ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ራዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲተላለፉ አድርገዋል እስኪ ስለሁኔታው አጫውቱን?

በጊዜው አማራ ራዲዮ የሚያስተላልፈው ስርጭት የአንድ ሰዓት ነበር:: ከዛ ውስጥ ቅዳሜ ቀን ከዜና በኋላ ለ30 ደቂቃ የሚቆይ የአድማጮች የዘፈን ምርጫ ነበር:: የሞባይል ስልክ ይቅርና የመስመር ስልክም ቢሆን በአብዛኛው አድማጭ ዘንድ ባለመኖሩ በደብዳቤ ነበር አድማጭ ዘፈን የሚገባበዘው:: ፕሮግራሙ ደግሞ ከሙዚቃ ካሴቶች ወደ ሪል ቴፕ ተቀርጾ አብሮ የአስተዋዋቂው ድምጽ ገብቶበት ከተቀዳ በኋላ አየር ላይ ይወጣል:: ስለዚህ 30 ደቂቃ ሙሉ የተቀዳውን ለአድማጭ ከፍተህ ቁጭ ብለህ ማውራት ነው:: ይህ ምቾት አይሰጠኝም ነበር፤ ስለዚህ ለምን ካሴቱን እያስገባሁ በቀጥታ አልሞክረውም? የሚል ሃሳብ መጣልኝ።

አሁን ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት እየሰራ የሚገኘው  ጋዜጠኛ ሽበሽ አለማየሁ ነበር በወቅቱ የዘፈን ምርጫ ተረኛ አቅራቢ፤  በደንብ እንግባባ ነበር:: እንደተለመደው በሪል ቴፕ ለመቅዳት ሲመጣ ለምን በቀጥታ አንሞክረውም? አልኩት:: “የሚከብድ ይመስለኛል አለኝ”፤ ግዴለህም ስለው “እሺ እንለማመድ” አለኝ:: በቀጥታ አየር ሰዓት ሳንገባ መለማመድ ጀመርን፤ ካሴቶቹ ልክናቸው ወይ?  መክፈት ይችላል? ጊዜውን ይጠብቃል? የሚለውን ስጋቱን ለማስወገድ የእኔንም ፍላጎት ለመፈጸም ተለማመድን:: የንዋይ? ሲለኝ የንዋይን እከፍታለሁ፤ የእከሌን ሲለኝ እከፍታለሁ፤ በዚህ መንገድ ተለማመድን:: ይህ ሁሉ ሲሆን ፕሮግራም አስተባባሪው አያውቅም፡፡

ጋዜጠኛ ሽበሽ አለማየሁ በልምምዳችን ምንም ስህተት ባለመኖሩ እና ከዚያ በፊት ሢሰራበት ከነበረው መንገድ ወጣ ያለ ነገር በማየቱ “ጎበዝ” ብሎ ምሳ ጋበዘኝ:: ማታ ነው ለሙዚቃ ግብዣ ዝግጅቱ የምንገባው::  ጋዜጠኛ ዜና ታደሰ  ይባላል የዝግጅት ኃላፊው::  የዛን ቀን ፕሮግራሙን የሚመራው እሱ ነው::  እንዳይነቃ ካሴቶቹን  ደብቄያቸዋለሁ:: በሪል ቴፑ ፕሮግራሙ እንደሚሄድ ነው የሚያውቀው::ሌላ ጊዜ በሪል ቴፑ ተቀድቶ ካለቀ በኋላ ሺበሺ ወደ ቤቱ ይሄዳል፤ የዛን ቀን ሺበሺ ቤቱ ባለመሄዱ ምን እየሆነ ነው? የሚል ጥርጣሬ ጋዜጠኛ ዜና ታደሰ አድሮበታል:: “ለምን ወደ ቤትህ አትሄድም?” ይለዋል::ሺበሺም “አይ የምሄድበት ስለሌለኝ ልቆይ ብየ ነው” አለው::

ሰዓቱ ሲደርስ ካሴት ማውጣት ስጀምር ፕሮግራም አስተባባሪው ደነገጠ: :“ለምንድን ነው ካሴት የበዛው”? አለ:: “አይ ዛሬ ቀጥታ እንሞክር ብለን ነው” አልኩት:: ጋዜጠኛ ዜና ታደሰ ላብ በላብ ሆነ፤ ችግር ይገጥማል የሚል ፍርሃት አደረበት:: ነገር ግን ያለ ምንም ችግር የመጀመሪያውን ሙዚቃ ላክነው:: ትዝ ይለኛል የሻምበል በላይነህ ዘፈን ነበር:: እሱ በድንጋጤ ላብ በላብ ሆኖ እኔ በደስታ ስሜት ጭፈራውን አቀለጥኩት፡፡

ከዛ ሙዚቃው አልቆ ማይክ ስሰጠው “እንግዲህ በዚህ ዘፈን ስንቶቻችሁ እንደተደሰታችሁ ባላውቅም ከፊት ለፊቴ ቴክኒሻናችን በለጠ ወንዴ እስክስታውን እያስነካው ነበር” ብሎ ወደሚቀጥለው ሙዚቃ ምርጫ ማስተዋወቅ ገባ:: ያለምንም ክፍተት ያልምንም ችግር የዕለቱን የሙዚቃ ምርጫ ዝግጅት ጨርሰን ወጣን፡፡

 

በክር ካሴት የፈለከውን ሙዚቃ ለይቶ ለማጫወት ይከብዳል እና እንዴት ነበር መለየት የሚችሉት?

በመጀመሪያ የምትለየው ሀ እና ለ ጎኑን ነው:: የምትፈልገውን የዘፈን ዓይነት ታጫውተውና ልክ ሊጀምር ሲል መልሰህ በፕላስተር ምልክት አደርግበታለሁ:: ካሴቶቹ ላይም የሚሄዱበትን ተራ በቅደም ተከተል ቁጥር እጽፍባቸዋለሁ:: በቃ ይሄው ነው ሌላ የተለየ ዘዴ የለውም፡፡

 

ከአለቆች እውቅና ውጪ ቀጥታ የሙዚቃ ምርጫ ዝግጅትን በማስላለፍህ ቅጣት አልገጠመህም?

ያኔ ጉድ ሞርኒንግ ሚቲንግ የምንለው ነበር አሁን ድህረ ግምገማ ነው መሰል የምትሉት፤ እዛ ላይ አቶ ታቦር እና አቶ ጀማልም (አሁነ ዶክተር) ነበሩ፤ “ቴክኒሻኑ እስክስታ ይመታል ማለት ቀልድ ነው የሚመስለው” የሚል ሀሳብ በአቶ ጀማል ተሰነዘረ፤ በወቅቱ ይህን አይነት ነገር የተለመደ ስላልነበር እንደሆነ ይሰማኛል:: ስለሆነም የፕሮግራም አስተባባሪው ላይቭ ነው የሄደው በዛ ምክንያት የደስታ ስሜት ስለነበረ ነው ተብሎ ተመለሰ:: አቶ ጀማልም ደስ አለው:: ቀጥታ የዘፈን ምርጫውን በማስኬዴ ምንም የገጠመኝ ነገር የለም:: ዋናው ነገር ችግር እንዳይገጥም መዘጋጀት፣ ሲገጥምም የምትወጣበትን መንገድ በቶሎ መፈለግ፣ እዲሁም እርግጠኛ ያልሆንክበት ነገር ላይ ደግሞ ዘለህ አለመግባት ከችግርም ከውድቀትም ያድንሃል ብየ ነው የማስበው:: በእርግጥ ስህተት አይገጥምም ማለት አይቻልም፣ ሰው ካልተሳሰተ አይማርምና፡፡

… ይቀጥላል!

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here