ለሰላም ጥሪዉ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠዉ ይገባል!

0
159

የአማራ ክልል ግጭት የፈጠረው ቀውስ ሰባዊ፣ ቁሳዊ፣ ማህበራዊ… ኪሳራ አድርሷል።  ተማሪዎች  ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል፣ ሕሙማን   ታክመው ለመዳን እና መድኃኒት ለማግኘት     አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮባቸዋል…  ቀውሱ በየትኛውም የልማት መስክ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከባድ ነው።

በክልሉ የራቀውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ  በጋራ መቆምን በእጅጉ ይሻል። ቀውሱ በአንድ ፓርቲ፣ በአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም፣ በተወሰኑ ቡድኖች አማካኝነት ብቻ አይፈታም። ችግሩ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የሚሳተፉ አካላትም ሊበዙ ይገባል።

በጫካ ያሉ ተፋላሚዎች፣ ሕዝቡ፣ በተለያዩ የሙያ መስክ  ያሉ ወገኖች፣ ሁሉም አካላት ለሰላም ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ለንግግር እና ድርድር መዘጋጀትን ግድ ይላል።  መነጋገር እና መደራደር የጠብ መንጃ አፈ ሙዝን ከድኖ  ወደ ሐሳባዊ ጠረጴዛ ለመሄድ  አስቻይ  ሁኔታን ይፈጥራል።

በሐሳብ መሟገት፣ መረታታት፣ መስማማት ይቻላል። አሸናፊ  የሆነው  ሐሳብ ገዢ ይሆናል። ጠንካራ ሐሳብ ለጠንካራ ተቋማት ግንባታም መሰረቱን ይጥላል። ተቋማት ሲጠነክሩ ደግሞ ፍትሕ ይሰፍናል፣ የሕግ የበላይነትም ይረጋገጣል። የሕግ የበላይነት በተረጋጠጠበት ሀገር ውስጥ ተኩስ አይኖርም፣ መፈራረጁ እና መቧደኑም ይቀንሳል። ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል።  ንግግር እና ድርድር ሁሉን አሸናፊ የሚያደርጉ የፖለቲካው ዓለም ቁልፍ   ጉዳዮች ናቸው።

ሀቀኛ ውይይት፣ ንግግር፣ እና ድርድር ሲኖር ሁሉም ይደመጣል፣ሁሉም ይስማማል። ጠርዝ ከመቆም ወደ መሃሉ መምጣት ይገባል። በመሆኑም  ሁሉም አካል ለሰላማዊ ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት  ሕዝብን እና ሀገርን ከውድመት ሊታደግ ይገባል።

ግጭቱ አብሮን በዋለ እና  ባደረ ቁጥር ችግሮች እየተወሳሰቡ፣ ደም መፋሰሱ እየጨመረ እና  የንፁሃን ሕይዎትም ወደ አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። በመሆኑም ለሕዝብ፣ ለሀገር እና ለሰባዊነት ሲባል ለሰላም ጥሪው ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።  ለሰላማዊ ጥሪው አወንታዊ ምላሽ መስጠት የሕዝብን ድምፅ ማክበር እንዲሁም የነፍስ አድን ተግባርም ነው።

ሀገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት ለሰላም ጥሪው ፈጣን ምላሽ ለማግኘት ሌሎች ሀገራት ችግሮቻቸውን የፈቱበትን መንገድ በመከተል    ዛሬም ነገም ሕዝብን በማወያየት፣ ለተፋላሚ ወገኖች ያላሰለሰ ጥሪ በማድረግ  የጠፋውን ሰላም ለመመለስ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡  ሕዝብም እንደ ሕዝብ ለቀረበው የሰላም ጥሪ ተባባሪ እና አመቻች በመሆን አይተኬ ሚናውን ሊወጣ ይገባል፡፡ በጫካ ያሉ ኃይሎችም ተኩስ የችግር መፍቻ ስለማይሆን የህዝብን ሰቆቃ ለመቀነስ ወደ ንግግር መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here