በምድራችን ከሚከናወኑ ዓለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ዝግጅቶች መካከል የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ቀዳሚ ነው:: የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከ200 በላይ ሀገራት የሚሳተፉበት የዓለም ቀዳሚ የስፖርት ሁነት ተደርጎም ይወሰዳል:: ይህ የስፖርት ውድድር ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግሪክ መጀመሩን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ:: በወቅቱም ውድድሩ በየአራት ዓመቱ ይደረግ የነበረ ሲሆን ተሳታፊ ሀገራት ባህል እና እሴቶቻቸውን ያስተዋውቁበታል::
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጨዋታዎች በዘመናዊ መልክ እንደገና መደረግ ጀምረዋል:: የኦሎምፒክ መሰረት የሆኑትን አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገትን ማሳደግ፣ የተሻለ ሰላም የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት የመግባባት እና የአብሮነት መንፈስን ማሳደግ፣ የኦሎምፒክ ሀሳቦችን ከመላው ዓለም ጋር ማስተሳሰር እና የበጎ ፈቃደኝነት ስሜት መፍጠር የኦሎምፒክ ጽንሰ ሀሳቦች ናቸው:: አርማው ወይም ምልክቱም ይህን ያስረዳል:: አምስቱ እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩት የኦሎምፒክ ቀለበቶች አምስቱን አህጉር እንደሚገልጹ የኦሎምፒክ ድረገጽ መረጃ ያስነብባል::
ዘመናዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በግሪክ አቴንስ በ1896 እ.አ.አ እንደተጀመረ በታሪክ ተመዝግቧል:: በመጀመሪያው ኦሎምፒያድ 241 ስፖርተኞች ከ14 ሀገራት ተሳትፈዋል:: ሁለተኛው ኦሎምፒያድ ደግሞ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ መደረጉን ታሪክ ያወሳል:: በ1924 እ.አ.አ ፓሪስ ድጋሚ ኦሎምፒኩን አስተናግዳለች፡፡ ከመቶ ዓመታት በኋላ ዘንድሮም 33ኛው ኦሎምፒያድ በፓሪስ ከተማ ከሀምሌ 19 እስክ ነሐሴ አምስት ይደረጋል::
በዚህ የስፖርት መድረክ ከ206 ሀገራት የተውጣጡ አስር ሺህ 500 አትሌቶች በ329 የስፖርት ዓይነቶች የሚፎካከሩ ይሆናል:: የፓራለምፒክስ ውድድር ደግሞ ከነሐሴ 20 ጀምሮ ለተከታታይ አስር ቀናት የሚከናወን ይሆናል:: በፓራለምፒክስ ዘርፍም ከ184 ሀገራት የተውጣጡ አራት ሺህ 400 አትሌቶች በ549 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ:: በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ከ15 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ፈረንሳይን እንደሚጎበኙ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል::
ዋና ዋናዎች የአትሌቲክስ ውድድሮች በሰሜናዊው የፓሪስ ዳርቻ በሚገኝው ስታዲዮ ፍራንስ ይከናወናሉ:: የፓሪሱ ኦሎምፒክ በ15 የመወዳደሪያ ቦታዎች የሚደረግ ሲሆን ለፓራለምፒክስ ውድድር ደግሞ 11 የውድድር ቦታዎች ተዘጋጅቷል:: የፓራለምፒክ ውድድሮችም በሰሜናዊው የፓሪስ ክፍል እና ከፈረንሳይ ድሀ ከሚባሉ ክፍሎች አንዱ በሆነው ሴአኒ ሴንት ዴንስ ግዛት ይደረጋል:: የብስክሌት እና የማራቶን ውድድር የሚደረግባቸው ቦታዎች እና መንገዶች የትራፊክ እንቅስቃሴ ገደብ ይደረግባቸዋል ተብሏል::
በዓለም ላይ ከ36 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በስደተኞች የመጠሊያ ጣቢያ እንደሚኖር የተባበሩት መንግስታትን ድርጅትን ጠቅሶ ዘ ኢንድፔንደንት አመልክቷል:: በስደተኞች ጣቢያ የሚኖሩ በርካታ ስፖርተኞች ስለመኖራቸውም ተዘግቧል:: እነዚህ ስፖርተኞች ከ2016 እ.አ.አ ጀምሮ በየአራት ዓመቱ በሚደረገው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ::
በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በአስተናጋጇ ሀገር ፈረንሳይ በሚገኝው የስደተኞች ጣቢያ 36 ስፖርተኞች በውድድሩ ይካፈላሉ:: በአጠቃላይ ግን ከ11 የተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የስደተኞች ጣቢያ የተውጣጡ ስፖርተኞች በኦሎምፒኩ እንደሚካፈሉ መረጃዎች ወጥተዋል:: ለአብነት 15 ስፖርተኞች ከኢራን እና አምስት ስፖርተኞች ከሶሪያ ወደ ፓሪስ ለመብረር ተዘጋጅተዋል::
44 በመቶ የሚሆነው የፓሪስ ከተማ ነዋሪ ግን ከተማቸው ኦሎምፒኩን ማስተናገዷ ምቾት አልሰጠውም:: “መጥፎ ዕድልም” ብሎታል:: በርካቶችም ከመክፈቻው ቀን ጀምሮ ከተማቸውን ለቀው ለመሰደድ ወስነዋል:: ፓሪሳውያን እንቅስቃሴያችን ተገድቧል፤ ነፃነታችንን ተነፍገናል በማለት ለቢቢሲ ስፖርት ቅሬታቸውን አቅርበዋል::
የፈረንሳይ መንግስት ውድድሩ ያለምንም የፀጥታ እንከን በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከ40 ሺህ በላይ የፖሊስ እና የፀጥታ ሰዎችን አዘጋጅቷል:: ከእነዚህ መካከል ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት ከወዳጅ ሀገራት መምጣታቸውን የኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር አስታውቋል:: ከ30 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ደግሞ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ አገልግሎት እንዲያቀላጥፉ ተመድበዋል::
የኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር ምንም እንኳ ለደህንነታቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ እና የፖሊስ ሠራዊት አሰማራለሁ ቢልም፤ አሁን ከስጋት ግን ነፃ አይደለንም ማለቱ እያነጋገረ ነው:: የኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር የድሮን ጥቃት ስጋት አለብኝ ብሏል:: ታዲያ ይህ ስጋትም የተጋባዥ እንግዶችን ቁጥር እንዲቀንሱ አስገድዷቸዋል::
መጀመሪያ ላይ 600 ሺህ ሰዎች የተጋበዙ ቢሆንም በኋላ ላይ በግማሽ ዝቅ እንዲል ተወስኗል:: በውድድሩ ወቅት የሩሲያን ሰንድቅ አላማ መያዝ እንደማይችሉም ተነግረዋል:: ፓሪስ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ስታስተናግድ የዘንድሮው ለሦስተኛ ጊዜ ነው:: ይህም ከለንደን ቀጥሎ ኦሎምፒክን ሦስት ጊዜ ያስተናገደች ከተማ ሆናለች::
የ2024ቱን የፓሪስ ኦሎምፒክ እና ፓራለምፒክ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት አራት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዩሮ ገንዘብ በላይ ወጪ ተደርጓል:: 96 በመቶ የሚሆነው ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ከትኬት ሽያጭ፣ ከአጋር ድርጅቶች እና ከመሳሰሉት የተገኝ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል:: እስካሁን ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ትኬት በላይ መሸጡን መረጃዎች አስነብበዋል:: በቴሌቭዥን መስኮት ደግሞ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል::
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ምክንያት ስፖርተኞች ወደ ፓሪስ አለማቅናታቸው ተዘግቧል:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባሳደረው ጫና ምክንያት፤ ሩሲያ ከፓሪሱ ኦሎምፒክ እንድትገለል ሆኗል:: የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌ ላቭሮቭ ግን እገዳው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል::
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ እስራኤል ከሀማስ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ምክንያት ከፓሪስ ኦሎምፒክ አለመታገዷን ጠቅሰው የእኛም ጦርነት ፍትሐዊ ነውና መታገዳችን ኢፍትሐዊ ነው ብለዋል:: በተመሳሳይ ለሩሲያ ድጋፍ የምታደርገው ቤላሩስም ከውድድር መድረኩ ታግዳለች:: በግላቸው የሚወዳድሩት ሩሲያውያን አትሌቶች ግን ወደ ፓሪስ ማቅናታቸው ተሰምቷል::
የዘንድሮውን ኦሎምፒክ ከባለፉት መድረኮች ለየት የሚያደርገው የወንድ እና የሴት ተፎካካሪ ስፖርተኞች ቁጥር እኩል መሆኑ ጭምር ነው:: በፓሪሱ ኦሎምፒያድ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የሚጠበቁ ይሆናል:: በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን፣ በዐስር እና አምስት ሺህ ርቀቶች በሁለቱም ጾታዎች ይጠበቃሉ:: በተጨማሪም አሜሪካዊቷ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ ሲሞን ባይልስ፣ የመም እና የሜዳ ተግባራት ንግስቷ ጃማይካዊቷ ሽሊ አና ፍሪዝር፣ አሜሪካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጯ ሽካሪ ሪቻርድሰን፣ የጦር ውርወራ ንጉሱ ኔራጅ ቾፕራ እና ታምረኛዋ የስኬት ቦርዲንግ ባለተሰጥኦዋ ብራዚላዊት ራይሳ ሌል በፓሪስ ስማይ ስር ይደምቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ተጠቃሽ ናቸው::
እንግሊዝ፣ ግሪክ ስዊዘርላንድ እና ፈረንሳይ በኦሎምፒክ መድረክ 29 ጊዜ በመሳተፍ ቀዳሚ ሀገራት ናቸው:: ይሁን እንጂ አሜሪካ ሁለት ሺህ 629 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የደረጃ ሰንጠረዡን ትመራለች:: ከእነዚህ ሜዳሊያዎች መካከል አንድ ሺህ 61ዱ የወርቅ ሜዳሊያ ነው:: 830ው የብር ሜዳሊያ ሲሆን 730 የነሐስ ሜዳሊያ አላት::
በዘንድሮው ኦሎምፒክ የማትሳትውፈው ሩሲያ አንድ ሺህ ዐስር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአሜሪካ በመቀጥል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች:: ሩሲያ 395 የወርቅ፣ 319 የብር እና 296 የነሐስ ሜዳሊያዎችን እስካሁን መሰብሰብ ችላለች:: እንግሊዝ እና ቻይና ደግሞ በቅደም ተከተል ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል:: ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ 58 ሜዳሊያዎችን እስካሁን ስብስባለች:: በአትሌቲክስ ስፖርት የምትታወቀው ሀገራችን በፓሪስ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ልዑኳን ልካለች::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም