የጣና ገዳማት

0
318

ከባህር ዳር ከተማ የጣና ወደብ ተነስተናል፤ ከጧቱ 1፡00 ይላል ሰዓታችን። ታላቋ ጣና ነሽ መርከብ ለጉዞ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋ ለመጓዝ ሞተሯን ታሟሙቃለች።

ጣና ሐይቅ በማለዳዋ የፀሀይ ብርሀን ፈክቶ ያፈካል፣ ፀጥ ረጋ ብሎ ተኝቷል። 3,600 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት በኢትዮጵያ አንደኛ በሆነው የጣና ሀይቅ ላይ ስአት እስከፈቀደ ድረስ በምናብ ይዤያችሁ ልጓዝ ነው አብራችሁኝ ሁኑ።

ጣናን አይንን ብቻ አይደለም ጆሮንም ያስደምማል። ከባህር ዳር ወደብ ጀምሮ ጣና ዳር ለዳር በእግር እየተንሸራሸሩ የሚዝናኑበት የእግር መንገድ ዙሪያውን ተጠምጥሞበታል። የጣናን ውበት እንደጨመረው የበፊቱን ሁኔታ የሚያውቅ ሰው በቀላሉ ይረዳዋል። ጣና እንደ ገጠር ሙሽራ ሽፍንፍኑን ገላልጦ ፍንትው ብሏል። መንፈስን ቀለል ያደርጋል፣ ለማንኛውም ጉዞ ልንጀምር ነው። የምናብ ጀልባችሁን እናንተም አስነሱና አብረን እንጓዝ።

ፈጣኗ ጀልባችን የዋዛ አይደለችም የሐይቁን ዉሀ እየመተረችው ሸመጠጥን። ፀጥ ረጭታውን በጠበጥነው መሰል መገላበጥ ጀመረ። ነፋስ ከውዲህና ወዲህ እየነፈሰ ጉዟችንን ቀጠልን። አይ የኔ ነገር ከአሁኑ በጣና ተፈጥሮ ውበት ሰጥሜ የጉዟችንን አላማ ሳልነግራችሁ ከመጀመሪያው መዳረሻዎችን ልንደርስ ነው፤ ሰባት ኪሎ ሜትር አለን ገና፤ ወደዚያው እየወሰድኳችሁ ነው። በጣና ውስጥ  ካሉ ወደ 20 የሚሁኑ ገዳማትን ጊዜ የፈቀደልንን ያህል እያስጎበኘኋችሁ እንውላለን።

በጣና ዙሪያ ደሴቶች እና ታሪካዊ ገዳማት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ብዙም ያልተራራቁ መንትያ ደሴቶች ከቅርብ ርቀት ይታዩኛል፤ ከሚወስድብን 45 ደቂቃ ያህል አርባውን ጨርሰን ደሴቶቹ ጋ ለመድረስ የአምስት ደቂቃ ብቻ ቀርቶናል። ደሴቶቹ እየገዘፉ እኛ እየደቀቅን ደረስንባቸው። ክብራን ገብርኤል እና እንጦስ የተባሉ ሁለት ጥንታዊ ገዳማት አሉ። አይንን የሚያፈዝዝ የተፈጥሮ አቀማመጥ ላይ፣ በደን በተሸፈነ ኮረብታማ ስፍራ ለዘመናት ተጎራብተው የኖሩ ውብ ታሪካዊ ደሴቶች።

ክብራን ገብርኤል የወንድ መናንያን፣ እንጦስ  ደግሞ የሴት መናንያን መኖሪያ እንደነበር ይነገራል። እንጦስ ገዳም በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት መናንያኑ እየለቀቁ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ስለሄዱ ለረጅም ጊዜ ገዳሙ ባዶ ሆኖ ቆይቷል ።

በዐፄ አምደ ፂዮን ዘመነ መንግሥት እንደተመሰረተ የሚነገርለት ክብራን ገብርኤል ጥንታዊ የእደ ጥበብ ውጤቶችን የሚያሳዩ አሻራዎች ይታዩበታል። ከአምደ ፅዮን በኋላ በዳግማዊ ዳዊት እንዲሁም በአዲያም ሰገድ እያሱ በድጋሜ እንደተገነባ ይነገራል። በዚህ ጥንታዊ ገዳም የነገሥታት ስጦታዎች፣ እና ሌሎች ቅርሶችን ይዞ ይገኛል። በዚህ ገዳም የሚታየው ሁሉ መንፈስን ያድሳል። ሁለቱን መንትያ ውብ ደሴቶች ትተን ጉዞ ወደ ፊት እንቀጥል።

የመጣነውን ያህል ሰባት ኪሎ ሜትሮች ከፊታችን ይጠብቀናል። ጣናን ከምእራብ ወደ ምስራቅ ገፍቶ የያዘ ባህረ ገብ መሬት መታየት ጀመረ። እየቀረብን ስንሄድ ከቅርብ ርቀት የተዘረጋው መሬት ሲታይ ክንፎቹን ዘርግቶ የተቀመጠ አሞራ ይመስል ነበር። የዘጌ ባህረ ገብ ወይም ፔንሱላ። ጀልባችንን ወደቡ ላይ አስረን ወረድን እና የዘጌን መሬት ረገጥን።

ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነው ምድር የጣና ፈርጥ ዘጌ ከባህር ዳር 15 ኪሎ ሜትር የባህር ላይ ርቀት አለው።  በመኪና ደግሞ 23 ኪሎ ሜትር  ሲርቅ እስከ ሁለት ሰአት ይወስዳል። በውስጡ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችን ይዟል። ዘጌ ሲነሳ አቡነ በትረ ማሪያም አብረው ይነሳሉ። እንደቆረቆሯት የሚነገርላቸው አባ በትረ ማሪያም ዘጌ ውስጥ ምንም ጅራፍ እንዳይጮህ በማዘዛቸው በዘጌ ምድር በበሬ አይታረስም። በመሆኑም የዘጌ ኗሪዎች ተፈጥሮ የለገሰችውን ፀጋ እየተጠቀሙ ሕይወታቸውን እንደሚመሩ አባቶች አስረዱን።

ከወደቡ ወደ ውስጥ የሚያስገባውን በቀጭን የእግር መንገድ ተያያዝነው። ግራና ቀኝ በአረንጓዴ የተከበበችውን መንገድ ይዘን ቀድመን ወደ ምናገኘው ገዳም ወደ አስራ አምስት ደቂቃ መጓዝ አለብን፣ በእግር። በነገራችን ላይ በዘጌ ባህረ ገብ ውስጥ ሰባት ገዳማት እንደሚገኙ እግረ መንገዳችንን እንጠቁማችሁ። መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ፣ አቡነ በትረ ማሪያም፣ ኡራ ኪዳነ ምህረት፣ አዙዋ ማሪያም፣ ደብረ ሥላሴ፣ ኢጋንዳ ተክለ ሀይማኖት እና ፉሬ ማሪያም የተባሉ ጥንታዊ ገዳማት ይጠቀሳሉ። ከኢጋንዳ ተክለ ሀይማኖት እና ፉሬ ማሪያም በስተቀር ሁሉም አቢያተ ክርስቲያናት መጠነኛ ጀልባዎችን የሚያስጠጉ ወደቦች አሏቸው።

አዙዋ ማሪያም ገዳም ከኡራ ቀጥሎ ከአስራ አምስት እስከ ሰላሳ ደቂቃዎች የእግር ጉዞ በኋላ ትገኛለች። በ14ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ አምደ ፅዮን እንደተገነባች የሚነገርላት አዙዋ ማሪያም እንደ ኡራን ሁሉ በግድግዳ ስእሎቿ ትታወቃለች። አንዳንዶቹ ስእሎች ዙሪያቸውን በብር ጉብጉባት የተሰሩ ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ነገስታት የተበረከቱ ከስድስት መቶ አመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶች የተከማቹበትን ሙዚየም መጎብኘት ይችላሉ። በተለያየ ጊዜ ገዳሟን ለመጎብኘት ከመጡ ነገስታት መካከል ንግሥት ዘውዲቱ፣ ዐፄ ልብነ ድንግል፣ እቴጌ ምንትዋብ እና  ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት የሚጠቀሱ ሲሆን የወርቅ መስቀል፣ ዘውዶችን፣ ካባዎችን እና ሌሎችን ቅርሶች ማየት ይቻላል። በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድ እንደፃፈው የሚነገርለትን ከ1,500 በላይ ገፆች ያሉትን የዜማ የብራና መፅሀፍ ይገኛል።

ከዘጌ ገዳማት በእድሜ አንጋፋ ከሚባሉት አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ገዳም መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ ነው። በ13ኛው ክፍለ ዘመን በአቡነ በትረ ማሪያም እንደተመሰረተ ይነገራል። በውስጡ የተለያዩ ቅርሶችን ይዟል።

ከመሀል ዘጌ ጊዮርጊስ አጠገብ ደግሞ የአቡነ በትረ ማሪያም ቤተክርስቲያንን እናገኛለን። ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ የቆየ አንዱ ጥንታዊ ገዳም ነው። አቡነ በትረ ማሪያም ከሞቱ በኋላ ተከታያቸው አቡነ በርተሎሚዎስ በመቃብራቸው ላይ ለመታሰቢያ ያስገነቡት ገዳም እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ። የጥንቱን ዘመን ቅርፃ ቅርፅ ጥበብ የእንጨት ቅርፃ ቅርፆች በበሩ እና በመስኮቶቹ ላይ ይታያሉ። ባማላይ ስእሎችም ግድግዳዎቹ ያሸበረቁ ገዳም ነው።

ከዘጌ ሳንወጣ ጣናን ከሁሉም አቅጣጫ ማየት የሚያስችል ተራራ ይገኛል። በዚህ ተራራ አናት ላይ ታዲያ ይጋንዳ ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን ተሰርቶበታል። በዐፄ አድያም ሰገድ እያሱ በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ የሚነገርለት አንዱ ጥንታዊ ገዳም ነው። ዘጌ ከሚገኙት ገዳማት የበርካታ ቅርሶች ክምችት ያለበት ነው።

ደቅ ደሴት ጣና ውስጥ ከሚገኙ ደሴቶች ትልቁ ነው። ከባህርዳር ወደ ስሜን አቅጣጫ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በጀልባ ሦስት ሰዓታትን ሊወስድ ይችላል። ከደሴቱ በቅርብ ርቀት ላይ ያለውን ዳጋ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሰባት ገዳማትን ስለያዘ የሰባት ደብር ሀገር እየተባለ ይጠራል። እነርሱም ናርጋ ስላሴ፣ ቅድስት አርሴማ፣ ለታ ማሪያም፣ ዝባድ እየሱስ፣ ለጋ ዮሐንስ እና ጋዳና ጊዮርጊስ ናቸው። ቀደም ሲል ደሴቱ ለመናኒያን ብቻ የተለየ ሆኖ የቆየ ቢሆንም ቀስ በቀስ አለማውያን ሰዎች እየገቡ ቁጥራቸው እየበረከተ የገዳሙ ኗሪ መሆን እንደቻሉ ታሪኩ ያስረዳል። ደቅ ደሴትን ከሌሎች የጣና ደሴቶች የሚለየው የቀድሞ ነገሥታት ተቀናቃኞቻቸውን በግዞት ገለል የሚያደርጉበት ስፍራ መሆኑ ነው።

ናርጋ ሥላሴ ገዳም በደቅ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ሲሆን በክረምት ወራት የሀይቁ ዉሃ በሚጨምርበት ጊዜ ራሱን የቻለ ደሴት ይሆናል፤ በበጋ ወቅት ውሃው ሲቀንስ ደግሞ የደቅ ደሴት ምእራባዊ አካል በመሆን ይቀላቀላል። ገዳሙን እቴጌ ምንትዋብ እንዳሰሩት የሚነገር ሲሆን ከድንጋይ፣ ከኖራ፣ እና ክብ ቅርፅ ይዞ ከእንጨት የተሰራ ነው። ቁመታቸው አራት ሜትር ስፋታቸው ሁለት ሜትር የሆኑ ግዙፍ በሮች አሉት።

 

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here