‘እስኪዞፍሪኒያ’ የሥነ አዕምሮ እክል ዓይናችሁን ክፈቱ!

0
185

አካቢያችሁንም በውል አስተውሉ፤ ትናንት በትጋት ትምህርታቸውን ተከታትለው  የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀው ወገን እና ሀገር ለትልቅ ቁም ነገር  ሲጠብቃቸው  የነበሩ ወጣቶች በአዕምሮ የጤና እክል በጅምር ተጠልፈው የቀሩ  አልተመለከታችሁም? መልሱን ለእናንተው ትቸዋለሁ፤ እኔ ግን ብዙ አይቻለሁ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታችን ከክፍል ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ በትምህርት ቤቱ ደረጃ ይዘው ሲጨበጨብላቸው የነበሩ ጎበዝ  ተማሪዎች ነበሩ::  ዛሬ  ታዲያ  ከትልቁ የክብር መዳረሻቸው ተገተው በየጎዳናው ተጎሳቁለው እና ጨርቃቸውን ጥለው  በጫት እና ሲጋራ ታጅበው ይውላሉ፤ ያድራሉ፡፡  ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በየቤቱ እና በየጓዳው በሰንሰለት እና በገመድ ታስረው  “እብድ፣ ቀውስ” የሚል ያልተገባ  ክፉ ስያሜ ተለጥፎባቸው የመከራ ኑሮ ይገፋሉ፡፡

ለማሳያ ጎበዝ የነበሩ ተማሪዎችን አነሳሁ እንጅ ዛሬ እኮ በርካታ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር ገጥሟቸው በየጎዳና  ይታያሉ፤ ህብረተሰቡም ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ የሚያደርገው እገዛ የለውም፡፡ አንዳንድ ቤተሰብ ደግሞ  በገመድ ወይም በሰንሰለት አስሮ በቤት  ያኖራቸዋል ወይም ወደ ባህላዊ ህክምና ይዟቸው ይዞራል::

የሥነ አዕምሮ እክል ገፈቱ ብዙ ነው፡፡ ከግለሰብም፣ ከማህበረሰብም አልፎ ሀገር ላይ ከፍተኛ ዳፋ ያሳርፋል::

በርከት ያሉ የሥነ አዕምሮ ጤና እክሎች ቢኖሩም አደገኛው “እስኪዞፍሪኒያ” የተባለው በሀገራችን ሰፋ ብሎ ይታያል:: በባሕር ዳር እና አካባቢዋ  ወደ ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚመጡ የሥነ አዕምሮ ታካሚዎች መካከል 25 በመቶው  አሳሳቢው አስኪዞፍሬኒያ  የተባለው የሥነ አዕምሮ ህመም እንዳለባቸውም በሆስፒታሉ የሥነ አዕምሮ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ማቴዎስ ማሳኔ ነግረውናል::

“አዕምሮ የሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ሚዛን ማስጠበቂያ እና መቆጣጠሪያ ትልቁ ክፍል ነው:: አዕምሮ ሲታወክ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ይናጋሉ::  የአዕምሮን  ጤና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉም ኃላፊው ገልፀዋል::

በዓለም አቀፍ ጥናቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ቡታጅራ አካባቢ በተሠራ ጥናት ከአንድ በመቶ በላይ እስኪዞፍሪኒያ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዳለ ያመለክታል የሚሉን ዶክተር ማቴዎስ ይሄ ማለት ከ120 ሚሊየን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ ችግሩ አለበት ማለት ነው::

በባህርዳር ፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስነ አዕምሮ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ማቴዎስ  ማሳኔ አዕምሮ ሥራው በአግባቡ ማሰብ፣ ስሜትን በልክ መምራት እና ባህሪን ማስተዳደር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን በትክክል መምራት ሲቸግር ግን የአዕምር እክል አለ ብሎ መናገር እንደሚቻል ያስረዳሉ::

በርካታ የሥነ አዕምሮ ህመም መገለጫዎች  ቢኖሩም አሁን ላይ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ከሚታከሙት የሥነ አዕምሮ ታካሚዎች መካከል ከ25 በመቶ  እስኪዞፍሪኒያ እንደሆነ መረጋገጡን የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ዶክተር ማቴዎስ ጠቁመዋል::  ይህ ማለት ደግሞ እስኪዞፍሪኒያ የተባለው የስነ አዕምሮ እክል ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ጉልህ ማሳያ ነው::

እስኪዞፍሪኒያ የተባለው የሥነ አዕምሮ እክል መንስዔው ይሄ ነው ተብሎ መናገር የሚያስቸግር  ቢሆንም በዘር እና ከአጋላጭ ሁኔታዎች ጋር ተደማምሮ የሚከሰት እንደሆነም ይገልፃሉ:: ለአብነት  በወሊድ (በምጥ) ጊዜ የሚፈጠሩ አደጋዎች ፣ አፈጣጠር ላይ ጭንቅላት ውስጥ ያሉ ነርቮች ሲዛቡ፣ እንዲሁም ጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ ከሁኔታዎች ጋር ተደማምረው ለችግሩ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ዶክተሩ አረጋግጠዋል::

የእስኪዞፍሪኒያ ምልክቶቹ ያለው እውነታ  ተገልብጦ መታየት፣ የሌለ ነገር መታየት፣ ሰው ሳይጠራቸው አቤት ማለት፣ ሰው ሳያወራቸው ያወራቸው መምሰል፣ የሌለውን ነገር ማየት፣ የሌለ ድምፅ ለእነሱ ብቻ መሰማት፣ የተለየ እምነት መያዝ፣ የሚጠቅማቸውን ሰዎች እንደሚጎዷቸው ማሰብ፣ አብዝቶ መጠራጠር፣ ሰዎች ይከታተሉኛል፣ ካሜራ ገጥመውብኛል፣ በማለት የሚረዷቸውን ሰዎች በሌለ ነገር መክሰስ፣ መሸሽ፣ መለፍለፍ፣ ብቻን ወጥቶ መሄድ ፣ መፍራት፣  እየከፋ ሲሄድ ደግሞ  መገለል፣ ስሜት አልባ መሆን እና  አለማውራትም ሊከሰት እንደሚችል ዶክተር ማቴዎስ ያስረዳሉ::

እንደ የስነ አዕምሮ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ማቴዎስ አስተያየት እስኪዞፍሪኒያ በክትባት መልክ ቀድሞ መከላከል ባይቻልም አስቀድሞ የስነ አዕምሮ ሀኪሞችን በማማከር እና በሳይንስ የተረጋገጡ የስነልቦና ልምምዶችን (training) በመውሰድ ጤናማ የስነ አዕምሮ ሕይወትን መምራት ይቻላል::

ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግን እንደ ማንኛውም ህመም የሚታከም እንደሆነ ህብረተሰብ ተገንዝቦ ህክምናውን በሚገባ መከታተል እንዳለበት ዶክተሩ በአፅኖት ይመክራሉ::

ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግን  “በባዮሳይኮሶሻል” በሚባል ሞዴል ህክምናው ይሰጣል የሚሉን ዶክተሩ  ‘ባዮ’ ማለት መድኃኒቶችን በመስጠት ህክምና ማድረግን የሚገልፅ ሲሆን ‘ሳይኮ’ ስነልቦናዊ የንግግር እና የምክክር ህክምናን ያሳያል:: ‘ሶሻል’ የሚለው ደግሞ ከማህበረሰቡ የሚደረግ ድጋፍና ክትትልን የሚያሳይ ሲሆን  መንፈሳዊና ባህላዊ ህክምናዎችም የህመሙን መንስዔና ምክንያት ባገናዘበ መንገድ  ችግሩ የገጠማቸውን  ሰዎች ማገዝ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው::

በአጠቃላይ ግን ችግሩ የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ህክምና ማዕከል መጥተው በመታከም መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉ ዶክተር ማቴዎስ በአፅኖት ይገልፃሉ::

ከዚህ ባለፈም ዶክተር ማቴዎስ “ኩላሊቱ የታመመን ሰው ኩላሊቱ ታመመ፣ አይኑን የታመመውን ሰው አይኑ ታመመ፣ ከተባለ አዕምሮውን የታመመ ሰውም አዕምሮውን ታመመ እንጅ ቀውስ፣ እብድ እና መሰል ያልተገቡ ስያሜዎችን መስጠት ችግሩን ያባብሳልና ህብረተሰቡ ከዚህ ያልተገባ ስያሜ ሊቆጠብ ይገባል” ሲሉም ይመክራሉ::

ዶክተር ማቴዎስ በሥራ ላይ የገጠማቸውን ሲገልፁም “የስነ አዕምሮ ታካሚዎች ከድብደባ ብዛት ጆሮአቸው የማይሰማ፣ ከጠንካራ የሰንሰለት እስራት ብዛት የእጅና የእግር አጥንቶቻቸው የተሰበረ  እና ሌሎች ልብ የሚሰብሩ  መሰል ጉዳቶች ገጥመዋቸው እንደሚመጡ ይገልፃሉ:: ይህ ሁኔታም ችግሩን ያባብሳልና ህብረተሰቡም የስነ አዕምሮ ታካሚዎችን ተንከባክቦ ወደ ህክምና በማድረስ በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባው ዶክተሩ አሳስበዋል::

(ግርማ ሙሉጌታ)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here