ከገደብ ያለፈው የሙቀት መጠን

0
148

ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ሃገራት በፓሪስ የዓየር ንብረት ስምምነት ካስቀመጡት የሙቀት ጣሪያ የበለጠ መመዝገቡን ተከትሎ በየቀጠናው አስከፊ ሁነቶች መስተዋላቸውን ላይቭ ሳይንስ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

ካለፈው 2023 እ.አ.አ ሰኔ ወር ጀምሮ እስከ ያዝነው የ2024 ሀምሌ ወር የተመዘገበው የሙቀት መጠን አንድ ነጥብ 64 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ነው። ይህም በፓሪስ የዓየር ንብረት ስምምነት ከተቀመጠው ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንቲግሬድ የበለጠ መሆኑ አሳሳቢነቱን የጐላ አድርጐታል:: ይህም የኢንዱስትሪው አብዮት በዓለማችን ከመስፋፋቱ በፊት ከነበረው የበለጠ ነው፤ በእነዚያ ዘመናት ከብስባሽ የሚገኘው ነዳጅ ብቸኛ የኃይል ምንጭ እንደነበር  ልብ ይሏል::

የ “Copernicus climte change Service (c3s)” ዳይሬክተር ካርሎ ቦኦንቴም  በተከታታይ ባለፉት ወራት የተመዘገበው የሙቀት መጠን  አደገኛ  መሆኑን አስምረውበታል::

የሙቀት መጨመሩ በምስራቃዊ እና ፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ መስተዋሉን ተከትሎ በምስራቅና ማእከላዊ የምድር ወገብ ቀጠናዎች ከተቀመጠው አማካይ መብለጡም ነው የተሰመረበት::

ባለፉት 12 ወራት  የባህር  እና  የውቅያኖስ ውኃ መሞቁን ተከትሎ የአማካይ የሙቀት ጣሪያው   እንዲያልፍ እገዛ አድርጓል  ነው  ያሉት:: አሁን  ካለው የሙቀት መጠን የሚጨምር ከሆነ ሁነቱን ለመቀልበስ አዳጋች እንደሚሆንም ነው ያሳሰቡት:: ተመራማሪዎቹ አሁንም ሃገራት አቅማቸውን አሰባስበው በአንድነት የማያዳግም ተግባራዊ ውሳኔ ላይ መድረስ ግድ እንደሚላቸው ነው ያደማደሙት:: ይህ ካልሆነ ግን የውኃ ሙላት፣ ማእበል፣ የሰደድ እሳት የመሳሰሉ  አደጋዎች መብዛታቸው፣ እልቂቱ መበራከቱ አይቀሬ መሆኑን ነው ያስታወቁት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here