የባከኑ ቃላት

0
183

ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት የሆነኝ ልጄን ካንድ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የግል ማስተማሪያ ተቋም ሳስመዘግብ በሄድሁበት ጊዜ ያጋጠመኝ ነገር ነው:: መዝጋቢዋ ወጣት ስለትምህርቱ አስፈላጊነት በሰፊው ገለጸችልኝ:: ከሰፊው ገለጻዋ መዝዤ ያወጣሁት ቁም ነገር “ተማሪዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን ያለስህተት መናገርም ሆነ መጻፍ አለባቸው” የሚለው ነው::

በጣሙን የሚደገፍ ሀሳብ ቢሆንም “መምህሩስ?”  የሚል ጥያቄ አጫረብኝ:: ጥያቄው ደግሞ አንድ ነገር አስታወሰኝ:: እሷ ባትናገረውም በንግግርም ሆነ በጽሑፍ ወቅት እንግሊዝኛ ቋንቋን በትክክል አለመጠቀም ለትችት ይዳርጋል:: በተለይም ስህተት ሠሪው መምህር ከሆነና ስህተቱን በተማሪዎቹ ፊት ከሠራ ለተማሪዎቹ የሰላ  ትችት ሊጋለጥ እንደሚችል ጥርጥር የለውም::   ካንድ ዓመት በፊት ይመስለኛል፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ወደ መሥሪያ ቤታችን ይመጣሉ::

“እገሌ  የሚባለው  መምህር ያስተምራችኋል?”  ስል እንደ ቀልድ ጠየቅኋቸው::

አንደኛዋ ተማሪ ፈጠን ብላ፣ “ቲቸር እገሌማ ያስተምሩናል” አለችና በሳቅ ተንፈቀፈቀች::

በሁኔታዋ ተገርሜ “ምነው ሳቅሽ?” ስላት፣

“አይ ጋሼ እሳቸው ማለት ነው የሚገርም የእንግሊዝኛ ችሎታ ነው እኮ ያላቸው” አለችኝ:: ከዚያ እንደገና ትስቅ ጀመር፤ ሳቋን እስክትጨርስ ጠበቅኋት:: ስቃ ስቃ ስታበቃ “አንድ ጊዜ ማለት ነው ምን አሉን መሰለህ?”

“እሽ ምን አላችሁ?”

“ክላስ ነበረንና ማለት ነው ወደ ሁለተኛ ፎቅ ይዘውን ወጡ:: ከፎቁ እንደወጣን ቀድመውን ወደ መማሪያ ክላሳችን ሄዱ:: ወዲያውኑ ማለት ነው ተመለሱና ‘ስቱደንትስ ዚስ ክላስ ኢዝ ኦልረዲ ኦኩፓይድ ሌት አስ ድሮፕ ቱ ዘ ግራውንድ ክላስ’ አሉን ማለት ነው” አለችና ያን ሳቋን ለሦስተኛ ጊዜ ለቀቀችው:: ይሄኔ “አመድ በዱቄት ይስቃል” የሚለው ተረት ትዝ አለኝና ተረትሁላት::

“ምን ማለት ነው?” አለችኝ፤ ወደ ጓደኞቿ ዞራ እየተመለከተች:: ጓደኞቿ ‘እኛ የለንበትም፤ እንደጀመርሽው እዚያው ተወጭው’ በሚል ስሜት መልሰው ተመለከቷት:: እሷም ዓይኖቿን ከጓደኞቿ ወደ እኔ መልሳ ተመለከተችኝ፤ ‘በላ ለጠየቅሁህ ጥያቄ መልሷን ቁጭ አድርግ!’ የምትለኝ መሰለኝና፣ “ባንቺ እና በመምህሩ መካከል አጉል መናናቅ ነው የተፈጠረው” አልኋት:: አሁንም ንግግሬ የገባት አልመሰለኝም፤ ዝም ብላ ታየኝ ጀመር:: እናም ሀሳቤን አፍታታሁላት፤ “መምህሩ በንግግሩ መሀል እንግሊዝኛውን ባግባቡ አልተጠቀመበትም፤ አንቺም አማርኛውን ባዕድ ቃል በመጨመር እንዲሁም በመደረት ስህተት ሠርተሻል:: ስለዚህ ሊሳቅባችሁ የሚገባ በሁለታችሁም ነው” በማለት::

“ሊሳቅባችሁ የሚገባ ነው ያልከኝ ጋሼ?!… አማርኛ ደግሞ እንደፈለገን ብንጠቀምበት ምን ፕሮብሌም አለው?” ስትል ልትሞግተኝ ሞከረች::

“አማርኛም እንደ እንግሊዝኛዉ የራሱ ያጠቃቀም ሥርዓት አለው፤ ስለዚህ ለእንግሊዝኛው እንደምንጨነቀውና እንደምንጠነቀቀው ሁሉ ላማርኛ ቋንቋ አጠቃቀምም ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል:: እኛ ስህተት እየሠራን በሰው ብንስቅ ነገሩ ‘አመድ በዱቄት ይስቃል’ የሚለውን ተረት ከማሳሰብ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም” ስል ከስህተቷ ላርማት ሞከርሁ:: እሷ ግን የምትበገር አልሆነችም፤ ‘አማርኛ እስካግባባን ድረስ እንደፈለገን ብንጠቀምበት ችግር የለውም’ በሚለው አስተሳሰቧ  ጸናች::

የሳቂታዋ ተማሪ አስተሳሰብ በሁላችንም በተለይም አማርኛ ያፍ መፍቻ ቋንቋችን በሆነ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ላይ የሠለጠነ ነገር ሆኗል:: አማርኛ ቋንቋን እንደፈለግነው መጠቀም እንደምንችል የሚገልጽ አጓጉል ተረት  እየተረትን ቋንቋውን ሥርዓቱን እያፋለስን  ስንጠቀምበት እንስተዋላለን:: ርዕሰ ጉዳያችን ስለ ባከኑ ወይም የተደረቱ ቃላት ነውና በዚሁ ታጥሬ እስኪ ከሰማኋቸው እንዲሁም ካነበብኋቸው አገላለጾች የቃላት ብክነት የሚስተዋልባቸውን አንዳንድ አብነቶች ላንሳ፤

አብነት 1፡- “ሁለቱም የሚኖሩት አብረው በአንድ ቤት ውስጥ ነው::” በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ አብረው የሚለው ቃል ተደርቶ እናገኘዋለን፤ በአንድ ቤት የሚለው አብሮነትን የሚገልጽ ስለሆነ::

አብነት 2፡- “እንደገና በድጋሚ የተቋቋመው ክለብ…ዋንጫ ወስዷል::” እንደገና እንዲሁም በድጋሚ የሚሉት ቃላት ተመሳሳይ ፍቺን የያዙ ናቸው:: ስለሆነም አብረው መግባት አልነበረባቸውም፤ አንዳቸውን መጠቀም በቂ ነው::

አብነት 3፡- “ዛሬ ስለቲክቶክ ያወቅሁትን በሙሉ ላካፍላችሁ መጥቻለሁ ማለት ነው፤ ይሄን ቪዲዮ ጊዜ ሰጥታችሁ ብትከታተሉት በጣም ትጠቀሙበታላችሁ ማለት ነው፤ ልብ ብላችሁ ተከታተሉት ማለት ነው”  የሚሉት ዓረፍተ ነገሮች “መጥቻለሁ”፤ “ተከታተሉት”፤ “ትጠቀሙበታላችሁ” በሚሉት ግሦች መቋጨት የሚችሉ ሆነው ሳለ  “ማለት ነው” የሚሉት ቃላት ባክነዋል ወይም ተደርተዋል::

አብነት 4፡- “መቻል” በንግግርም ሆነ በጽሑፍ አላስፈላጊ እየገባ ወይም እየተደረተ ያለ ቃል ነው:: “… ፌክ ኒውስ መሆኑን መረዳት መቻል አለበት”፤ “ሥራችንን ባግባቡ መሥራት መቻል አለብን” በሚሉት ዓረፍተ ነገሮች “መቻል” የገባው አላስፈላጊ ነው፤ ቃሉን እያስወጣን ዓረፍተ ነገሮቹን ብናነብም ሆነ ብንጽፍ የሚጎድል ሀሳብ አይኖርም::

አብነት 5፡- “አቶ እገሌ ከእናቱ ከወይዘሮ እገሌ እና ካባቱ ከአቶ እገሌ ተወለደ:: … ሊሻለው ባለመቻሉ በተወለደ በ… ዓመቱ ሞተ…” እየተባለ ሲነገር እንሰማለን፤ ቀብር ሊፈጸም ሲል:: ሆኖም ከእናቱ፣ ካባቱ እንዲሁም ሊሻለው ባለመቻሉ የሚሉት የባከኑ ቃላት ናቸው:: ሟቹ ከአቶ እገሌና ከወይዘሮ እገሊት መወለዱን ከገለጽን ሰዎቹ ወላጆቹ መሆናቸው ይታወቃል:: እንዲሁም ሞተ ካልን የሞተው ሊሻለው ባለመቻሉ መሆኑ ስለሚታወቅ “ሊሻለው ባለመቻሉ” የሚለው አገላለጽ አያስፈልግም::

አብነት 6፡- “ችግሩን ለመፍታት ጥናት እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው”፤ “አገልግሎት እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ማለት ነው” የሚሉት ዓረፍተ ነገሮች “ችግሩን ለመፍታት ጥናት እየተደረገ ነው”፤ “አገልግሎት እየተሰጠ ነው” በሚል ቀልጥፈው ሊነገሩ ወይም ሊጻፉ ይችላሉ:: ሆኖም በመጀመሪያው ሦስት፣ በሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ደግሞ አምስት ቃላት ባክነዋል ወይም ተደርተዋል:: በሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ሰባት ቃላት ከባከኑ ምናልባት አንድ ገጽ በሚሞላ ጽሑፍ ወይም አሥር ደቂቃ በሚፈጅ ንግግር ውስጥ ምን ያህል ቃላት  ሊባክኑ እንደሚችሉ አስቡት!…

ይህ የቃላት ብክነት አባዜ አንድ ገጽ ጽሑፍን ለመጻፍ ለቀለም፣ ለወረቀት፣ ለመቀመሪያው (ኮምፒዩተር) መለዋወጫ የሚጠይቀው ወጪ፣ ጽሑፉን በሚያዘጋጀውም ሆነ በሚያነበው ሰው ላይ የሚፈጥረው ጫና… ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ስናጤን ብክነቱ የሀብት ጭምር እንደሆነ ይገለጽልናል:: እንዲህ ዓይነቱ የቃላት ብክነት ችግር ከመገናኛ ብዙኃን የአየር ሰዓት ውድነት አንጻር ሲመዘን ደግሞ የሚያስከትለው የሀብት ብክነት ይበልጥ ገዝፎ ይታየናል:: በተለይም ማስታወቂያ ለመንገር ወይም ለማሳተም በሰከንድም ሆነ በገጽ ከሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛነት አንጻር ነገሩን ስንመዝነው ቃላትን ማባከን ላላስፈላጊ ወጪ እንደሚዳርገን መረዳት አይከብደንም::

በእኔ እምነት ትልቁ ችግር በቃላት ብክነት ላላስፈላጊ ወጪ መዳረጋችን አይደለም:: ቋንቋ የማንነት መገለጫ ነው:: ለራስ ቋንቋ ተገቢውን ክብር አለመስጠት ለኢትዮጵያዊ ማንነት ክብር ከመንፈግ ወይም ራስን ዝቅ አድርጎ ከመመልከት ተለይቶ የሚታይ አይደለም:: ከዚህ አንጻር ይህ ባማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለው ችግር መፈታት ይኖርበታል:: ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ደግሞ በትምህርት ነው:: እንግሊዝኛን በትክክል መናገርም ሆነ መጻፍ እንችል ዘንድ የግል የእንግሊዝኛ ማስተማሪያ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ እንደሆኑት ሁሉ አማርኛ ቋንቋን በትክክል መናገርም ሆነ መጻፍ እንድንችልም ያማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያ የግል ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ::

ያማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ትምህርት ቤቶች መከፈት አለባቸው ስል ባማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም የሚስተዋለው ችግር በድረታ ብቻ የሚቆም አለመሆኑን ለውድ አንባቢያን በማስታወስ ጭምር ነው:: የፊደላትን ቅርጽ ያለመለየት እና አስተካክሎ ያለመጻፍ፣ ሞክሼ ፊደላት የሚገቡበትን ትክክለኛ ቦታ ያለማወቅ፣ ፊደላትን  መግደፍ፣ የጾታ እና የቁጥር ያለመስማማት፣ ሥርዓተ ነጥብን በተገቢው ቦታ ያለመጠቀም፣ የቃላትን ትርጉም ያለመረዳት ወይም ያለማጤን… ችግሮች በስፋት ይታያሉ:: የእነዚህ ችግሮች መኖር ያማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያ የግል ትምህርት ቤቶችን መከፈት አስፈላጊነት በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል:: ስለ ባከኑ ቃላት ይህን ያህል ካልሁ የቃላትን ትርጉም ካለመረዳት የተፈጠረን አንድ ቀልድ የሚመስል ክስተት በማውሳት ጽሑፌን ልቋጭ፤

ካሥር ዓመታት በፊት ይመስለኛል፤ ካንድ ባልደረባየ ጋር ሻይ እየጠጣን ሬድዮ እናዳምጣለን:: ጋዜጠኛው ዜና እያነበበ ነው:: እሱ እያነበበ፣ እኛም እያዳመጥን፣  “ሴት እህቶቻችን…” አለ፤ እኔና ባልደረባየ  ተያየንና ተሳሳቅን፤ ወንድ እህት አለ እንዴ በሚል:: በሳቃችን መሀል ባልደረባየ፣ “ ቆይቶ ደግሞ ወንድ ወንድሞቻችን እንዳይለን እንጂ” አለኝ:: “ይህን ፍራ…” ብየ ንግግሬን ልቀጥል ስል ጉደኛዉ ጋዜጠኛ በጎታታ ወፍራም ድምጹ “ወንድ ወንድሞቻችን…” ሲል  እየተሳሳቅን ከሻይ ቤቱ ወጣን:: ሆኖም የዚህ ሁሉ ያማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ስህተት ዋነኛ መሠረቶቹ በማኅበረሰባችን ዘንድ የተናገሩት ሁሉ ትክክል ተደርጎ የሚታይላቸው ጋዜጠኞቻችንን መሆናቸውን ስንገነዘብ “ለምን?” የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ተሰነቀረና ሳቃችን እንደጉም በኖ ጠፋ::

(ቦረቦር ዘዳርአገር)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here