ፀጋዎችን ለመጠቀም …

0
255

በኢትዮጵያ አጠቃላይ ለእርሻ ከሚውለው መሬት ከ35 በመቶ የሚበልጠውን የአማራ ክልል እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ። ክልሉ ለሰብል ልማትም ሆነ ለእንስሳት እርባታ ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የውኃ ሀብት እና ለም መሬት የሚገኝበት በመሆኑ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። በመልክዓ ምድራዊ አቀማምጡ ምክንያት የአማራ ክልል ሁሉም ዓይነት የአየር ንብረቶች (ውርጭ፣ ደጋ፣ ወይና ደጋ፣ ቆላ እና በረሃማ) ይገኙበታል።

በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው፡፡ ዞኑ ለኢንቨስትመንት ሥራ የሚውል ሰፊ የእርሻ መሬት ያለው ነው። ከእንስሳት ሀብት ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ እና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ይመረትበታል። የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እና ለፋብሪካ ግብዓት የሚውሉ እንደ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ጥጥ እና ሌሎች ሰብሎች በስፋት የሚመረቱበትም ነው። አካባቢው የለም መሬት ባለቤት በመሆኑ የተሻለ ምርት እየተመረተበት ይገኛል።

ዞኑ በርካታ ፀጋዎች የሚገኙበት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ቀጣና ያለው መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ከአሚኮ ወቅታዊ ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል። ምዕራብ ጎንደር ዞን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለቤትም ነው። ከአጎራባች ሀገር ጋር የሚገናኝ፣ ምርትን ማስወጣት እና ማስገባት የሚችል እንደሆነም  ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው እንዳብራሩት ከስድስት መቶ ሺህ ሔክታር በላይ የሚታረስ መሬት ሲኖረው በሦስት ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች ይሸፈናል። ይኸውም ለውጭ ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ፣ ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ እና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ የሰብል አይነቶች የሚመረቱበት ዞን ነው። ለመስኖ ልማት የሚሆኑ ሰፋፊ ወንዞች ባለቤትም ነው።

ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች ያሉበት አካባቢ ነው። በዞኑ 22 የሚደርሱ ወንዞች የሚገኙ ሲሆን ዘጠኙ ዓመቱን ሙሉ እንደሚፈሱም አስረድተዋል። ለአብነትም አይማ፣ ሽንፋ፣ ጓንግ እና አንገረብ ወንዞች ይገኙበታል። እነዚህ ወንዞች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የተሻለ ምርት ማምረት እንዲችሉ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል። አይማ 50 ሺህ ሔክታር መሬት፣ አንገረብ ከ50 ሺህ ሔክታር በላይ፣ ሽንፋ 95 ሺህ ሔክታር መሬት ማልማት እንደሚችሉም አስረድተዋል። በአጠቃላይ ወንዞቹ  ከሁለት መቶ ሺህ ሔክታር በላይ መሬት  ማልማት የሚችሉ ናቸው ብለዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል ወንዞችን በአግባቡ ተጠቅሞ በቂ ምርት ማምረት አስፈላጊ ነው ብለዋል። እነዚህን ወንዞች በሙሉ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ከክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር እየተሠራ ነውም ብለዋል። የተሻለ ምርት ለማግኘት ሰላምን ማስፈን፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን መከተል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማድረስ፣ መሬትን በክላስተር (በኩታ ገጠም) ማረስ፣ ሜካናይዜሽን ማስፋፋት አስፈላጊ በመሆናቸው ትኩረት እየተሰጣቸው ያሉ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ምርታማነትን ለማሳደግ 525 የሚሆኑ ትራክተሮች በዞኑ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።

ምዕራብ ጎንደር ዞን በቱሪዝም ዘርፍ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች የሚገኙበት አካባቢ ነው። በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሻለ እና ሊጎበኙ የሚችሉ እንደ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ ማሕበረ ሥላሴ ጥብቅ ደን እና ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት አለው። እነዚህ ፓርኮች የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ በኩል በተለይም የተስተካከለ ዝናብ እንዲኖር፣ መሬትን ከጎርፍ አደጋ በመከላከል፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ ለመድኃኒት ቅመማ፣ ለመሠረታዊ ሥራዎች እና ለሌሎች አገልግሎቶች እየዋሉ ይገኛሉ። በተለይም  ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ 18 ሺህ 987 ሄክታር መሬት ይሸፍናል ተብሎ ይገመታል። ፓርኩ የሰሃራ በረሃን ሙቀት ለመከላከል ከሚያስችሉ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ፓርኩ በውስጡ ከ27 በላይ የእንስሳት ዝርያዎችን የያዘ እና ከ57 በላይ የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖሪያ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብ ደኖችን እንዲጠበቁ እና ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንደገለፁት ዞኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ነው፤ ሰፊ የእርሻ መሬት በመኖሩ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው። የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩት ባለሀብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

እጣን እና ሙጫ በዞኑ ይገኛል፤ ይሁን እንጂ ምርቱን ለማምረት ውስንነቶች መኖራቸውን ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ወጣቶች በዘርፉ ተሰማርተው ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው ብለዋል።  ዞኑ ካለው ዕምቅ ሀብት አኳያ ምርቶችን ወደ ተሻለ ገበያ ለማድረስ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ፈተና መሆኑንም ነው ያነሱት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ እና በፌደራል መንግሥት የመንገድ መሠረተ ልማቶች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ከዱር ቤቴ እስከ መተማ ያለው መንገድ በፍጥነት መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል። ይህም የገበያ እና ማሕበራዊ ትስስሩን ያጠናክራል ነው ያሉት።

በዞኑ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ ከተለያዩ ቦታዎች በመምጣት ራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ ለዞኑ ብሎም ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በ2016/2017 የመኸር ወቅት ከ518 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ለማልማት ከታቀደው 518 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ425 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መሸፈኑን የመምሪያ ኃላፊው አቶ አንዳርጌ ጌጡ ተናግረዋል።

ምርታማነትን  ለማሳደግ ለአልሚዎች የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ማቅረብ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በባለፈው ዓመት ከአምስት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል የለማ ሲሆን ከሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃው ያሳያል።

ሰላምን ማፅናት፣ የማያቋርጥ የሕዝብ  ግንኙነት ሥራ መሥራት፣ የፀጥታ መዋቅሩን ማደራጀት እና የግብርና ግብዓቶችን ማሟላት የ2017 ዓ.ም የዞኑ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው  ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ኢንቨስተሮችን በሚስብ መልኩ ማዘጋጀት እና ለመስኖ ልማት ትኩረት መስጠትም ከትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው። በ2017 የምርት ዘመን 617 ሺህ ሔክታር መሬት በማረስ 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልፀዋል።

ክልሉ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ በመሆኑ ሁሉም ይህን ተረድቶ “እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ” የድርሻውን በመወጣት ክልሉ የሰላም አየር የሚተነፍስበትን ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በመጨረሻም ለምጣኔ ሀብት እድገት ዋነኛ መሠረቱ ሰላም በመሆኑ ሁሌም ለሰላም ልንተጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here