“ለመምህርነት ትልቅ ክብር አለኝ”

0
173

ለአዳዲስ አሠራሮች እና ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ፍላጎት እና ቶሎ የመላመድ ችሎታ እንዳላቸው ባልደረቦቻቸው የሚናገሩላቸውን የቴያትር ባለሙያ እና መምህር በለጠ ወንዴን ባለፈው ሳምንት እትም  በእንግድነት  አቅርበንላችሁ ነበር:: በዚህ የመጨረሻ ክፍል በሥራ ላይ ያጋጠሟቸውን ፈገግ የሚያስደርጉ ገጠመኞች እና ሌሎች ተሞክሮዎችን እናካፍላችሁ፤ መልካም ንባብ!

በአማተር የቴያትር ጥበብ ቆይታ ጊዜ የማይረሱት ገጠመኝ ካለ?

ቡሬ ከተማ ብዙ ታዳሚ አለን:: እናም አንድ ጊዜ ትያትር ይዘን ለማሳየት ሄድን:: እኔ ቀኑን በሙሉ  በከተማዋ እየተዘዋወርኩ በድምፅ ማጉያ ትያትር ለእይታ ሊበቃ እንደሆነ እና ሕዝቡ የመግቢያ ትኬት እንዲቆርጥ ቅስቀሳ ሳደርግ ዋልኩ:: ወደማታ በጣም ስለደከመኝ ረፍት ላድርግ ብየ ተለየሁ፤ ቡሬ ጥሩ ጠላ ስላለ የሆነ ቦታ ጎራ ብየ አንድ ሁለት… ስጠጣ ቆየሁ:: ትንሽ ረፍት ካደረኩ በኋላ ወደ መድረኩ ተመለስኩ::

ትያትሩ አልተጀመረም፤ ሙዚቃ በድምጽ ማጉያ ተለቋል፤ አብዛኛዎቹ ባልደረባዎቼ  ተስፋ ቆርጠው እቃ መሰብሰብ ይዘዋል:: ምንድን ነው? ብየ ስጠይቅ “ሰው አልመጣም” አሉኝ:: ምን እንዳነሳሳኝ አላውቅም ሙዚቃውን አቋርጬ “ክቡራን እና ክቡራት ትኬት የቆረጣችሁ ታዳሚዎቻችን ትሪቱ ሊጀምር ስለሆነ ትኬታችሁን እየያዛችሁ ወደ አዳራሽ እንድትገቡ በትህትና እንጠይቃለን” ብየ በድምፅ ማጉያው ተናገርኩ:: ሰው ከየባሕር ዛፉ እየወጣ ወደ አዳራሹ መግባት ጀመረ::

እንደገና እቃዎቹን በፍጥነት ገጣጥመን ትያትሩን ጀመርን:: ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነበር የጀመርነው፤ ትያትሩ ሦስት ሰዓት ይፈጃል፤ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ጨረስን:: ከዚያ  ራት ፍለጋ ወጣን፤ ወቅቱ ሮንድ የሚዞርበት ጊዜ ነበር እና “የት እየሔዳችሁ ነው?” አሉን ጠባቂዎቹ፤ አዲስ መሆናችንን አውቀዋል፤ “ራት ልንበላ” አልናቸው፤ “ከተማው ተዘግቷል በሉ ግቡና ተኙ” አሉን፤ ራታችንን ሳንበላ ኩርምት ብለን አደርን፤ ይሄንን አልረሳውም::

በመምህርነት አገልግለዋል እና የእሱስ ጅማሮ እና የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በ1984 ዓ.ም ነበር የጨረስኩት:: ከዚያ በአማተር የቴያትር ሙያ፣ ከዚያም በአማራ ራዲዮ ቴክኒሻንነት ስሠራ ቆየሁ:: ከስድስት ዓመታት በኋላ የመምህርነት ስልጠና ወስጄ  በምሥራቅ ጎጃም ጨጨራ የምትባል ቦታ በመምህርነት ተመደብኩ:: አስተምር የነበረው ሰልፍ ኮንቴንድ (ሁሉንም ትምህርት በአንድ መምህር ማለት ነው) በሚባለው ሥርዓተ ትምህርት ነበር፤ አንድ ዓመት እንዳስተማርኩ ለቀቅኩ:: ምክንያቱ ደግሞ እኔ በባሕሪየ አንድ ቦታ ላይ ተረጋግቶ መቀመጥም ሆነ መሥራት የማልችል በመሆኑ ነው እንጂ ለመምህርነት ትልቅ ክብር አለኝ::

ከሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ጋር የነበረውስ ሁኔታ?

ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል የክልሉን እሴት እና ባሕል ለማስተዋወቅ በሚል በ1990 ዓ.ም ሥራ ጀምሮ ነበር:: በዘርፉ የተመረቁ ልጆችን ከየዩኒቨርሲቲው እና ሌሎች ተቋማት ለመሰብሰብ ተሞክሯል፤ በኋላ አማተር የቴያትር ባለሙያዎችን ፈልጎ መቅጠር ጀመረ፤ በዚህም የተሻለ ሥራ ተሠርቷል:: በወቅቱ እኔ በመምህርነት ስልጠና ላይ ነበርኩ ብያለሁ:: መምህርነቱን ለቅቄ ከመጣሁ በኋላ በኮንትራት ውል ከሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ጋር በድምጽ እና በመብራት ቁጥጥር እንዲሁም ቴያትር መሥራት ጀመርኩ::

የመጀመሪያ መድረካችን በሰቆጣ ከተማ ነበር:: ባሕር ማዶ የሚል ትያትር ነበር የሚቀርበው:: በመጀመሪያው ቀን አዳራሽ ሞልቶ ትያትሩ ታየ:: ቀጣይ ወደ ወልድያ ነበር የምንሄደው:: እንጓዝ ሲባል፤ ልጆቹ አዲስ ነበሩ:: የአካባቢውን ሁኔታ አያውቁም:: እንደ አዲስ አበባ መስሏቸው “ይሄንን ሁሉ ተመልካችማ ጥለን አንሄድም” አሉ:: አዲስ አበባ ውስጥ መድረክ ሞልቶ ከታየ ታዳሚው እንዲደገምለት ይፈልጋል የሚል ልምድ አላቸው::

“ይደገም” ተብሎ ሀሳቡ ሲመጣ አቶ አብቹ ኃይለማርያም ነበር ኃላፊው “እሺ” ብሎ እንድናድር አደረገን:: በመኪና ከተማውን እየዞርኩ የቅስቀሳ ሥራ ሠራሁ:: በማግስቱ መድረኩ ተዘጋጅቶ ስንጠብቅ አንድ ሰው መጣ እና “የትናንቱ ነው ወይስ ሌላ አዲስ ነው?” ብሎ ጠየቀ:: ተመልካች ስለወደደው የትላንቱ ነው የሚደገመው ብለን መለስንለት:: “የትናንቱንማ አይቸው አይደል፤ በሉ ተውት” ብሎ ሄደ:: ትያትሩ ሳይሠራ በኪሳራ እዛው አድረን በማግስቱ ወደ ወልድያ አመራን::

በአማራ ራዲዮ የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ነበሩ?

አማራ ራዲዮ እያለሁ መብራት ትልቅ ችግር ነበር፤ የመብራት መቆራረጥ በተደጋጋሚ ይከሰት ነበር:: ይህ ሲሆን ዝግጅቱ ተቋርጦ እንዳይቀር ሮጬ ጄኔሬተር ለማስነሳት እየሔዳለሁ:: ነገር ግን በወቅቱ አቅሜ ደካማ ነበረና ጄኔሬተሩን ጎትቶ ማስነሳት ይከብደኝ ነበር:: በዚህ ጊዜ ጋዜጠኞቹ ሮጠው መጥተው ያግዙኛል፤ በተለዋጭ ኃይል ዝግጅታችንን እናስቀጥላለን:: ሁለት ሦስቴ ማዳመጥ ይጠይቃል፤ ከዚህ ውጪ የቴፕ መጎልጎል (መንከስ)፣ መደምሰስ፣ የፈለጉትን ሙዚቃ አለማግኘት ይከሰታል ( የ“ሀ” እና የ“ለ”ው ይገለባበጥብሃል):: ከካሴት ወደ ሪል ቴፕ ተገልብጦ ነበር የሚተላለፈው፤ አድካሚ እና ጊዜ ወሳጅ ነበር፤ በተለይ ለቴክኒክ ተቆጣጣሪ አሰልቺ ነበር::

አማራ ራዲዮ እያለሁ ደግሞ የገጠመኝን ልናገር፤ ስቱዲዮውን የገጠሙት ስዊድናዊያን ነበሩ:: ሁሉም ወደ ሀገራቸው ሄደው አንዱ ብቻ ቀርቷል:: በመቅረቱ ተቆጭቶ ሀገራቸው ላይ ስለሚከበር የሙዚቃ በዓል ይናገራል:: ልቡ ያለው ስዊድን ነው፤ የሚያወራው ስለ ዝግጅቱ ብቻ ነበር:: ሺበሺ አለማየሁ “ለምን ለዘፈን ምርጫ ሰውየውን ቃለመጠይቅ አድርጌ አልሠራውም”? አለ:: ጥሩ ተባባልን:: ሰውየውም ሲጠየቅ ደስ አለው:: ቀረጻውን እኔ አደረኩ:: በኋላ የእንግሊዝኛው ቃለምልልስ ትርጉም ደግሞ ተቀድቶ አንድላይ አቀናበርኩት::

በማግስቱ የማይፈለጉ የክር ቅጂዎችን ካሴቱን ለሌላ ቀረጻ ለማዘጋጀት በመደምሰሻ አስወግዳለሁ:: ሺበሺ ከኪሱ የሆነ ካሴት አውጥቶ “እንካማ ይሄንም አድርገው አለኝ:: አድርጌ ሰጠሁት፤ ግን ምንድን ነው አለኝ፤ መደምሰሻ ነው አልኩት:: የተደመሰሰው የሰውየው ቃለ ምልልስ ነበር:: ከመደናቀጥ ወጥተን ወደ መፍትሄ ነው የሄድነው:: ሰውየው ጊዮን ሆቴል ነበር ያረፈው፤ ቴሌ ደውለን የጊዮን ሆቴልን ስልክ ተቀብለን ደወልን:: ሊወጣ ሲል ነበር ያገኘነው:: ስቱዲዮ አስገብተን ቀጥታ ሦስቱም ሰዎች እየተጠየቁ ተቀረጸ:: “ሰውየውም ይህ ነው ትክክለኛው መንገድ አለ” በዚህ መልኩ ገጠመኙን አሳልፈነዋል::

አሁን የፈለከውን መረጃ ከኢንተርኔት ገልብጠህ ላይቭ አስገብተህ፣ በፈጣን መተግበሪያዎች አቀናብረህ ጊዜ እና ድካም ቆጥበህ ሰፊ መረጃ እና መዝናኛ ለሕዝብ ማድረስ ይቻላል፤ ገንዘብም ይቆጥባል::

አሁንስ ከሬዲዮ ጋር ግንኙነት አለዎት? በዋናነትስ ምን ሥራ ላይ ተሰማርተዋል?

በስቱዲዮ ሥራ በተደጋጋሚ እንገናኛለን:: እዚህም (በሙሉዓለም ባሕል ማዕከል) ስቱዲዮ አለን:: በስፖንሰር የሚሠሩ በአማራ ራዲዮ እና በኤፍኤሞች የሚተላለፉ ድራማዎችን እና ጭውውቶችን እንዲሁም ማስታወቂያዎችን እኔ ነኝ የምቀርጻቸው:: አሁን በሙሉዓለም የባሕል ማዕከል የኦዲዮ ቪዢዋል ባለሙያ ሆኜ ነው እያገለገልኩ ያለሁት::

ከሥራ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ገጠመኞችን ያካፍሉን?

አንድ ገጠመኝ ላንሳ፤ አንድ ቴክኒሻን ከጋዜጠኛ ሀሰን መሀመድ ጋር የዘፈን ምርጫን ሊያቀርቡ ስቱዲዮ ገቡ:: የተመረጠው ዘፈን የንዋይ ወይም የኤፍሬም ከሁለት አንዱ ነበር:: ቴክኒሻኑ ሌላ ዘፈን ከፈተ፤ ሀሰን “እሱ አይደለም” ሲለው ደግሞ ተደናብሮ ሌላ ሙዚቃ አደረገው:: “በቃ ተወው” ብሎት ያዘፈን ካለቀ በኋላ “ዘፈኑን የጋበዛችሁ ቴክኒሻናችን እከሌ ነው” ብሎ ተናግሮ የዘፈን ግብዣውን ቀጠለ::

አንድ ጊዜ ደባርቅ ከተማ ትያትር ለማስተዋወቅ እና ፕሮግራም ለመዘርጋት ሄድኩ:: አንድ አውቶብስ ነው ያለችው:: ጠዋት ትመጣለች፤ ማታ ትመለሳለች:: እናም ትንሽ ፖስተር ስለጣጥፍ ሌላም ጉዳይ እየተጣደፍኩ ስጨራርስ ቆየሁ፤ ለማደር ተጨማሪ ወጪ አወጣለሁ፤ በቂ ገንዘብ ደግሞ አልያዝኩም፤ እናም አውቶብሷ እንዳታመልጠኝ ለአንድ ሰው “ይሄ የትያትር ፖስተር ነው፤ ወንድም ካለህ አስለጥፍልኝ” ብየ አደራ አልኩት:: ምንም ችግር እንደሌለው ነግሮ ተቀበለኝ::

ትያትሩ “አራት የደም ጥሪዎች” ነው የሚለው:: ልጁ እንዳልኩት ለጥፎታል፤ ነገር ግን ልጁ ደባርቅ ውስጥ የመጀመሪያው እምነቱን የቀየረ ሰው ስለነበር ማኅበረሰቡ በሌላ ተረድቶት ፖስተሩን ገነጣጥሎታል:: እኛ ሀገር አማን ነው ብለን ስንሄድ አንድም ፖስተር የለም:: “እንዲህ አይነት ትያትር ይመጣል፤ እንዳታዩ!” ተብሎ ሁሉ ተወግዟል:: የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለመመለስ ብዙ ነገር አደረግን፤ ሆኖም አልተሳካልንም::

አንድ ፈገግ የሚያደርግ የመጨረሻ ልናገር፤ ወቅቱ ክረምት ነበር፤ ማታ አንድ ሰዓት ከሩብ ነው፤ ዝናብ ይጥላል፤ የስቱዲዮ ተረኛ አስተዋዋቂ ጋዜጠኛ ሀሰን መሐመድ ነው:: ሀሰን አስተዋውቆ ለዜና አንባቢው ስቱዲዮውን ለቀቀ:: ዜና አንባቢው ገባ፤ በድንገት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ:: እኔ እየሮጥኩ ጄኔሬተር ለማስነሳት ሄድኩ:: አብርቼው ስመለስ ስቱዲዮ ውስጥ ማንም የለም:: ግራ ተጋባን፤ አማራጭ ስለሌለ በተደናገጠ ስሜት ሀሰን ዜናውን አነበበ:: ለካ ዜና አንባቢው “በክረምት ዝናብ ሲጥል የሬዲዮ ማቀነባበሪያ መሳሪያው መብረቅ ይስባል” እያሉ ቴክኒሺያኖቹ ሲያወሩ በመስማቱ መብረቅ እንዳይመታው ጠረጴዛ ሥር ተደብቆ ነው ያነበበው:: ከዛ በኋላ ጋዜጠኛው “መብረቁ” የሚል ቅጽል ስም ወጣለት::

እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here