የሰላም በርን ለመክፈትጥሪው ይሰማ!

0
141

ውሎ ለማምሸት፣ አምሽቶም ለማደር፣ አድሮም ለመዋል ሰቀቀን የሆኑበት አስራ ሁለት ወራቶች ተሸኙ። ካሰቡት ለመጓዝ፣ ታሞ ለመታከም፣ ለመማር፣ ለመሥራት ያልተመቹ ወራት ነበሩ። የአማራ ክልሉ ቀውስ ወገንን ከወገን አፈራርጆ ያገዳደለ እና ቁስን ያወደመ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

አሁንም የፀጥታ ሥጋቱ አልተቀረፈም። ጥርጣሬው፣ ፍረጃው፣ መተኳኮስ አልቆመም። የ2016  ግጭት ወደ 2017 ዓ.ም ተሻግሮ የሰላም እጦቱ እንዳይቀጥል የሰላም ጥሪው እየተስተጋባ ይገኛል። ጥሪው በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች እና መንግሥት እንዲደራደሩ የሚወተውት ነው። የተቆለፈ የሚመስለው የሰላም አዳራሽ የሚከፈተው በውይይት፣ በንግግር እና በድርድር   ነው።   በመደራደር እና በመነጋገር የተኩስ ምንጭ  የሆኑ ጉዳዮችን  መፍታት ይቻላል። መደራደር ሲኖር የፖለቲካ ሥነ – ምህድሩ ይሰፋል። የሚሰሙ ድምፆች ይበረክታሉ። የኩርፊያ መንስኤ ተለይተው ይፈታሉ። አብሮነት ጎልብቶ አንድነት ይፀናል። ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነት ስለሚመጣ፡፡

ሰላምም በዘላቂነት ይሰፍናል። ሰላም  በዘላቂነት የሚሰፍነው ሁሉም ተነጋግሮ ሲግባባ፣ የተግባቡበትን ቃልኪዳን ወደ ተግባር ሲመነዝረው መሆኑ ግልፅ ነው። ልጆች እንዲማሩ፣ እናቶች በሕክምና እንዲወልዱ፣ ሰቅጣጩ የአፈሙዝ ትናጋ እንዲዘጋ፣ ሐሳብ እንዲገዛ የሰላም መንገድ የሆነው ሀቀኛ ድርድር እና ንግግር  በእጅጉ አስፈላጊ  የሰላም አላባ (Element )ነው።  ሁሉም ወገን ለሠላም ዘብ መቆም እና የሕዝብ የመኖር ደህንነትን ማረጋገጥ ነው።  አባቶች “በአፍላ ፍቅር እና በአፍላ ጦርነት መሃል ምክንያታዊነት  እና እውነት  ይሸሸጋሉ::” እንደሚሉት በጦርነት  ጥላቻ፣ ፍረጃ፣ በጥርጣሬ  ምክንያት  ትርጉም አልባ መገዳደል፣  መቆሳሰል ይበረክታል። በጦርነት ውስጥ ሆኖ ነገን፣ የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት እና  ማን ወዳጅ እና ጠላት እንደሆነ እንኳን ለማወቅ ውስንነት ስለሚፈጥር ከጦርነት አዙሪት በንግግር መውጣት ይገባል።

በግጭት ውስጥ ማን? መቼ? ምን? እንደሚደርስበት እርግጠኛ ስለማይሆን  አልሞ እና አቅዶ ለመሥራት ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም። ለዚህም ነው፣ ጦርነት እና ግጭት ስልጣኔን፣ ሰባዊነትን፣ ቁስን፣ ትውፊትን  ቆራርጦ የሚበላ ፀረ ሰው ክስተት ነው የሚባለው። ከዚህ ሁሉ ውስብስብ የሰላም እጦት ለመውጣት ሁሉም ወገን ለሰላም ጥሪው አወንታዊ አበርክቶ በማድረግ  ሠላምን በዘላቂነት እናስፍን። ሰላምን ለማስፈን ማንም፣ መቼም፣ በየትኛውም አጋጣሚ ቀናኢ ሆኖ መትጋትም ይገባል።

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here