ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ጉዳዩን ትኩረት አልነፈጉትም። ከበርካታ የሴራ ትንተናዎች ጋር አዳዲስ መረጃዎችም እየተነበቡ፤ እየተደመጡ ጭምር ነው- የዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ።
የ78 ዓመቱ አዛውንት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ከ2017 እስከ 2021 እ.አ.አ ማገልገላቸው የሚታወስ ነው። ድጋሚ መንበረ ስልጣኑን ለመቆናጠጥም ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ተፋጠዋል። በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የምርጫ ቅስቀሳ ያካሄዱ ሲሆን ከተቀናቃኛቸው ጋር የመጀመሪያውን የምርጫ ክርክር በቀጥታ የቴሌቭዥን መስኮት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
እ.አ.አ ሕዳር አምስት ቀን 2024 ለሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲ ዕጩዎች ክርክር፤ የግድያ ሙከራው ከመፈጸሙ ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ነበር የተደረገው። አሜሪካውያን መራጮችም በግዙፉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን በቀጥታ የተደረገውን የምርጫ ክርክር ተመልክተዋል፤ አድምጠዋልም።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት እና የሪፐብሊካን ዕጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ክርክሩ የበላይነት ማሳየታቸው በብዙዎች ተመስክሮላቸዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሀሪስም በክርክሩ ጆ ባይደን መበለጣቸውን መናገሯን አልጀዚራ አስነብቧል።
ከምርጫ ክርክሩ ሁለት ሳምንታት በኋላ ዕጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በፔንስልቬኒያ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው። ከደጋፊዎቻቸው ፊት ለፊት ቆመው ንግግር እያደረጉ ባለበት ወቅት ወደ እርሳቸው በተተኮሰ ጥይት የቀኝ ጆሯቸውን ተመተዋል። ቶማስ ክሩክስ ትራምፕ ንግግር ለማድረግ ከቆሙበት መድረክ 130 ሜትር ብቻ ርቀት ላይ ሆኖ ነው በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተኮሰባቸው።
ዕጩ ፕሬዝዳንት የግድያ ሙከራ ከተፈፀመባቸው በኋላ ፊታቸው ላይ ደም እየታየ ሴክሬት ሰርቪስ ተብሎ በሚጠረው በአገልግሎት ጥበቃ አባላት ሽፋን ተሰጥቷቸው ከመድረኩ ሲወርዱ በተለቀቀው የተንቀሳቃሽ ምስል ታይተዋል። ይሁን እንጂ የደረሰባቸው ጉዳት ከባድ አለመሆኑን ሮይተርስ አስነብቧል። ጥቃት ፈጻሚው የ20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ ወዲያወኑ እርምጃ ተወስዶበታል::
የምርጫ ቅስቀሳውን ከቤተሰቦቹ ጋር እየታደመ የነበር አንድ ግለሰብ ለቤተሰቦቹ ሽፋን በመስጠት ራሱን ሰውቷል። ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኋላ በሰጡት ቃለ ምልልስ “በዕድል ወይም በፈጣሪ” መትረፋቸውን ተናግረዋል። በትክክለኛው ስዓት ጭንቅላቱን ማንቀሳቀሱ ሊተርፍ እንዳስቻላቸው ተደምጧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለዋሽንግተን ኤክስሚናር “ይህ መላውን ግዛት አንድ የሚያደርግ አጋጣሚ ነው፤ ዓለምን አንድ የሚያደርግ ዕድል ነው” ብለዋል። የ78 ዓመቱ አዛውንት የግድያ ሙከራው ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ግን አልሸሸጉም።
ይህ ሁነት የአሜሪካንን ፖለቲካ እስከ ወዲያኛው ሊቀይር እንደሚችል ብዙ የፖለቲካ ተኝታኞች እየተናገሩ ነው። በግድያ ሙከራው የተጠረጠረው የቤተል ፓርክ ፔንስልቬኒያ ግዛት ነዋሪ የሆነው የ20 ዓመቱ ወጣት ቶማስ ማቲው ክሩክስ ነው።
ጉዳዩንም ኤፍ ቢ አይ (FBI) እያጣራው መሆኑ ተዘግቧል። የኤፍቢአይ ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ቶማስ ማቲው ክሩክስ ብቻውን የግድያ ሙከራ ማድረጉን ደርሼበታለሁ ብሏል። ኤጀንሲው ከተጠርጣሪው ጋር የተያያዘ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት መረጃ እንዳላገኘ አስታውቋል። ቶማስ ክሩክስ የርዕዮት ዓለም ልዩነት እንደሌለው እንዲያውም የሪፐብሊካን ደጋፊ አባል መሆኑ ተደርሶበታል። ከ17 ዓመቱ ጀምሮ የፖለቲካ ደጋፊ የነበረ ሲሆን 15 ዶላር ክፍያ መዋጮ መክፈሉም ተነግሯል።
የግድያ ሙከራ ከጥብቁ የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት እና የአገልግሎት ጥበቃ አባላት (ሴክሬት ሰርቪስ) እንዴት ሊሰወር ቻለ? የሚለው ዛሬም ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። እንደዚህ ዓይነት መሰል የምርጫ ቅስቀሳዎች ሲኖሩ የአካባቢውን ፖሊሶች እርዳታ ጭምር በመጠየቅ የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት ጥበቃውን እንደሚያጠናክረ ተሰምቷል።
ታዲያ በርካታ የፖሊስ እና የደህንነት አባላት ባሉበት የግድያ ሙከራው እንዴት ተፈፀመ አሁንም ከመላምት የዘለለ ተጨባጭ መረጃ አልተገኝም። ታዳሚዎቹ እንዳሉት ተጠርጣሪው ከመተኮሱ በፊት ጣራ ላይ እያለ መመልከታቸውን ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። የበትለር ክፍለ ግዛት የፖሊስ ኃላፊ የሆነው ማይክል ስሉፕ ግን አይቶ ባላየ ማለፉን መስክረዋል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በትራምፕ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ በፅኑ አውግዘዋል። ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ በተደረገ ማግስት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሜሪካ ለእንደዚህ ዓይነት ህገወጥ ድርጊት ቦታ የላትም፤ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲለመዱ መፍቀድ የለብንም ብለዋል። ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ በሀገራችን ፖለቲካዊ ንግግሮች፣ ወሬዎች እጅግ ተጧጡፏልና ቀዝቀዝ ማለት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትራምፕ የግድያ ሙከራ የፕሬዚደንት ጆ ባይደን እጅ እንዳለበት እየተነገረ ይገኛል። በቀጣይ ሕዳር ወር በሚደረገው ምርጫ፤ ዶናልድ ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነ የእርሳቸው ምክትል ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት ሴናተር ጄዲ ቫንስ ለትራምፕ የግድያ ሙከራ ባይደንን ተጠያቂ አድርገዋል። ከሴናተሩ በተጨማሪ በርካታ የትራምፕ ደጋፊዎች የግድያ ሙከራው ከባይደን አስተዳደር ይሁንታ እና ፈቃድ ያገኘ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በኤክስ (X) በቀድሞው ትዊተር በተባለ የማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ደግሞ ሚሊዮኖች ድራማ ነው በማለት አስፍረዋል:: ያም ሆነ ይህ ግን ጥቃቱ ለዶናልድ ትራምፕ ያልታሰበ ሲሳይ ይዞላቸው መጥቷል። ትራምፕን ለመደገፍ ሲያመነቱ የነበሩት ሙሉ በሙሉ ድጋፋቸውን እንዲሰጠጧቸው አድርጓል። ከጥቃቱ በኋላ በ24 ሰዓት ውስጥ 53 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የምርጫ ድጋፍ ገንዘብም ተሰብስቧል። ቢሊየነሮች ኤሎን መስክ እና ቢል አክማን ድጋፍ ካደረጉት መካከል ይገኙበታል።
ልዕለ ኃያሏን አሜሪካ በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶናልድ ትራምፕ ከንግድ እና መዝገቦች ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በ34 ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውም አይዘነጋም።
የግድያ ሙከራው ከተሰማ በኋላ ግን የፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ሦስቱን ክሶችን መሰረዙ ተሰምቷል። በአሜሪካ ታሪክ በሰልጣን ላይ ያለም ይሁን ከስልጣን የወረደ ፕሬዝዳንት በወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሲባል የትራምፕ የመጀመሪያው ነው።
የግድያ ሙከራው መራራውን የሁለቱን ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነት ያባብሰዋል የሚል ስጋትን አሳድሯል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፖለቲካ ቀውስ አሜሪካውያንን ስጋት ላይ ጥሏል። ሮይተርስ አነጋገርኳቸው ካላቸው ሦስት ሰዎች ሁለቱ ከምርጫ በኋላ ሁከት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል። እ.አ.አ በ2020 ትራምፕ በባይደን ከተሸነፉ በኋላ የትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ ካፒቶል ግዛት ምርጫው ተጨብርብሯል በሚል አመጽ አስነስተው እንደነበረ አይዘነጋም።
የተለያየ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ያላቸው አሜሪካውያን ትራምፕ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ እያወገዙ ነው። 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በዲሞክራሲያችን ውስጥ ለአመጽ ቦታ የለንም በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ቢል ክሊንተን እና ጂሚ ካርተር ጥቃቱን አጥብቀው ከተቃወሙ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ናቸው።
ቢሊየነሩ ኤሎን መስክም “ዕጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ሙሉ በሙሉ እደግፋለሁ፤ በፍጥነት እንደሚያገግሙም ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት መልካም ምኞቱን ገልጿል።
የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የቻይና፣ የሩሲያ፣ የካናዳ፣ የጃፓን እና የጣሊያን መሪዎች በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተሞከረውን ጥቃት ካወገዙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በእርስ በእርስ ግጭት ለዜጎች የምድር ሲኦል የሆነው የአፍሪካ አህጉር መሪዎችም የግድያ ሙከራው እንዳስደነገጣቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ ሀገር ሆና ከተመሰረተችበት 1776 እ.አ.አ በኋላ በተለያዩ ፕሬዝደንቶች በርካታ የግድያ ሙከራዎች ተደርገዋል። በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች፣ ምሽት ክለቦች እና በሌሎች የሕዝብ ቦታዎች ላይ የጅምላ ጥይት መተኮስ የተለመደ ነው። በፈረንጆች 1981 ለመጨረሻ ጊዜ የቀድሞው ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገን ለመግደል ከተሞከረ በኋላ ግን በአሜሪካ ፕሬዝደንት ወይም በዕጩ ፕሬዝደንት ላይ የተደረገ የመጀመሪያው የግድያ ሙከራ ነው።
በዶናልድ ተራምፕ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ከ43 ዓመታት በኋላ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ከዚህ በፊት አራት ፕሬዝዳንቶች ሲገድሉ፤ ሦስቱ ደግሞ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል። 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን የአሜሪካን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም ያደረጉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ናቸው። ይሁን እንጂ በ1865 እ.አ.አ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝው ፎርድ ቲያትር ቤት ተውኔት እየተመለከቱ በመድረክ ተዋናዩ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው አልፏል።
ጀምስ አብርሃም ጋርፊልድ ከእ.አ.አ 1981 መጋቢት ወር እስከ መስከረም ልዕለ ኃያሏን ሀገር በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። እ.አ.አ በ1981 በወርሀ መስከረም ግን በሁለት ጥይቶች ተደብድበው ተገድለዋል። ዊሊያም ማኪንሌይ ከ1897 እስክ 1901እ.አ.አ 25ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው አሜሪካን መርተዋል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለህዝባቸው ንግግር እያደረጉ ባሉበት ወቅት በጥይት ተመተው፤ ከቀናት በኋላ ህይወታቸው አልፏል።
35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በፕሬዝደንት መንበረ ስልጣን ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው የቆዩት። ፕሬዝዳንት ኬኔዲ በዳላስ ቴክሳስ በዴሊይ ፕላዛ በኩል ታጅበው ሲጓዙ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው አልፏል። ቴዎዶር ሩዝቬልት በ1912 እና ሮናልድ ሬጌን በ1981 እ.አ.አ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ናቸው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም