ሀገራት የገጠማቸውን ግጭት እንዴት ተሻገሩት?

0
166

ኮንሰርን ዶት ኔት (concern.net) የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ጦርነት፣ ረሃብ፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ ድርቅ፣ … የዓለማችን ፈተናዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ ጦርነት ለረሃብ እና ድህነት ዋና መንስኤ በመሆን የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለው እንደሆነ ያስነብባል። በበርካታ ሀገራት የሚታዩ አሁናዊ ጦርነቶች፣ ግጭቶች እና መሰል ችግሮች አስከፊ መዘዛቸው መቀጠሉንም ያክላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ሀገራት የገጠማቸውን አስከፊ ጦርነት በብልሃት በማለፍ ዜጎቻቸውን ወደ ተሻለ ሕይወት ማሸጋገራቸውን መረጃው ያስታውሳል። ለአብነትም ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አየርላንድ፣ ቤኒን፣ ሴራሊዮን፣ … ተጠቃሽ ናቸው። የሀገራቱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ውይይት፣ ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ፣ በይቅርታ ወንድማማችነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ዋናዋናዎቹ ሀገራቱ ከችግራቸው የተሻገሩባቸው ስልቶች ናቸው።

ሪሰርች ጌት (Research Gate) የተባለው የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው ደግሞ ከ140 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ናይጄሪያ ከ250 በላይ ብሔረሰቦች መገኛ ናት፤ በተመሳሳይ ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኬንያም ከ70 በላይ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ ሀገራት ታዲያ ብሔር በወለደው ግጭት ሲታመሱ ነበር፤ ነገር ግን ሀገራቱ በወሰዱት ቁርጠኛ የእርምት እርምጃ እና ለሕዝቡም ስለ ብሔርተኝነት መዘዝ በፈጠሩት ግንዛቤ መዘዙን በእጅጉ ቀንሰውታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ስለ ብሔርተኝነት ማውራት ዘብጥያ ሊያስወረውር የሚችል የተወገዘ ድርጊት ሀኗል።

ሀገራቱ ብሔር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴን እስከ ማገድም ደርሰዋል፡፡ ለአብነትም ከዐሥር ዓመት በፊት በኬንያ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ብሔር ተኮር ግጭት ተቀስቅሶ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፤ ይህን ተከትሎም የብሔርተኝነት ፖለቲካ ማራመድን ሀገሪቱ በሕግ አግዳለች። በሀገር ደረጃ የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር እና የእርቅ ኮሚሽን ችግሩን ለመሻገር ጉልህ ሚና እንደነበረው ከድረ ገጹ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሌላው ጦርነት ካስከተለባቸው ከባድ ፈተና በጥበብ የተሻገሩ ሕዝቦች መካከል የሚጠቀሱት ሩዋንዳዊያን ናቸው። በ48 ሰዓታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ገደማ ያለቁበት የዘር ፍጅት የቆመው በምክክር፣ በይቅርታ እና ፍትሕን በተግባር በማረጋገጥ ነበር። የመረጃ ምንጩ አክሎ እንደሚያብራራው ሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት ለአክራሪ ብሔርተኝነት ምንም ቦታ የላትም፣ ሁሉም ሩዋንዳዊያን የሚጸየፉት ሆኗል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ብሔርተኝነትን ያቀነቀነ ደግሞ ሕግ ይቅርታ አያደርግለትም። እንደ መረጃው ከሆነ የሩዋንዳዊያን ሀገር በቀል ዕውቀት (በእኛ ሀገር ሽምግልና) ከገጠማቸው ከባድ ፈተና ለመሻገር ጉልህ አስተዋፅኦን አበርክቶላቸዋል። ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ታዲያ በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ነው የመረጃ ምንጩ ያስነበበው።

በተመሳሳይ ሰሜን አየርላንድ ለብዙ ዘመን በከፍተኛ ግጭት ውስጥ የቆየች መሆኑን ሪሰርች ጌት ያስታውሳል፤ እንደ መረጃው ከሆነ ግጭቱ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ነበር። የግጭቱ መዘዝ የከፋ እንደነበር በማንሳት በኋላም በሲቪክ ማሕበራት እና በምሁራን ሀገራዊ ምክክር ተካሂዶ ችግሩ መፈታቱን አስነብቧል።

በአጠቃለይ ሕዝብ ባለቤት በሆነባቸው፣ ግልጽ እና አሳታፊ ምክክሮች ያካሄዱ፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን የተጠቀሙ እና ፍትሕን በተግባር የተረጎሙ ሀገራት ከገጠማቸው ፈተና መሻገር የቻሉ ናቸው ብሏል ድረ ገጹ።

በሌላ በኩል ውስን ሀገራት የገጠማቸውን ፈተና ለመሻገር እንደተሳናቸው የመረጃ ምንጩ ያብራራል። የመን፣  ሶሪያ፣  ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ይጠቀሳሉ። ለዚህ በምክንያትነት የሚነሳው ደግሞ የውጪ እና የውስጥ ኃይሎች (ሀገራት) ጣልቃ ገብነት፣ ምክክሮች የሕዝቡን ባለቤትነት ያላረጋገጡ መሆን፣ ግልጽነት የጎደለው አካሄድ ዋናዋናዎቹ መሆናቸውን አብነቶችን በማንሳት ያብራራል። ለአብነትም በየመን እየተካሄደ ያለው ግጭት ጣልቃ ገብነት ስላለበት ምክክሩ ፍሬ አላፈራም። በሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነትም ተባብሶ የቀጠለው ከውጪ ጣልቃ ገብነት ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት መኖር እንደሆነ መረጃው አክሏል።

በተመሳሳይ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎችም ሀገራት አሁንም ድረስ ከግጭት ያልተላቀቁ ሀገራት ናቸው። ሁለት ዓመትን የተሻገረው የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነትም በደም አፋሳሽነቱ ተባብሶ ቀጥሏል። የውጭ ጣልቃ ገብነት ደግሞ የችግሩ አቀጣጣይ ነዳጅ ነው።

መዛግብት እንደሚያስገነዝቡት አብዛኛው የዓለማችን ታሪክ በጦርነት የታጀበ ነው። ጦርነቱም ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን በልቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራት የተለያዩ ስልቶችን ተግብረው ታሪክ አድርገውት ቀርተዋል። በልማት ጎዳና ላይ በመረማመድም ሀገራቸውን የዜጎች ምቹ መኖጊያ አድርገዋል። የገጠማቸውን ችግር በስክነት በማየት፣ ሕዝባቸውንም የችግሩ እና የመውጫ መንገዱ ባለቤት በማድረግ በትኩረት መሥራታቸው፣ ለሀገር በቀል የችግር መሻገሪያ ስልቶች ከፍተኛ ዋጋ መስጠታቸው፣ ሚዛናዊ እና ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማትን መገንባታቸው፣ ተጠያቂነትንም ማረጋገጣቸው፣ … ከገቡበት አጣብቂኝ ተመንጥቀው በመውጣት በዕድገት ጎዳና እንዲራመዱ ያስቻሏቸው ዋና ዋና መንገዶች ናቸው።

በሀገራችን የተከሰተውን ግጭት እልባት ለመስጠትም የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ የሚበጁትን መውሰድ ይገባል። አማራ ክልል አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በግጭት ውስጥ መሆኑ ይታወቃል። የክልሉን ሰላም ለመመለስ ታዲያ የሰላም ካውንስል (ምክር ቤት) ተቋቁሞ የሰላም ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here