ንጉሠ ነገሥት፣ የሀገር መሪዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የጦር አዛዦች፣ ራሶች፣ የአውራጃ አስተዳዳሪዎች … ወዘተ የደም ምስ ለነበረበት፤ ለ1960ዎቹ ለያኔው ትውልድ ፖለቲካ ጭዳ ሆነውለታል:: ቀሪዎቹም ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ተዋክበዋል፤ ተሰደዋል:: በዚህ ደም በለመደ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብተው ከወደቁ እውቅ ሰዎች መካከል ደግሞ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና የሙዚቃ ግጥም ደራሲዋ የሸዋሉል መንግሥቱ የምትረሳ አይደለችም:: በያኔው የግራ ቀኝ ፖለቲካ መሳሳብ ውስጥ ገና በ32 ዓመት እድሜዋ በአንድ የኢህአፓ ታጋይ ነኝ ባይ ወጣት በጥይት ተመትታ የወደቀችው የሸዋሉል መንግሥቱ ሲበዛ ሽቅርቅር ውብ በዘመኑ ቋንቋ “ጆሊ” የምትባል ሰው ነበረች ሲል ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ በአርትስ ቴሌቪዢን ተናግሯል::
ስለዚህች ዝነኛ ሰው በተለያየ ጊዜ በሬዲዮ እና በጋዜጣ እንዲሁም በሌሎች መጣጥፎች ተጽፈው የነበሩና አንዳንድ የሸዋሉል መንግሥቱን በአካል የሚያውቋት ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት እንደሚስማማ አድርገን አሰናድተነዋል:: ለዚህም “የደራው ጨዋታ የሬዲዮ ፕሮግራም፣ ታዛ መጽሔት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ አፍሮ ኤፍ ኤም እና ሌሎች የሬዲዮ ፕሮግራሞች ዋነኛ ግብዓት ሆነውናል::
የስመ ጥር ደራሲ እና ጋዜጠኛ የሸዋሉል ነገር ለዘመናት ተዳፍኖ ከቆየ በኋላ አሁን አሁን እንደአዲስ ይነገር ይዟል:: በተለይ ደረጄ ኃይሌና አዜብ ወርቁ ያሰናዱት “የደራው ጨዋታ” የሬዲዮ ፕሮግራም የሸዋሉልን ነገር ህያው አድርጎታል ለማለት ያስደፍራል:: ይህን በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1960ዎቹ ዓመታት ላይ ሰጥታው የነበረውን ቃለ ምልልስ ለአድማጮቹ በማስደመጥ የሸዋሉል ድምጽ፣ የአወራር ዘዬ፣ የህይወት ፍልስፍና እና ሌሎች ጉዳዮች ምን ይመስሉ እንደነበር የእርሷን ነገር ለማወቅ ለሚጓጓው ወዳጅ እና አድናቂ አዲስ ምስልና እይታ አምጥቶላታል::
የሸዋሉል መንግሥቱ እንደ ህይወቷ ፍልስፍና እና ኑሮዋ ስሟም ያልተለመደ ነበር:: ብዙዎች ሲጠሯት የሸዋልዑል ይሏታል:: በእርግጥም በአማርኛ ስያሜ “ልዑል” የሚለው ስያሜ ለተባዕት (ለወንድ) የሚሰጥ ማዕረግ ወይም ስም እንጂ ለሴት የሚሰጥ አይደለም:: (ለሴት ልዑል ሳይሆን ልዕልት መባሏን ልብ ይሏል::) ተሾመ ብርሃኑ ማሞ በታዛ መጽሔት ላይ ያሰፈረውም ይሄንኑ የሚያጠነክር አባባል ነው::
“አንዳንዶች ሲጽፉ ወይ ሲናገሩ ‘የሸዋልዑል መንግሥቱ’ ይሏታል። እሷ የራሷን ስም በምትጽፍባቸው አጋጣሚዎች ላይ ግን “የሸዋሉል መንግሥቱ” ብላ ነው የምትጽፈው። እንግዲህ አንድም የሸዋልዑል ብሎ ስም ለሴት ስለማይወጣ (ልዑል የተባዕት ተጸውኦ በመሆኑ)፤ አንድም ከባለቤቱ ያወቀ…” እያለ ስለየሸዋሉል መንግስቱ ያሰናዳውን ጽሐፍ ይቀጥላል::
በአንድ ወቅት በሸዋሉል መንግሥቱ የሙዚቃ ግጥም ሥራዎች እጅግ በመደነቅ ፈረንሳይ ሀገር በሚገኝ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ ትምህርት ቤት ገብቶ አማርኛን በመማር ስለእርሷ ኑሮ እና ሥራዎች ማጥናት የጀመረው ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬድሪክ ማርቴል ከአፍሮ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚነግረን ከሆነ ደራሲና ጋዜጠኛ የሸዋሉል መንግሥቱ የተወለደችው በያኔው አጠራር ምስራቅ ሃረርጌ ጃርሶ (ኤጀርሳ ጎሮ) አካባቢ በ1937 ዓ.ም ነው:: የሸዋሉል ለእናቷ ብቸኛ እና ብርቅዬ ልጅ ነበረች:: ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬድሪክ ማርቴል ደረስኩበት እንደሚለው ጥናት ከሆነ የሸዋሉል እናት ልጅ መውለድ ተስኗቸው ከቆዩ በኋላ በ46ኛ ዓመታቸው ላይ ማህጸናቸው ለምልሞ ሴት ልጅ አገኙ፤ “የሸዋሉል” ሲሉ ሰየሟት::
ስለሸዋሉል መንግሥቱ የመጀመሪያ ሥራዎች የሚነገሩት የተለያዩ መረጃዎች ናቸው:: በእርግጥ ለደራሲው “የኔ የመጀመሪያ ሥራዬ ነው” ብሎ በድፍረት የሚናገረው “የመጀመሪያውን ብዕር እና ብራናን ያገናኘበትን ጽሑፉን ወይስ ለህዝብ ያቀረበውን ስራውን?” የሚለው ጉዳይ አበይት ጥያቄ ነው:: የሸዋሉል መንግሥቱ በአንድ ወቅት ለጸደይ መጽሔት የሰጠችውን ቃለ ምልልስ ዋቢ በማድረግ ስለእርሷ የመጀመሪያ ሥራ በታዛ መጽሔት የጻፈውን ተሾመ ብርሃኑ ማሞን እና ለንጽጽር እንዲረዳ ደግሞ ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬድሪክ ማርቴል በጥናቱ ስላገኘው ሥራ በአፍሮ ኤፍ ኤም የተናገረውን በየተራ እናቅርብ::
“ትምህርቷን እዚያው የትውልድ ቀዬዋ አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን እሷና ሥነ- ጽሑፍ ገና ከ10 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ተዋውቀዋል። በአንድ ወቅት ለጸደይ መጽሔት በሰጠችው ቃለ-መጠይቅ ላይ እንደተናገረችው፤ በዚህ ዕድሜዋ የጻፈችው “የኢዮብ ትግስት” የተሰኘ ድርሰቷ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማለትም በ19 ዓመት እድሜዋ ጥቂት ማሻሻያ አክላበት በኢትዮጵያ ሬድዮ “የትያትር ጊዜ” በተባለ ፕሮግራም ላይ ተላልፎላታል። ይህ ሥራ በድርሰት ዓለም የመጀመርያ ስራዋ መሆኑ ነው” በማለት ተሾመ ብርሃኑ ማሞ ጽፏል::
ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬድሪክ ማርቴል ደግሞ እንዲህ ይለናል “የሸዋሉል ግጥም ጽፋ ህዝብ በተሰበሰበበት ያቀረበችው ገና በስምንት ዓመቷ ነበር:: አጋጣሚውም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የትውልድ ሀገራቸው የሃረርጌ ኤጀርሳ ጎሮ ጉብኝት ነበር:: የሸዋሉል ንጉሥ ፊት ቀርባ ግጥም አንብባ የ50 ብር ሽልማት አግኝታለች::”
ደራሲ አፈንዲ ሙተኪ ነሐሴ 19 2005 ዓ.ም ስለ ሸዋሉል እንዲህ ጽፏል “ይህቺ ሴት በ1969/1970 በኢህአፓ ገዳይ ስኳዶች “ሰባራ ባቡር” በሚባለው ሰፈር ከነበረው ቤቷ በራፍ ላይ ተገድላለች:: ኢህአፓዎች የግድያዋን ምክንያት ሲያስረዱ “በንጹሐን ደም እጇን ያጨቀየች ቀንደኛ የመኢሶን ገራፊ እና የገዳይ ጓድ መሪ ነበረች” ነው የሚሉት:: ሴትዮዋ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኛ እና የፕሮግራም መሪ ሆና ሳለ እንዲያ ዓይነት ተግባር ውስጥ የገባችበትን ምክንያት በትክክል መረዳት ቢከብደኝም በኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተጻፈውን ገለጻ የማስተባብልበት መንገድ ስላልነበረኝ “ታሪኩ እውነት ነው” በማለት ተቀብየው ኖሬአለሁ:: ስለርሷ በጎውን የሚናገሩ ጽሑፎችን እና ቃለ ምልልሶችን አልፎ አልፎ ባነብም ሙያዋን እና ችሎታዋን በዝርዝር ያስረዳኝ ሰው ስላልነበር በጨካኝነቷና በገራፊነቷ መዝግቤአት ቆይቻለሁ:: “የአከም ነጉማ” ደራሲ እርሷ መሆኗን ከተረዳሁበት ዕለት ጀምሮ ግን አቋሜን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ተገድጃለሁ::
አዎን! የሸዋሉል ከዕድሜዋ በፊት የተቀጨች ባለ ልዩ ችሎታ እመቤት ነበረች:: ከጥላሁን “አከም ነጉማ” ሌላ በርካታ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ዘፈኖች ግጥምና ዜማ ደራሲ ናት:: ለምሳሌም በቅርብ ጊዜ ካገኘሁት መረጃ እንደተረዳሁት “ወይ ዮቢ ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የሚለውን የዓሊ ቢራ ዘፈን የደረሰችው እርሷ ናት:: የሸዋሉል በጋዜጠኝነቱም ቢሆን ወደር አልነበራትም:: አድናቂዋ እና የሙያ ባልደረባዋ የነበረው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ‘ኢትኦጵ’ ከሚባል መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ “ትንታግ” በሚል ቃል ገልጿት እንደነበር ይታወሰኛል (በወቅቱ የርሱ ቃለ ምልልስ ዘርዘር ያለ ስላልነበር ስለርሷ በጎውን እንዳስብ ሊያነሳሳኝ አልቻለም እንጂ):: ነገር ግን የዚያ ዘመን የደም ትርኢት ይህችን የመሰለች ውብ የኪነት እመቤት ምንጭቅ አድርጎ በላት::
እኔ ጸሐፊው ከሁለቱም ወገን አይደለሁም:: የኢህአፓም ሆነ የመኢሶን አድናቂ አይደለሁም:: በመሆኑም የኢህአፓዋን ወይዘሮ ዳሮ ነጋሽን “ነፍሰጡሯ ሰማዕት” እያልኩ የማሞግስበትና የመኢሶኗን የሸዋሉል መንግሥቱን “ዮዲት ጉዲት ናት” ብዬ የምራገምበት ምክንያት የለም:: ለኔ ቀይ ሽብርም ሆነ ነጭ ሽብር ውጉዝ የሆነ የታሪክ እዳ ነው:: ያንን እዳ ማወራረድ ያለበት ግን ያኛው ትውልድ ራሱ እንጂ ይህኛው ትውልድ አይደለም:: ከያኔው ጥላቻ ጋር የሰዎችን ስብዕና እያጎደፉ መበከል በዚህ ትውልድ መቀጠል የለበትም:: ውቢቷ የብዕር ገበሬና ጠንካራ ጋዜጠኛ የነበረችው የሸዋሉል መንግሥቱም በታሪክ ተገቢ ስፍራዋ ሊሰጣት ይገባል::”
በሀገር እስራኤል ያለው ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን በደረጀ ኃይሌና አዜብ ወርቁ የደራው ጨዋታ የራዲዮ ፕሮግራም ላይ ስለ ሸዋሉል እንዲህ ብሎ ነበር። “ደረቅ ፖለቲካ ለጋዜጠኛ/ አርቲስት እንደማይሆን ያረጋገጥኩት በሸዋሉል መንግሥቱ ነው። ሸዋሉል ዘመኑ ፖለቲካ ስለሆነ ጠርቷት በአጭር የተቀጨች ሰው ናት። ዘመኑ ጥሩ አልነበረም፤ ዘመን ያሳድጋል ዘመን ይቀጫል”።
በኢሕአፓ የተገደለችው ጋዜጠኛ የሸዋሉል መንግስቱ ፖለቲካ ላይ ከነበራት ተሳትፎ በተጓዳኝ ለመሐሙድ አሕመድ ‘ትዝታ’ እና ‘አታውሩልኝ’፣ ለጥላሁን ገሠሠ ደግሞ ‘አካም ነጉማ’ ለተሰኙት ዘፈኖች በተጨማሪ ለአሊቢራም የዘፈን ግጥሞች ጽፋ የሰጠች ጎበዝ የጥበብ ሴት ነበረች። በሞተችበት ወቅት የአምስት ልጆች እናት እንደነበረች ይነገራል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም