የድሆች አለኝታ

0
252

“አፍሪካ ከድህነት መላቀቅ ያልቻለችው የትምህርት ሥርዓቱ ችግር እና በበርካቶች ዘንድ ለግብርናው  ዝቅተኛ አመለካከት መፈጠሩ  ነው” ስትል  ላቲሺያ ሙኩንጉ ትገልፃለች::

ለአብነት ልጆች ሲያድጉ በሚያዩት እና በሚሰሙት ጭቃን እና የገጠር ኑሮን ተፀይፈው እና ጠልተው ያድጋሉ:: ቤተሰብ እና መምህራንም ልጆችን ሕግ፣ ሕክምና፣ ምህንድስና… እንዲማሩ ሲያነሳሱ የግብርና ሥራን ግን በአማራጭነት ግንዛቤው አይፈጥሩላቸውም ፤እንዲያውም በትምህርቱ ደከም ያለን     ተማሪ “ገበሬ ነው የምትሆነው” ብለው በማስፈራራት ግብርና የሰነፎች ሥራ ተደርጎም እንደሚቆጠር    ላቲሺያን ጠቅሰው ሪዞሊውሽን ኘሮጀክት ዶት ኮም እና አኒዛ ኘራይዝ ዶት ኦርግ በድረ ገጻቸው አስነብበዋል::

የአፍሪካን ግብርና ለመለወጥ ከተፈለገም በትምህርት ሥርዓቱ እና በትምህርት ቤቶች ዘርፉን  የሚለውጥ ዕውቀት ማስጨበጥ እና ሠርቶ ማሳያ ማዕከል ማቋቋም ተገቢ እንደሆነ በኬንያ ገጠራማ አካባቢ ቡካራ ከተማ የተወለደችው  ላቲሺያ ውኩንጉ ጠቁማለች::

የውኩንጉ እናት እርሷን ጨምሮ  ሦስት ታናናሽ እህቶቿን በብቸኝነት እንደምታሳድግ መረጃዎች አመላክተዋል::  ከልጅነቷ ጀምራ በእናቷ ድካም ብቻ ያደገችው  ላቲሺያ  ቤተሰቡን አቅሟ በፈቀደው መጠን ለማገዝ  ከትምህርቷ ጎን ለጎን ባላት ትርፍ ጊዜ ተማሪዎችን በማስጠናት  የምታገኘውን ገንዘብ ድጋፍ ታደርግ ነበር::

ለትምህርት በተለይ ለግብርና ትልቅ ክብር እና ፍላጎት ያላት ላቲሺያ እናቷ እነሱን በብቸኝነት ለማሳደግ ልፋቷን በማየቷ በእማወራዎች  ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን መደገፍ የሚያስችል የግብርና ዘርፍ እንዲኖር እንድታስብ እና እንድትሠራ በመገፋፋት ሥራ የጀመረችው ገና በ 14 ዓመት ዕድሜዋ ነው::

በአካባቢዋ ያሉ 15 እማወራዎችን  በመሰብሰብ ጥንቸል ማርባት መሠረተች::  ላቲያ የጥንቸል ርባታውን የመረጠችው በጥቂት መነሻ ገንዘብ፣  ሥራው ቀላል ከመሆኑ ባሸገር ፀጉራቸው፣ ስጋቸው፣  ጽዳጃቸው እና ሽንታቸው ለአልባሳት፣  ለእርሻ  ግብአት… በማዋል   ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስላለው እንደሆነ ተናግራለች::

ለዚህ ተግባር ድጋፍ እንዲያደርግ የፈለገችው ደግሞ በአካባቢያቸው ያለውን ትምህርት ቤት ነው:: በቅድሚያም ለአመራሮች ሀሳቧን አቅርባ በማወያየት ማሳመን ቻለች:: ሀሳቧ ተቀባይነት እንዳገኘ ወዲያውኑ /በ2014 እ.አ.አ/ በ40 ሺህ የኬንያ ሽልንግ   ጥንቸሎችን ገዝተው ሰጧት::  እሷም በመሰረተችው የሴቶች ማህበር አማካኝነት የጥንቸሎች  ቁጥር በፍጥነት ተበራከተ::

ላቲሺያ ተወልዳ ባደገችበት መንደር የመሰረተችው ማህበር ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 290 ኪ.ሜ ርቀት አለው::  አባላት ጥንቸሎችን መግበው፣ አራብተው እና ተንከባክበው ከነ ሕይወታቸው ወደ ናይሮቢ  በመላክ በወር ከአንድ ጥንቸል ከወጭ ቀሪ  እስከ 30 የአሜሪካ ዶላር በማግኘት ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በጥሩ ሁኔታ መምራት  ቻሉ::

ላቲሺያ ለማህበሩ አባላት የርባታ ሥራውን  በብቃት  (ስኪል) ለመምራት እና ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና እንዲያገኙ ታደርጋለች:: ይህን ተከትሎ ነው አባላት በስልጠናው በቀሰሙት ዕውቀት በመታገዝ  ጥንቸሎችን በፍጥነት እያሳደጉ ከድህነት መውጣት የቻሉት:: ላቲሺያ ዘርፉን በማስፋት እማወራዎችን  ጨምሮ ሌሎች ችግረኞችንም   ተጠቃሚ ለማድረግ የበለጠ በመነሳሳት በኬንያ ምዕራባዊ ክፍል የምትገኘውን ሶፊያ ታውን ሽፕ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ምርጫዋ አደረገች::

ወጣቷ ትምህርት ቤቱን የመረጠችበትን ምክንያት ስትገልጽ “350 ወላጆቻቸውን በሞት እና በተለያዩ ምክንያቶች በማጣት ለችግር የተጋለጡ ተማሪዎች በመኖራቸው፣ ይህን ተከትሎ    የማቋረጥ ምጣኔው ከፍተኛ በመሆኑ፣ በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ የትዳር መበተን በመኖሩ በዛው ልክ የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ መከሰቱ…ነው:: ኘሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባም ከትምህርት ቤቱ 10 መምህራን እና አምስት የማህበረሠብ አባላትን የቦርድ አባል አድርጎ ነበር::

የፕሮጀክቱ  አባላት ባደረጉት ጥረት ከዘጠኝ ዓመት በኋላ/በ2023 እ.ኤ.አ/   ከ20 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ አገኘ:: በዛው ዓመት ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያመጡ  20 ሺህ ዜጎች  ከድህነት ተላቀቁ:: ፕሮጀክቱ የገጠር ሴቶችን ከነበረባቸው የከፋ ችግር አውጥቶ ገቢ እንዲፈጥሩ   በማስቻሉ አኒዛ ፕራይዝ በተሰኘ ድርጅት ለሽልማት በቃ::  ከዚህ ባለፈ በኘሮጀክቱ የሚሳተፉ ሴቶች ዘር ይሰጣቸዋል፤ ልጆቻቸው ደግሞ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ  ቁሳቁስ እና የትምህርት ቤት የደምብ ልብስ ያገኛሉ::

ጥንቸሎች በትንሽ ሀብት እና በአካባቢው የሚገኘውን ሳር ብቻ መመገባቸው   ኘሮጀክቱን ስኬታማ አድርጎታል:: የጥንቸል ፀጉር በበጋ ወራት የሚለበሱ ውድ አልባሳትን ለመሥራትም የሚጠቅም ነው::

ላቲሺያ ውጤታማ በመሆን  የአኒዛ ፕራይዝ ሽልማት እጩ በሆነችበት ወቅት ከሽልማቱ በላይ ለሽልማቱ እጩ ሆና ስትቀርብ ያደረችውን ንግግር በመስማት ብዙ ድጋፍ እና ደጋፊ ኘሮጀክቶችን የማግኘት ዕድል ከፍቶላት እንደነበረ ትገልፃለች:: ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ  የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በሰጣት የነፃ ትምህርት ዕድል በኮስታሪካ ዩኒቨርሲቲ  የአግሪካልቸራል ኢንጅነሪንግ ትምህርት እየተማረች ትገኛለች::

በደቡብ አፍሪካ የሊደርሽፕ አካዳሚ ደግሞ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታለች:: ባሁኑ ወቅት እኗቷ  የእርሻ ሥራዋን ትመራላታለች::

“ሴቶችን ሁሉ የኘሮጀክቱ አካል አድርጌ በመሥራቴ ሥራ እንዳይወድቅ ተጠንቅቀው እንዲመሩት አድርጓል:: ከወደቁ ደግሞ የነሱም ኑሮ አብሮ ስለሚወድቅ   በጥንካሬ ይሠራሉ” ስትል መስክራለች::

በኮስታሪካ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ተከታትላ ስትጨርስ ደግሞ ወደ አፍሪካ ተመልሳ በተሻለ መንገድ ለመሥራት ዕቅድ አላት:: የ24 ዓመቷ ላቲሺያ ኬኒያ ውስጥ ሴቶች በግላቸው አምርተው እንዲጠቀሙ ደግሞ የሦስት ወር ስልጠና እየተሠጣቸው እንደሚገኙ  ተናግራለች::

እንደ  ላቲሺያ እምነት “በመጀመሪያ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ  ወጣቶች የገንዘብ ድጋፍ ቢደረግላቸው በግብርና ለውጥ ይመጣል” ትላለች::  በግብር ለመሥራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በትምህርት እና በገንዘብ ድጋፍ  ማበረታታት ከተቻለ በአፍሪካ ካለው ለመሥራት ምቹ እና ጥሩ የአየር ንብረት ጋር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ታምናለች::

ላቲሺያ እንደምትለው ትምህርት ጠቃሚ ቢሆንም  ሥራ ፈጣሪነት ግን ከትምህርት በላይ ነው:: “የራስን ህልውና መገንባት፣ አጋጣሚዎችን  በተለይም በችግሮች መካከል ማየት መቻል ፤  በተለይም በድህነት፣ በበሽታ፣ በሥራ አጥነት እና በረሃብ የምትታወቀው አፍሪካ በርካታ ዕድሎች እንዳሏት ማሰብ ይገባል:: ምክንያቱም ችግሮች የፈጠራ መነሻ ናቸውና“ ስትል ትገልጻለች::

ወጣቱ ዶክተርም፣ መምህርም፣ ገበሬም ቢሆን በሥራው አዲስ ነገር መፍጠር እና የራሱን ሥራ መምራት ከቻለ የለውጥ መሪ እንደሚሆን በፅኑ ታምናለች፤ ቤተሰብ፣ መምህራን እና ሌሎችም ልጆችን እንደ ሌላው የሙያ ዘርፍ ሁሉ ስለግብርና አዋጭነት ግንዛቤ ሊፈጥሩላቸው እንደሚገባ ላቲሺያ ጠቁማለች::

ገና በ14 ዓመቷ በራሷ በግብርናው በእንስሳት ርባታ ዘርፍ  አዋጭ ሥራ  ፈጥራ የገባችው ላቲሺያ በ15 ትንሽ ጥንቸሎች   እናቷን ጨምሮ 15 ቤተሰቦችን በመያዝ የተጀመረው ሥራ ዛሬ ከ400 በላይ ጥንችሎችን በወር በማቅረብ ችግረኛ እማዎራዎችን ጨምሮ ሌሎችም ከድህነት ተላቀዋል::  300 በችግር ምክንያት መማር የማይችሉ ልጆችን መደገፍ የሚችል ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተዳደር የቻለ ኘሮጀክት መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል::

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here