እንቅልፍ እና የስኳር ህመም

0
159

ለጤናማ ሰው ከሚመከረው የእንቅልፍ ጊዜ ያነሰም ሆነ የበዛ ምጣኔ የሚያሳልፉ ጐልማሶች ለአይነት ሁለት የስኳር  በሽታ ተጋላጭነታቸውን እንደሚያመላክት ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን ያገኙትን ውጤት የቫንደር ቤልት ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው ጤናማ ያልሆነ፣ በባለሙያ ከሚመከረው ያነሰም ሆነ የተራዘመ እንቅልፍ ማዘውተር ከስኳር በሽታ ተጋላጭነት ጋር ይገናኛል::

ባለሙያዎቹ ለአንድ ጤናማ ሰው ከሚመከረው በቀን ከሰባት ሰዓት ያነሰም ሆነ ከዘጠኝ ሰዓት የበለጠ የእንቅልፍ ጊዜ ማዘውተር ከስኳር በሽታ ተጋላጭነት ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል:: ይህ ማለት ኢንሱሊን ሲበዛ በሚደርሰው መነቃቃት የእንቅልፍ ጊዜ  ሲያንስ በመድከም ረዘም ላለ ሰዓት መተኛትን ያስከትላል ሲሉ ነው ያብራሩት::

ሰላሳ ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ተሳታፊዎች የተዘጋጀውን መጠይቅ ያስሞሉት ተመራማሪዎቹ ቀደም ብሎ ከተደረጉት በተሻለ በእድሜ፣ በሥራ መስክ፣ በመኖሪያ አካባቢ ስብጥር እዲኖራቸውም አስችለዋል:: መጠይቅ የሞሉት ተሣታፊዎችም በማህበረሰብ ጤና ማእከሎች የተመረጡ መሆናቸውን በጠንካራ ጐንነት ገልፀውታል- ተመራማሪዎቹ::

በመጠይቁ የተሰጡ ምላሾችን የተነተኑት  ባለሙያዎቹ   በባለሙያ ከሚመከረው በቀን ከሰባት ሰዓት ያነሰ በእንቅልፍ የሚያሳልፉ ለዓይነት ሁለት የስኳር ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ  አረጋግጠዋል::

የአጠረ ጊዜ በእንቅልፍ የሚያሳልፉ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ እና የአካል እንቅስቃሴ ባለማድረግ የሚመጣ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ::  ሚመከረው የተራዘመ የእንቅልፍ ጊዜ የሚያሳልፉ የስኳር ህመም በሚያደርሰው ድካም መንስሄ ሊሆን እንደሚችልም ነው የጠቆሙት:: በመሆኑም የተራዘመ የእንቅልፍ ጊዜ በተከታታይ መስተዋል የስኳር ህመም ተጠቂነትን  መተንበያ ተደርጐ ሊወስድ እንደሚችል አስገንዝበዋል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here