የታንጋኒካ ኃይቅ

0
201

የታንጋኒካ ኃይቅ ከምሥራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ በስተምዕራብ ይገኛል:: ከኃይቁ አራት ሀገራት ማለትም ብሩንዲ ስምንት በመቶ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ 45 በመቶ፣ ታንዛኒያ 41 በመቶ እንዲሁም ዛምቢያ ስድስት በመቶ ድርሻ አላቸው::

የታንጋኒካ ኃይቅ ከደቡብ እስከ ሰሜን 676 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም አማካይ የጐን ስፋቱ 50 ኪሎ ሜትር ተለክቷል::

ኃይቁ በአፍሪካ በጥልቀቱ ቀደሚ ነው- ከፍተኛው ጥልቀቱ 1470 ሜትር አማካዩ ደግሞ 580 ሜትር መሆኑም ተረጋግጧል:: በጥልቀቱ ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ በስምጥ ሸለቆ ቀጣና ከሚገኙ ኃይቆች 32,600 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በተለካ ስፋቱ እንዲሁም በ1828 ኪሎ ሜትር የባሕር ዳርቻው (shore line) ቀዳሚነትን ተቆናጧል::

የታንጋኒካ ኃይቅ በአጠቃላይ የያዘው የውኃ መጠን 18980 ኪሎ ሜትር ኪዩብ (18980 km3) ሲሆን ይህም በአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ አስይዞታል:: ኃይቁን ሦስት ወንዞች ሩሲዚ፣ ማላጋራሲ እና ካላምቦ በውኃ ያረሰርሱታል::

የታንጋኒካ ኃይቅ የታችኛው ወለል ፅዋትን ጨምሮ  በእንስሳት ብስባሽ ቅሪት ግግር የተሞላ ነው:: ለዚህ ደግሞ ከኃይቁ የሚወጣ ወንዝ አለመኖሩ  ተጠቅሷል::

በታንጋኒካ ኃይቅ 300 የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ:: ከነዚሁ ዝርያዎች 95 በመቶ የሚሆኑት  በሌላ ቦታ የማይገኙ (endemic) መሆናቸው ተጠቁሟል::

በኃይቁ ዙሪያ ለሚገኙ ኗሪዎች ዓሳ የሚዘወተር ምግብ ነው:: የዓሣ ሀብት ኢንዱስትሪው መቶ ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ መስክ ወይም መተዳደሪያ ሆኗቸዋል:: በተለምዷዊውም ሆነ በዘመናዊው የዓሣ ማስገሪያ ከ165 ሺህ እስከ 200 ሺህ ቶን ዓሣ በዓመት እንደሚመረት የድረ ገፆች ጽሁፍ አመላክቷል::

ለታንጋኒካ ኃይቅ ተፋሰስ ዘላቂነት ስጋት ሆነው ከተቀመጡት መካከል የሕዝብ ብዛት መጨመር፣ ያልተገደበ  የሀብት አጠቃቀም፣ ሀብቱ  በመጤ አረም ወይም ዝርያዎች መወረር፣ ተፈጥሯዊ ለምነቱ መመናመን፣ ብክለት እና የዓየር ንብረት ለውጥ ይገኙበታል::

በኃይቁ ላይ የሚደረጉ የልማት እና የአስተዳደር ጥረቶችን የሚያስተባብር  ባለሥልጣን ራሱን ችሎ ተቋቁሟል::

ባለሥልጣኑም የዓሣ ሀብት አጠቃቀምን በእቅድ መምራት፣ ሀብቱ በመጤ አረም እንዳይጠቃ መቆጣጠር፣ የምርምር ተግባራትን መሥራት፣ ማሠራት፤ ጥበቃን ማጠናከር እና የመምራት ኃላፊነትን ተረክቧል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አፍሪካን ግሬተር ሌክስ፤ ግሎባል ኔቸር እና ዛምቢያ – ኢንፎ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here