በጃፓን ቶኪዮ ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የክፍል ጓደኛቸው የያዘውን የታሸገ የድንች ጥብስ ተካፍለው የበሉ 14 ተማሪዎች በደረሰባቸው ህመም ሆስፒታል መግባታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
በቶኪዮ ኦታ ዋርድ ቀጣና ሮኩጎ ኮካ በተሰኘ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ መሆኑን የሚያስገነዝብ ጽሁፍ የታተመበት የድንች ጥብስ የበሉ 14 ተማሪዎች በደረሰባቸው ህመም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል::
የተጠበሰውን ድንች ተካፍለው የበሉት ተማሪዎች በደረሰባቸው የአፍ እና የሆድ መለብለብ ራሳቸውን ስተው በመገኘታቸው ነው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት:: እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ተማሪዎች በቸልተኝነት የበሉት የሚለበልብ የድንች ጥብስ ለከፋ ህመም ዳርጓቸዋል:: ይህን የሰማው የድንች ጥብሱ አምራች ኩባንያ በእሽጉ ላይ ከ18 ዓመት በታች የማይመከር ለመሆኑ የማስጠንቀቂያ ፅሁፍ ማኖሩን አስታውቋል::
የድንች ጥብሱ የታሸበት “ቡት ጆልኪያ” የተሰኘ የሚለበልብ በርበሬ በዓለም የክብረወሰን መዝገብ በእጅጉ የሚያቃጥል መሆኑ ተረጋግጦ የሰፈረ ነው:: የማቃጠል ደረጃውም ከተራው በርበሬ 200 እጥፍ መሆኑ ነው የተጠቀሰው – በድረ ገጹ::
በማጠቃለያነት ማንኛውንም ምርት ገዝቶ ከመጠቀም በፊት ማሸጊያው ላይ የሚገኘውን የጥንቃቄ መልእክት ይዘቱን መገንዘብ ተገቢ መሆኑ ነው በድረ ገጹ የተሰመረበት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም