“ከሀገር በላይ ምንም የለም”

0
166

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ናቸው:: በዘርፉ ከ120 በላይ ጥናት እና ምርምሮችን አድርገዋል:: በመማር ማስተማር፣  በአሥተዳደር፣ በምርምሮች እና በማኅበረሰብ ግልጋሎት ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል:: የተለያዩ ሽልማቶችም ተበርክተውላቸዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በያዙ በ16 ዓመታት ብቻ የፕሮፌሰርነት ማዕረግን አግኝተዋል:: ይህም በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው ያደርጋቸዋል:: በቡድን ሥራ እና በቀልጣፋ ውሳኔያቸው እንደሚያደንቋቸው ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ፡- ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ:: ከፕሮፌሰር ታምራት ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ::

የት ተወለዱ? የት ተማሩ? የልጅነት ጊዜዎስ እንዴት ነበር?

የተለድኩት በደሴ ከተማ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በቅዳሜ ገበያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: ከዛ በኋላ ብዙ ስመጥር እና ትልልቅ ኢትዮጵያዊያንን ባፈራው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ዘጠነኛ እና 10ኛ ክፍልን ተምሬያለሁ:: ቀጥሎ በሆጤ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርቴን ተከታትያለሁ::

ታላቅ ወንድሜ እንዳነብ እና የተሻለ ውጤት እንዳመጣ ይፈልግ ነበር፤ ይገፋፋኝም ነበር:: አንዱ የመገፋፊያ መንገዱ ደግሞ እሱ የደረሰበትን ደረጃ በመንገር ነበር፤ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበር በወቅቱ:: እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ብዙም ማንበብ አልወድም ነበር:: በወቅቱ የማንበብ ልምዱ፣ ስሜቱ እና ፍላጎቱ ስላልነበረ ለማንበብ ደብተሩን ወይም መጽሐፉን ስይዘው እንቅልፌ ይመጣ ነበር:: ከዚያ እንቅልፉን ለማስወገድ እግሬን በቀዝቃዛ ውኃ ዘፍዝፌ ማንበብ ጀመርኩ:: ወንድሜ ከደረሰበት ደረጃ ለመድረስ መንፈሳዊ ቅናት ስለነበረኝ በዚህ መንገድ ማጥናት የጀመርኩት፤ ረጅም ሰዓት የማንበብ ልምድም አዳበርኩ:: በኋላ ላይ ሌሊት ሁሉ እየተነሳሁ ሳነብ ወላጆቼ እያሳሰባቸው በቃህ ብለው መብራት ሁሉ ያጠፉብኝ ነበር::

ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካመጣሁ በኋላ መሆን የምፈልግ የነበረው የጥርስ ሀኪም ወይም ባዮ ሜዲካል ኢንጂኔር ነበር:: ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ የቅድመ ምህንድስና ኮርስ ወስጄ ካየሁት እንዲሁም ከሲኒየር ጓደኞቼ ጋርም ስንወያይ ስለነበር ቴክስታይል ኢንጀነሪንግን መረጥኩ::

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባልተለመደ ሁኔታ በ16 ዓመታት ውስጥ እንዴት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ሊያገኙ ቻሉ?

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ምን ምን ደረጃዎች ላይ በየትኛው ጊዜ እና እድሜ መድረስ አለብኝ የሚለውን አቅጄ ነበር:: የፕሮፌሰርነት ማዕረግንም በትምህርቱ ዘርፍ ነበር ማግኘት የምፈልገው:: ስለዚህ የፕሮፌሰርነቱን ደረጃ በትንሹ ከዘገየ በ38 ዓመቴ አገኛለሁ የሚል እቅድ ነበረኝ:: ይህን ስኬት ለማግኘት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል፣ ፕሮግራሞቼን በሙሉ አስተካክየ ነበር የምንቀሳቀሰው:: በውጥኔ መሠረትም የፕሮፌሰር ማዕረጌን በ37 ዓመቴ አግኝቻለሁ::

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በአብዛኛው ከትምህርት ክፍል ወደ ዶርም፣ ከዶርም ወደ ላይብራሪ፣ ከላይብራሪ ወደ ቤተክርስቲያን ነበር እንቅስቃሴየ ማለት ይቻላል:: እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም እናነብ ነበር:: የዶርም አባላቶቼ አንባቢ ነበሩ:: ዶርም ስገባ ሰው አጥቼ ወደ ላይብራሪ የምመለስበት ጊዜ ነበር:: ለመነቃቂያ ከረሜላ ነበር የምጠቀው:: የዛን ጊዜ በደንብ ማንበቤ ለቀጣዩ ሕይወቴ መሠረት እንዲኖረኝ አድርጎኛል::

 

በአስተዳደር ረገድ የሰሩባቸውን ቦታዎች ይንገሩን?

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀልኩት በ1997 ዓ.ም ነበር:: በተማሪነት ጊዜዬ በተለያዩ ክበባት ውስጥ እሳተፍ ነበር፤ ስለዚህ ከመምህርነት እና ከኃላፊዎች ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ችያለሁ:: መምህር ሆኜ ከተቀጠርኩ በኋላም በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ:: ከዲፓርትመንት ሄድ ጀምሮ፣ አካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር፣ የድህረ ምረቃ ዲን አሁን ደግሞ በሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት እያገለገልኩ እገኛለሁ::

 

ከ120 በላይ የምርምር ሥራዎችን በግል እና በቡድን ሠርተዋል።  ምን ውጤት አምጥተዋል?

አብዛኞቹ እኛ የምንሠራቸው ምርምሮች ሀገራችን ላይ ብዙ ያልተሞከሩ ናቸው:: ያለንን የተፈጥሮ ስጦታ ወደ ሀብትነት የመቀየር ሥራ ነው የሚሠራው:: ለሀገራችን አዲስ እውቀትም ነው:: በዚህ እውቀት ላይ ብዙ ባለሙያዎች እንዲፈሩ አድርገናል:: የእውቀት ሽግግር በማምጣት ረገድ ጠቃሚ ናቸው::

በኢንዱስትሪዎች እና በግለሰብ ደረጃ የሥራ እድል አንዲፈጠር ያስቻሉ የምርምር ውጤች አሉ::  የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ማምረቻ ኢንደስትሪዎች ላይ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር አለማቀፍ ተፎካካሪ እና ዘላቀቂ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ምርምሮች ወደ ፕሮጀክት ተቀይረዋል:: በዚህም ከ17 ፋብሪካዎች ጋር እየሠራን ነው::

በሌላ በኩል የተለያዩ ሀገር በቀል እጽዋቶችን በመጠቀም ብዙ ምርቶችን ሠርተናል፤ አንዳንዶቹ ወደ ምርት ገብተዋል፤ ወደፊት ይፋ እናረጋቸዋለን:: ለምሳሌ በሀገራችን የሳኒተሪ ፓድ (ንጽህና መጠበቂያ) ጨርቅ እጥረት አለ፤ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ክፍል አልቋል፤ በሚቀጥለው ዓመት ምርት እንጀምራለን::

 

ብዙ ነገሮችን የቀየረውን በደቡብ አፍሪካ የገጠመዎትን ነገር ያጫውቱን?

የምርምር ህትመቴ ጥሩ የሚባል ስለነበር እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ጥሩ የምርምር ባለሙያዎች ብሎ ካወጣቸው 30 ተመራማሪዎች ውስጥ አንዱ በመሆኔ የተለያዩ የሥራ  እድሎች ይመጡልኝ ነበር:: በመሆኑም በውጭ እና በሀገር ውስጥ እየተመላለስኩ ነበር የምሠራው:: በወቅቱ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬን በደቡብ አፍሪካ አገኘኋቸው:: ተመላልሼ እንደምሠራ ሲያውቁ “እንደዚህ ሆነህ የምትቀጥል ከሆነ ሀገርህን በደንብ ሳታገለግል ትቀራለህ፤ ከእኔ ተማር፣  ጠቅልለህ ሀገርህ ግባ ብለው መከሩኝ::

በደቡብ አፍሪካ ያለው አይነት ማዕከል በሀገሬ ቢከፈት ለብዙዎች የሥራ እድል ይፈጥራል፣ ሀብቷን መጠቀም ያስችላታል፤ ምንዛሬ ያስገኛል፣ የእውቀት ሽግግር ያመጣል፣ የሥራ እድል ይፈጥራል ብየ አሰብኩ:: ብዙዎችን ሀገር ውስጥ እንዲያገለግሉ ማድረግም ይቻላል፤

በሌላት አቅሟ ብዙ ወጪ አውጥታ ያስተማረችኝን ሀገሬን ላገለግላት ይገባል ብየ ወደ ሀገር ተመልሼ እዚሁ መሥራት ቀጥያለሁ:: ሀገር የሚያስብላት የሚሠራላት ትውልድ ነው የሚያስፈልጋት:: ከሀገር በላይ ምንም የለም፤ አሁን በጣም በደስታ ነው የምሠራው:: በደቡብ አፍሪካ ያለውን ያክል ባይሆንም ያሰብነውን ማዕከልም ማቋቋም ተችሏል:: የተሻለ ቴክኖሎጂም እያበለጸግን ነው::

 

ስለ ፋሺን ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ይንገሩን?

እንደሚታወቀው የፋሽን ኢንዱስትሪው ከመድሃኒት ቀጥሎ ብዙ ብዙ ኢኮኖሚ እና የሰው ኃይል የሚያንቀሳቅስ ነው:: በዚህም ከአንድ ነጥብ ሰባት ትሪሊየን በላይ እና ከ400 ሚሊየን በላይ ሰው የሚያንቀሳቅስ ነው::

በፋሺን ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትታችን ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሆኜ በመመረጤ በጣም እድለኛ ነኝ:: ፋሺን ቴክኖሎጂ  ኢንስቲቲዩት የተመሠረተው በ1963 ዓ.ም ነው:: ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ከመሠረቱት አምስት ትምህርት ክፍሎች አንዱ ነው:: በወቅቱ ቴክስታይል ቴክኖሎጂ የሚባል አንድ የዲፕሎማ ፕሮግራም ብቻ ነው የነበረው:: በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከለያቸው በሀገሪቱ ከሚገኙ 10 ምርጥ የቴክኖሎጂ ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው:: ሰባት የዲግሪ ፣ ስምንተ የማስተርስ እና ዘጠኝ የፒኤችዲ ፕሮግራሞችን ይሰጣል:: እኛ እንደምናስበው በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ተቋም ነው::

እኛ ጋር የተመረቁ ልጆች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ይህን ዲፓርትመንት በማቋቋም ላይ ይገኛሉ:: የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ካየነው በየዓመቱ ጥናት እናደርጋለን:: ምሩቃኖቻችን የት ናቸው የሚለውን ማለት ነው:: አብዛኛው ምሩቅ ወይ ራሱን ሥራ ፈጥሯል አሊያ ተቀጥሯል፤ ከ85 በመቶ ተመራቂዎቻችን ሥራ ያገኛሉ:: ከ25 በመቶ በላይ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረዋል፤ ከ2 እስከ 180 ሰው በስራቸው ቀጥረዋል::

 

ያሰቡትን ዓላማ ለማሳካትዎ ምንድን ነው ሚስጥሩ?

ሚስጥር ከተባለ እንግዲህ ላሰብኩት አላማ መሳካት የሚከፈለውን ዋጋ እከፍላለሁ:: ቅድም እንዳልኩት እያንዳንዱ ደረጃ ላይ ለመድረስ በጊዜ ከፋፍያቸዋለሁ:: 1997 ዩኒቨርሲቲ ገብቼ 2000 ዓ.ም ላይ እንደጨረስኩ በሁለት ዓመታት ውስጥ ማስተርስ መማር አለብኝ ብየ አቀድኩ:: በአንድ ዓመት ተኩል ማስተርሴን ጀመርኩ:: ሦስተኛ ዲግሪየን በ30 ዓመቴ እይዛለሁ ብየ በ31 ዓመቴ ያዝኩ፤ እሷ ብቻ ከእቅዴ ውጪ ሆናለች:: ሌሎቹን ቀድሜ ወይ ባሰብኩት ጊዜ አሳክቻለሁ:: ስለዚህ እቅድ አውጥቶ መሥራት ያስፈልጋል:: ጊዜን በአግባቡ እጠቀማለሁ፤ እያንዳንዱን ሥራ በጊዜ ከፋፍየ ነው የምሠራው፤ ቢሮ ገብቼ የምሠራበት፣ ተማሪዎቼን የማገኝበት፣ ለራሴ ጊዜ የምሰጥበት የተከፋፈል ክፍለ ጊዜ አለኝ::

ከዚህ ውጪ የምሰራቸውን ሥራዎች በቡድን ነው የምሠራው:: ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁም የቡድን የምርምር ማዕከል ነው ያቋቋምኩት:: በእኔ የትምህርት ዝግጅት ሊጠቅም የሚችል 10 መምህራን ያሉበት ማዕከል ነው ያቋቋምነው::

 

ያገኟቸውን ሽልማቶች ቢጠቅሱልን?

ደቡብ አፍሪካ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተቋም ቤስት ሪሰርች አዋርድ በፈረንጆቹ 2017 አግኝቻለሁ:: በተመሳሳይ ዓመት ቤስት ሪሰርቸር በሚል የመጀመሪያውን ጎራ አግኝቼ እንደገና  ኩዋዙሉ ናታል ዩኒቨርሲቲ ተሸልሜያለሁ:: ከዛ ውጪ አብዛኞቹ ሽልማቶች የፕሮጀክት ናቸው:: ከስምንት የማያንሱ ትልልቅ  ፕሮጀክቶችን በማስጀመሬ ተሸልሜያለሁ:: ሌሎች ሽልማቶችም አሉ::

እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here