ሰላም ዋጋው ስንት ነው?

0
146

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “ሰላም ማለት ፍፁም ጤናን፣ ዕረፍትን፣ ዕርቅን፣ ፍቅርን አንድነትን፣ ደኅንነትን፣ ተድላን፣ ደስታን እና ሰላምታን ያቀፈ ጽንሰ ሐሳብ ነው። ሰው ሲገናኝ፣ ሲለያይ የሚለው፣ የሚናገረው የቡራኬ እና የምርቃት ቃል ነው” ሲሉ ትርጓሜ ሰጥተውታል።

በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችም ስለ ሰላም ብዙ ብለዋል። ለአብነትም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ሮናልድ ሬገን “ሰላም ጥል የሌለበት ማለት አይደለም:: ሰላም ማለት ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት መቻል ማለት ነው” በማለት ይገልጹታል:: የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን “ሰላምን በጉልበት ማስጠበቅ አይቻልም:: ሰላምን ማሳካት የሚቻለው በመግባባት ብቻ ነው” ብሏል::

ፋክትስ ዶት ኔት (facts.net) የተባለው ድረ ገጽ ደግሞ “የሰላም ዋጋው (The cost of peace) ስንት ነው?” በማለት ጥያቄ በመሰንዘር፣ “ምትክ የለሽ፣ ከየትኛውም ዕንቁ የሚበልጥ ዋጋ ያለው፣ የሁሉም ነገር መሠረት” በማለት ያብራራዋል።

በአጠቃላይ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በማንሳት “ያለ ሰላም ለቅሶ እንኳን አያምርም” በማለት የሰላምን ኃያልነት በርካቶች ያብራሩታል። ሰላም ካለ ሀገር ያድጋል፤ ሕዝብ ውሎ ይገባል፤ ሕፃናት ተምረው እና ፈንድቀው ከቁምነገር ይደርሳሉ። እናቶች፣ አባቶች እና አዛውንቶች ትውልዱን እያነፁ እና እያሳደጉ በጊዜያቸው አርጅተው ወደ ዘላለማዊ ጉዞ ይሄዳሉ:: ያለ ሰላም ምንም ዕቅድ እና ግብ ስኬታማ አይሆንም:: በመሆኑም ግጭትን በመግባባት፣ በመነጋገር፣ በይቅር ባይነት መፍትሔ መስጠት አትራፊው መንገድ ነው::

ለዚህም ነው “ጉልበት የእንስሳት እንደሆነ ሁሉ ሰላም የሰው ልጆች መንገድ ነው:: በጉልበት የተገኘ ድል ከሽንፈት እኩል ነው:: ምክንያቱም ጊዜያዊ ስለሆነ:: ይቅር ማለትም የትልቅነት ምልክት ነው” በማለት የሕንድ የነጻነት አባት ማሕተመ ጋንዲ የሰላምን ኃያልነት የገለጹት::

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል የሰላም እጦት ከተከሰተ አንድ ዓመትን አስቆጥሯል። የሰላም እጦቱም የበርካቶችን ሕይወት ነጥቋል። የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ የኑሮ ምስቅልቅሎሽን አስከትሏል። የንግድ እንቅስቃሴው በመቀዛቀዙም ምጣኔ ሀብታዊ ድቀትን አስከትሏል። በተመሳሳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ አፈናቅሏል።

የክልሉን ሰላም ለማምጣት ታዲያ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም የተፈለገውን ውጤት አላመጡም። በቅርቡ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ግን ተስፋ የተጣለበት ሆኗል። በተዋረድም አባላት ተሰይመው በየደረጃው ምክክር እየተካሄደ ነው። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ምክክሮች የተሳተፉ ነዋሪዎችም “ሰላም ይስፈንልን” ሲሉ ተማጽነዋል።

ሀገራችን ለገባችበት ችግር ምክንያቶቹ የዋሉ ያደሩ ናቸው፤ ለአብነትም የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት እንደአብነት ይጠቀሳል:: በመሆኑም ከገባንበት አጣብቂኝ ለመውጣት የወል ትርክትን ማረጋገጥ እንደሚገባ በተለያዩ አጋጣዎዎች እየተስተጋባ ነው::

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዘዳንት ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) በቅርቡ በተካሄደ ምክክር “የወል ትርክትን በመገንባት ሀገርን ማሳደግ ይቻላል” ብለዋል:: የታሪክ ምሁሩ እንዳሉት ታሪክን የማያውቅ ዜጋ መሠረት የለውም፤ በመሆኑም የወል ትርክትን መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

በምክክሩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ታሪክን በአግባቡ አለመያዝ እና አለመጠቀማችን በአሁኑ ወቅት ለሚስተዋሉ አለመግባባቶች ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፤ ያደጉ ሀገራት ለዕድገት መሠረታቸው ታሪክን በአግባቡ ሰንደው በመያዛቸው ነው፤ በመሆኑም ሀገርን ወደ ዕድገት ጎዳና ለማሻገር እና ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለመፍጠር ታሪካችንን በአግባቡ እውነታውን ሳይለቅ አክብሮ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ “የታሪክ ምሁራን ኃላፊነታችሁን ተወጡ” ብለዋል።

ያደጉ ሀገራት ታሪክ እንደሚያስገነዝበው በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶችን አስተናግደዋል። ይሁን እንጂ ግጭቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለዕድገታቸው መስፈንጠሪያ አድርገውታል። በሁሉም ጉዳዮች ሕዝቡን ተሳታፊ ማድረግ እና ባለቤትነቱንም ማረጋገጥ፣ ዘመን ተሻጋሪ የፍትሕ ተቀማትን መገንባት እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በዘመን ተሻጋሪ የፍትሕ ተቀማት በኩል ማረጋገጣቸው ደግሞ ሰላምን የማስጠበቂያ ምሰሶዎች ናቸው።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here