“ጥሩዬ፣ ጥሩዬ፣ ወጣች፣ ወጣች፣ የነብር ግልገል” በማለት እ.አ.አ በ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ በዐስር ሺህ ሜትር ውድድር እንደ አቦ ሸማኔ አፈትልካ ስትወጣ ማሸነፏን ያበሰረበት ከብዙዎች ጆሮ የማይጠፈው የጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ድምጽ ነው።
“ከኋላ ስትሮጥ አጠገቧ ሆኜ እንኳ ትንፋሿ አይሰማም፤ በጭራሽ ብዙ ሜትሮችን የሮጠች ሳይሆን ገና የምትጀምር ነው የምትመስለው። ከእርሷ ጋር ተፎካክሮ ለማሸነፍ መሞከር ሞኝነት ነው። ይህ ምስክርነት ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የቀድሞዋ የቱርክ ሯጭ ኤልቫና ዓብይ ለገሰ የተሰጠ ነው።
ከፈረንጆች ሚሊኒየም ወዲህ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ስማቸው ተደጋግሞ ከተጠሩት መካከል “ጥሩነሽ ዲባባ” የሚለው ስም ቀዳሚ ነው። ይህ ስም በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትር ርቀት በሚወዳደሩ ሴት አትሌቶች ዘንድ በእጅጉ የሚፈራ ጭምር ነው። በረጅም ርቀት ስማቸው ከናኘ አትሌቶች መካከል ጥሩነሽ ዲባባ ከቀዳሚዎች ተርታ ትሰለፋለች።
አትሌቷ በአንድ የኦሎምፒክ መድረክ ድርብ ድል ያስመዘገበች፤ በዓለም ሻምፒዮና ያሸነፈች ወጣት አትሌት በመሆን በክብር መዝገብ ስሟን ያሰፈረች ናት- አትሌት ጥሩ ነሽ ዲባባ።
የጥሩነሽ ዲባባ ትውልድ እና እድገቷ በአርሲ ዞን በቆጂ ከተማ ነው። አካባቢው ከባህር በላል በላይ ሁለት ሺህ 800 ሜትር ከፍታ አለው። ይህ ደግሞ ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም ለበርካታ አትሌቶች መውጣት ምክንያት ሆኗል። ጥሩነሽ ዲባባ እናቷን ለማገዝ ውሃ ለመቅዳት እና ትምህርት ቤት ለመሄድ በየ ቀኑ የምታደርጋቸው ሩጫዎች ለአትሌቲክስ ህይወቷ መሰረት መጣላቸውን በአንድ ወቅት ከሲ ኤን ኤን ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ መናገሯ ይታወሳል።
በ1999 እ.አ.አ ጥሩነሽ ዲባባ ከትምህርት ጋር ያላት እህል ውሃ አብቅቶ ወደ አትሌቲክስ ህይወት የገባችበት ወቅት እንደነበር አይዘነጋም። ጥሩነሽ ከአርሲ በቆጂ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከአክስቷ ጋር ትምህርት ለመማር ዕቅድ ቢኖራትም የትምህርት ቤቱ ምዝገባ ካለፈ ከስድስት ቀናት በኋላ በመድረሷ ከትምህርት ጋር ለመለያየት በቅታለች። ታላቅ እህቷ እጅጋየሁ ዲባባን እና አክስቷን ደራርቱ ቱሉን ተከትላም ወደ አትሌቲክስ ስፖርት ተቀላቅላለች።
የደራቱን እና የእጅጋየሁን መንገድ በመከተል የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባል በመሆን ስልጠና ጀምራለች። በ2003 እ.አ.አ በ18 ዓመቷ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በአምስት ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈች ወጣት አትሌት በመሆን ስሟን በክብር መዝገብ አስፍራለች። ለአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪም በረጅም ርቀት አዲስ ኮከብ አትሌት መወለዷን ያበሰረችበት ወቅት ነበር።
አትሌት ጥሩነሽ በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ግዜ የተሳተፈችው በ2004ቱ የአቴንስ ኦሎምፒክ ነበር። በወቅቱ በተወዳደረችበት አምስት ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋለች። መሰረት ደፋር በበላይነት ስታጠናቅቅ ኬኒያዊቷ ኤስቤላ ኦቺቺ ደግሞ ሁለተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው።
በቤጅንግ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊቷ አቦ ሸማኔ በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትር ርቀቶች ሁለት ወርቆችን ለሀገሯ ማምጣቷ አይዘነጋም። በዐስር ሺህ ሜትር አዲስ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ጭምር ማሸነፏ የሚታወስ ነው። በአንድ መድረክ በሁለቱም ረጅም ርቀቶች ወርቅ ያሳካች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትም ሆናለች።
በዚሁ የቤጂንግ ኦሎምፒክ አትሌት ቀነኒሳም በሁለቱም ርቀቶች ድርብ ድል ማስመዝገቡ አይዘነጋም። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዚሁ ዓመት በመም እና በሜዳ ተግባራት የዓመቱ ምርጥ አትሌት ክብርን ተጎናጽፋለች። ጃማይካዊው የቀድሞው የአጭር ርቀት ሯጩ ዩዜየን ቦልት በወቅቱ ለእርሱ ጥሩነሽ ምርጥ አትሌት መሆኗን መስክሮላታል።
ከቤጂንግ ኦሎምፒክ ውድድር በኋላ ጥሩነሽ ጉዳት የገጠማት ቢሆንም በ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ ግን ማሸነፍ አልተሳናትም። በ30ኛው ኦሎምፒያድ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች። እርሷ በተወዳደረችባቸው ርቀቶች ፉክክሩን በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉት ኮሜንታተሮች ቃላት እስኪያጥራቸው አወድሰዋታል። የህጻን ፊት ያላት አትበገሬዋ (Baby face Destroyer) ሲሉም ቅጽል ስም አውጥተውላታል።
በ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ ጥሩነሽ በዐስር ሺህ ሜትር ወርቅ ስታመጣ፤ ተከታዩን ደረጃ ኬኒያውያን አትሌቶች ይዘው አጠናቀዋል። መሰረት ደፋር በበላይነት ባጠናቀቀችበት አምስት ሺህ ሜትር ርቀት ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋለች። ኬኒያዊቷ ቪቪያን ቺሮየት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ አይዘነጋም።
በ2016 እ.አ.አ በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሪዮ፤ ጥሩነሽ በዐስር ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሯ አምጥታለች። ርቀቱን አልማዝ አያና በበላይነት ስታጠናቅቅ በተመሳሳይ ኬኒያዊቷ ቪቪያን ቺሮይት ነበረች ሁለተኛ ደረጃን ይዛ የጨረሰችው።
የረጅም ርቀት ንግዕስቷ ጥሩነሽ በኦሎምፒክ ድግስ በተወዳደረችበት ርቀት ያለ ሜዳሊያ ተመልሳ አታውቅም። ሦስት ወርቅ እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያ በማምጣት በድምሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። ይህም በኦሎምፒክ መድረክ በርካታ ሜዳሊያ የሰበሰበች ቀዳሚ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያደርጋታል። አትሌቷ በኦሎምፒክ ሦስት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ብቸኛዋ አትሌትም ነች።
በአጠቃላይ እስካሁን ባለው የአትሌቲክስ ህይወቷ በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች 16 ወርቅ፣ አምስት የብር እና ስድስት የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ከ2017 እ.አ.አ ጀምሮ ፊቷን ወደ ማራቶን በማዞር እየተወዳደረች ትገኛለች። በፈታኙ የማራቶን ውድድርም ስኬታማ መሆኗን አስመስክራለች።
ማራቶን በጀመረችበት በ2017 በፈረንጆቹ የቺካጎ ማራቶንን አሸንፋለች። በ2014 በለንደን እና በ2018 በበርሊን ማራቶንም የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በ2017 የለንደን ማራቶን ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፏ አይዘነጋም። ጥሩነሽ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለአራት ዓመታት ያህል ከውድድር ርቃ የቆየች ቢሆንም ባለፈው ዓመት ወደ ፉክክር መድረኩ ተመልሳለች። እ.አ.አ በ2023 ጥር ወር በተደረገው 25ኛው የሁስተን ማራቶን በማሸነፍ በድል ተመልሳለች። ጥሩ ነሽ የምንጊዜም የቦታውን ፈጣን ስዓት በማስመዝገብ ጭምር ማሸነፏ አይዘነጋም።
የሀገር ፍቅር፣ እልህ፣ አይበገሬነት እና መልካም ስነ ምግባር ለውጤታማነቷ ምክንያት እንደሆኗት ደጋግማ ትናገራለች። አትሌቷ በልምምድ ወቅት ብዙ ጊዜ ሴቶች የእርሷን የፍጥነት አቅም መቋቋም ስለሚሳናቸው ከወንዶች ጋር መሮጧ ጠንካራ እና አይበገሬ እንድትሆን አድርጓታል።
በአትሌቲክስ ስፖርት ያላትን መልካም ስም እና ዝና ለበጎ ተግባር ከተጠቀሙ አትሌቶች መካከልም አንዷ ናት። ትምህርት ቤት በመገንባት፣ ታዳጊዎች ወደ ስፖርቱ እንዲመጡ በመደገፍ እና ሌሎች በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።
የረጅም ርቀት ኮከቧ በ2012 እ.አ.አ ታይም መጽሄት ከዓለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል የጥሩነሽን ስም አካቶት እንደነበር አይዘነጋም። ዘንድሮም ESPN የተባለው የስፔን ጋዜጣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ስፖርተኞችን ሲመርጥ በሁለቱም ፆታዎች ከምርጥ ስፖርተኞች መካከል አምስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ከሴቶች ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች።
አትሌቲክስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚዘግበው የእንግሊዙ አትሌቲክስ ዊክሊ መጽሔት ከአንባቢያን በሰበሰበው ድምጽ ባለፉት 75 ዓመታት ምርጥ አትሌቶችን ከአራት ኣመታት በፊት መምረጡ ይታወሳል። ከሴቶች አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ቀዳሚዋ ምርጥ አትሌት መሆኗን መረጃው ያመለክታል። በ2008 በቻይና ቤጅንግ ባሳየችው ድንቅ ብቃት በቻይና መንግስት ትብብር በዋና ከተማችን አዲስ አበባ “የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል” በ15 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ በስሟ ተሰይሟል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም