የአክሱም ሐውልቶች

0
239

121ኛውን የአድዋ ድል የአፍሪካ ድል አድርጎ ለማክበር ከዚያም ከዚህም እንግዶችን የተቀበለችው የአድዋ ከተማ፣ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት  ዶ/ር ሙላቱን እና የማንዴላን ሀገር ልጅ ታቦይ ኢምቤኪን የመሳሰሉ ትላልቅ እንግዶችን ተቀብላ ነበር:: ታሪካዊቷ አድዋ ታላቁን የአፍሪካውያንን ድል የሰሩ ታላላቅ ጀግኖቻችንን አሻራዎች ጠብቃ ይዛ ለትውልድ የማስተላለፍ አደራዋን እየተወጣች ነበር::  አድዋ ግሩም የእንግዳ ተቀባይ ደጋግ ሕዝብ መኖሪያ መሆኗን እኔና ጓደኞቼ በቆይታችን ለማረጋገጥ ችለናል:: በልዩ የአፍሪካ ድልነት ደምቆ በተከበረው የበዓል አጋጣሚ ከአድዋ ከተማ፣ ትንሽ ወጣ ብለን የአድዋ ጀግኖች የወደቁበትን የሶሎዳ፣ ሸዊት፣ እና ኪዳነ ምሕረት ወደ ተባሉት ተራሮች ስር ስንገኝ ትናንት የተፈፀመውን ታሪክ ቦታው ራሱ ተረከልን፣ ለሀገር ክብር እና ለነፃነት የተከፈለውን ዋጋ አባቶቻችን በወደቁበት ስፍራ ተገኝተን አየን፣ በአባቶቻችን ጀግንነት የተሰማንን የኩራት ስሜት በስፍራው መገኘት ካልሆነ በእኔ ደካማ ቃላት ልገልፅላችሁ በፍፁም አልችልም::

በአድዋ ያሉት ድንቅ ታሪካዊ አሻራዎች እንዲህ ባጭሩ የሚገለጹ አይደለም፤  ላልጨርሰው አልጀምረው አይነት ስሜት አሸንፎኝ ለዚህ ሳምንት የበኩር እትም የሽርሽር አምዳችን ወደ መረጥነው ጉዳይ በቀጥታ ልንወስዳችሁ ወደድን፤ ወደ አንጋፋዋ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ አክሱም:: የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን  በወቅቱ በአክሱም የነበረንን የጉብኝት ቆይታ እያስታወስን አብረን እንዘልቃለን::

ከአድዋ ከተማ በማለዳው ተነስተን የአስደናቂ ታሪካችንን አሻራ ለማየት በላቀ ሀገራዊ ስሜት ስለ ቀድሞው ታሪካችን እየተጨዋወትን ወደ አክሱም ጉዞ ጀመርን:: በማይጠገበው የቡድን ጨዋታ ተመስጠን፤ በጨዋታ መሀል ውሉን ፍፁም በማይዘነጋው ጥንቁቁ ሾፌራችን መሪነት መንገዱ ሳይታወቀን አክሱም ገባን:: ጥቂት ሰዓታትን የሚወስደው መንገድ የደቂቃዎች ያህል ነበር ያጠረብን::

አክሱም ከተማን መርገጥ ለአብዛኞቻችን የመጀመሪያ ነበር:: የአክሱም ታሪካዊነት በማለዳው ዝምታ ውስጥ ይነበባል:: በጧት በመድረሳችን ብዙም ሰው ባናይም የከተማዋ ሕንፃዎች ግን ታሪክ ነጋሪ ባይኖር እንኳ ራሳቸው እንደሚገለጥ የታሪክ መፅሀፍ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ብቻ በማለዳው በአክሱም ከተማ ገፅታ እየተደመምን በቀጥታ ሰማይ ጠቅሶቹ የአክሱም ሐውልቶች ወደቆሙበት ስፍራ አቀናን:: የከተማው አካል ከሆነውና ‘ሴንትራል ስቴሌ ፓርክ’ ከሚባለው ከተማው መሀል ከሚገኘው የሐውልቶች መንደር ስንደርስ በታሪክ የምናውቀው የአክሱም ሐውልት ከእነ ግርማው ብቅ አለ:: ሁላችንም የሚገርም ስሜት ነበር የተሰማን:: አስደማሚ ስሜት::

የአክሱም ሐውልቶች ያሉበትን ፓርክ ከመጎብኘታችን በፊት ለአፍታ ታሪኩን ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስታውስ:: የአክሱም ሀውልቶች ዓመታት ቆመው ከትውልድ ትውልድ ታሪክ እየነገሩ የዘለቁ በምድራችን የሰው ልጅ ከተጠበባቸው ስራዎቹ ድንቆቹ ናቸው:: ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለረጅም ጊዜያት የቆየው የአክሱም ስርወ መንግሥት በአካባቢው እና በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ኃያል መንግሥት ነበር:: የዓለም የንግድ ማዕከል በነበረችው አክሱም ከተማ ላይ መዲናቸውን የመሰረቱት የአክሱም ኃያላን ነገሥታት የስልጣኔ ደረጃቸውን መስካሪ አሻራዎች በአክሱም እና በአካባቢዋ ትተው አልፈዋል::

ለሺ ዓመታት የቆሙት የአክሱም ሐውልቶችን ስናይ በተለይ እኛን ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ፍጥነት ከዚህ ትውልድ መረዳት በላይ ወደ ሆነው እፁብ ድንቅ የአባቶቻችን የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ እውቀት እያምዘገዘጉ ይወስዱናል:: በእርግጥ አንዳንዶቹ እንደቆሙ፤ የተወሰኑት ወዳድቀው ያሉ ናቸው:: ሆኖም ሁሉም የአክሱም የቀደመ ዘመን ክብር ቅሬቶች ናቸው:: እንዲሁም ከዓለም ኃያል መንግሥታት መካከል አንዱ እንደነበር ምስክር ናቸው:: የብዙ ፎቆች ሕንፃዎችን የሚወክሉት ሐውልቶቹ፤ ከማንም ሀገር በፊት የእኛው ጥንታዊ ስልጣኔ ታላላቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን የመገንባት አቅም እና ችሎታው እንደነበረው ይገልጡልናል:: ይበልጥ ቀረብ ብለን ስንመረምር እና ለማጤን ስንሞክር፤ ተደራራቢ ፎቆች የሚያስመስል እንከን የለሽ አካፋይ፣ ጌጠኛ  በሮች እና መስኮቶች የሚመስሉ ቅርፆች ያለጥርጥር  የዚያን ሩቅ ዘመን ሲቪል መሀንዲሶቻችንን ከፍተኛ የሆነ የኪነ ሕንፃ የእውቀት ደረጃ እና ጥራት የነበራቸው መሆኑን ግልፅ ምስል ይሰጣሉ:: ያም ሆነ ይህ የአክሱም ሐውልቶች ለአስደናቂው ታሪካችን ተጨባጭ አብነቶች ናቸው::

አባ ጋስፓሪኒ እንደፃፉት ሐውልቶቹ በአክሱም ነገሥታት  የተገነቡ ሲሆን እስከ መቶ ይደርሳል፤ ከእነዚህ መካከል ስድስት የሚሆኑት ትልልቅ ናቸው:: በስመ ገናናው ንጉሥ ኢዛና ዘመን በርካታ ሐውልቶች የተገነቡ ስለመሆኑ ብዙ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ:: በአክሱም ከተማ የሚገኙት ሐውልቶች በዓለም አምሳያ የሌላቸው ግዙፍ እና ድንቅ የሰው ልጅ የስራ ውጤት ተደርጎ ይታመናል::

የአክሱማውያን ድርጅታዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ክህሎቶች አብይ መገለጫ የሐውልት ግንባታ ነበር:: እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ከአፍሪካ ቀደምት ትውፊቶች ጋር እንዲጣጣሙ ሆነው የተፈጠሩ እና ከአንድ ወጥ የግራናይት አለት የተሰሩ ናቸው:: አለቶቹ ጎቤድራ ከሚባል ወደ አራት ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ ከቋጥኝ የበዛበት  አካባቢ እንደሚቆረጡ እና እንዲተከሉ ወደ ተፈለገበት ስፍራ ተጓጉዘው እንዲመጡ ይደረግ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ::

በአብዛኛው ሐውልቶቹ የባላባቶችን እና ንጉሣዊ ቤተሰቦችን መቃብሮች የማመልከት ዓላማን መሠረት አድርገው የሚተከሉ ናቸው:: ትልቁ ሐውልት የአክሱማውያን ነገሥታትን መቃብሮች ማስዋቢያም ሆኖ የሚታይ ነው:: ከአንድ ወጥ አለት የተቀረፁ ሐውልቶች በከተማዋ ሰሜናዊ እና ደቡብ ምእራባዊ አካባቢዎች ጨምሮ፤ በጉዲት ስቴሌ ፊልድ እና በሴንትራል ስቴሌ ፓርክ ውስጥ ተሰራጭተው ይገኛሉ:: ሴንትራል ስቴሌ ፓርክ የሚባለው ስፍራ ከ100 ዓ.ም አካባቢ የአካባቢያዊ ክብረ በዓል እና የሰፈራ ማዕከል በመሆን እና በረቀቀ መንገድ የተመረቱ እና የተዋቡ የአክሱም አንድ ወጥ አለት ሐውልቶች መናኸሪያ በመሆን ብቅ ማለት እንደጀመረ ይነገራል:: እኛም ጉብኝታችንን በዚሁ የሐውልቶች መንደር ይሆናል ሴንትራል- ስቴሌ ፓርክ::

በሴንትራል ስቴሌ ፓርክ በርካታ ሐውልቶች ቢኖሩም ታላቁ ሐውልት፤ የአክሱም ሐውልት እና የኢዛና ሐውልት የተባሉ ድንቅ ስራዎች በቁመታቸው፣ በክብደታቸው፣ በአቀራረፅ ስልታቸው እና በተለየ ታሪካዊ እሴታቸው ምክንያት ትልቅ ትኩረት አግኝተዋል:: ከከተማዋ ስር ሆኖ ወደ ላይ እንዲታዩ በታሰበበት አግባብ መጠነኛ ዳገታማ ስፍራ ላይ እንዲተከሉ ተደርገዋል::

ከትልቁ ሐውልት ወይም በሳይንሳዊ መለያ ስሙ ‘ስቴሌ ዋን’ ተብሎ ከሚታወቀው ትንግርታዊ ግዙፍ ሐውልት እንጀምር:: 33 ሜትር ርዝመት እና ክብደቱ 520 ቶን ይመዝናል:: ምናልባትም ይህ ሰዎች ለመትከል ከሞከሯቸው ግዙፉ ከአንድ ወጥ አለት የተቀረፀ ሐውልት ሳይሆን አይቀርም:: ሐውልቱን ወድቆ የምናገኘው ሲሆን ምናልባትም ለመትከል ሙከራ ሲደረግ ወድቆ እንደሚሆን ይገመታል:: ሐውልቱ በወደቀበት ጊዜ፣ ነፋስ መውጫ ተብሎ በሚታወቅ ለቀብር አገልግሎት በተገነባ አዳራሽ ላይ በመውደቅ ጉዳት እንዳደረሰ ይታያል:: ግዙፉ ሐውልት ሲወድቅ እንደተሰባበረ ማየት ይቻላል::

ግዙፉ ሐውልት ከሌሎች ሐውልቶች በተለየ ሁኔታ በአራቱም ጎኖቹ የተጠረበ ነው:: ባለ አስራ ሦስት ፎቅ ሕንፃን የሚወክል ሲሆን ከስር በኩል  በሮች እና መስኮቶች የሚመስል ቅርፅ፤ ከፊት እና ከኋላ አሉት-ይህም ከሕይወት በኋላ ሕይወት አለ የሚለውን እምነት የሚወክል ነው:: በቁፋሮ እንደታወቀው በዚህ ሐውልት በሁለቱም ጎኖች በኩል ዋና ዋና መቃብሮች እንደሚገኙ ተረጋግጧል::

የአክሱም ሐውልት፦ ስቴሌ ሁለት፣ ወይም የአክሱም ሐውልት የሚባለው ታሪካዊ ሐውልት ሌላው የአክሱም ትንግርት ነው:: 24 ሜትር የሚረዝም እና 200 ቶን ክብደት እንዳለው ይገመታል:: ከጣሊያን ወረራ ጋር የሚገናኝ ልዩ ታሪክ አለው:: ታላቋን ሮም እንደገና ለመገንባት ቅዠት ውስጥ የነበረው የፋሺስት ኢጣሊያ መንግሥት የአድዋ አሳፋሪ ሽንፈታቸውን ለመበቀል ለ40 ዓመታት ያህል ዝግጅት ካደረገ በኋላ ኢትዮጵያ ላይ ባደረጉት ዳግም ወረራ ወቅት በግዝፈቱ ሁለተኛ የሆነውን የአክሱም ሐውልትን ባለቤትነት ወሰዱ፣ ይህ ብቻ አይደለም የይሁዳ አንበሳ የሚባለውን ዋና የኢትዮጵያ ምልክት የሆነውን ሐውልት፣ በርካታ ንጉሣዊ እና ክህነታዊ ዘውዶችን፣ የሀገሪቱን መዛግብት እና ስእሎችን ዘርፈው ወስደዋል::

እንደ ግዙፉ ሐውልት የአክሱም ሐውልትም ኢጣሊያኖቹ ሲወሰዱት ከተለያየ ቦታ ቆራርጠው በመርከብ በመጫን በምፅዋ አልፎ፣ ከዚያም በኔፕልስ ከተማ አድርጎ እና በመጨረሻም በ1929 ዓ.ም ሮም ገባ:: ሐውልቱን በሮም ከተማ፣ ከቀድሞ የጣሊያን የቅኝ ግዛት ሚኒስቴር ፊት ለፊት፣ ከሲርከስ ማክሲመስ አጠገብ፣ ፒያሳ ዲ ስፓርታ ካፔና ላይ እንደገና ተገጣጥሞ ቆመ:: ሮም የቆመው ሐውልት ጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ህልሟ አንዱ ምልክት ሆነ::

ከዚያም በ1939 ዓ.ም ጣሊያን የኢትዮጵያን  ቅርሶች ለመመለስ በፈረመችው የሰላም ውል መሰረት ከዓመታት ጥረት በኋላ በ1997 ዓ.ም ሐውልቱ ከሮም ተነቅሎ ከሦስት ተቆራርጦ በአውሮፕላን ወደ አክሱም ከተማ እንደገና በከፍተኛ ሀገራዊ ክብር ተመልሶ ዳግም ተከላው በ2000 ዓ.ም ሚሌኒየምን አስታኮ ተተከለ::

የንጉሥ ኢዛና ሐውልት፦ የንጉሥ ኢዛና ሐውልት ወይም ስቴሌ ሦስት፣ በ4ኛው ክፍለ ዘመን ለንጉሥ ኢዛና ክብር የተገነባ ሐውልት ነበር:: ሐውልቱ ያኔ በተተከለበት እስካሁን ያለ ብቸኛው  ቦታ ያልተቀየረለት ትልቅ ሀውልት ነው:: እንዲሁም የመጨረሻው ሐውልት እንደሆነ ይገመታል::

አክሱም ከተማ በእቅፏ እስካሁን ጠብቃ ከያዘቻቸው እነዚህን ለየት ያሉና አሰራራቸው የረቀቀ፣ እንዲቆሙ የተደረገበትን ምስጢር እስካሁን ያልታወቁ ግዙፎቹን ሐውልቶች አስቃኘን እንጂ ለቁጥር የሚታክቱ የቀድሞ የኢትዮጵያን የስልጣኔና የክብር ደረጃ መስካሪ በርካታ ቅርሶችን ጠብቃ ለትውልድ ማብቃቷን በመጠቆም ቅርሶቻችን የመጎብኘት ባህል ብናዳብር ስንል እየመከርን እኛ በዚሁ አበቃን::

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here