ካማላ ሀሪስ ማን ናቸው?

0
355

ስማቸው በህንድ ውስጥ ተወዳጅ በሆነው የባህር ላይ አበባ የተሰየመው   ካማላ ሀሪስ እ.ኤ.አ   በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከነበሩት ከጃማይካዊ አባታቸው እና በጤናው ዘርፍ  በተለይ በካንሰር በሽታ ተመራማሪ ከነበሩት እናታቸው በ1964 በካሊፎርኒያ ተወለዱ::

በአሜሪካ በ47ኛው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ  አሸናፊ ለመሆን የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ያሉት ካማላ ሀሪስ  በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይነስ እና በኢኮኖሚስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል::  በ1990ዎቹ ረዳት አቃቢ ሕግ ሆነው በሠሩባቸው ዓመታት የቡድን ፀብን፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን እና ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ከባድ በተባሉ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥተዋል:: በሥራቸው በነበራቸው ትጋትም በኦክላሆማ ግዛት ዋና አቃቢ ሕግ ሆነው ሠርተዋል:: በ2010 ዓ.ም በካሊፎርኒያ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ሆነው  ተመርጠዋል:: በዚህ ጊዜም በመንግሥት የሚደረገውን ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በመቋቋም አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል::

በሙያቸው እና በሚያደርጓቸው ንግግሮች በዴሞክራቶች መካከል አንፀባራቂ ኮኮብ መሆን የቻሉት ካማላ በ2015 ዓ.ም ለቋሚ የምክር ቤት አባልነት እጩ ለመሆን በቁ:: በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም በስደተኞች አያያዝ እና በሴቶች መብት ዙሪያ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልፀው ነበር:: በዚህም ብዙም ሳይፈተኑ ምርጫውን በ2016 ዓ.ም ማሸነፍ ቻሉ:: በ2017 ካማላ ሀሪስ የመጀመሪያዋ ትውልደ ህንዳዊት እንዲሁም በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባል ሁለተኛዋ ሴት ለመሆን በቁ:: በሥራ ዘመናቸው በንግግራቸው እና በምርመራ ብቃታቸው የበርካቶችን ቀልብ ይስቡም ነበር::

ካማላ እንደሚሉት በ2020 በአሜሪካ ኘሬዝዳንታዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ መንቀሳቀስ ቢጀምሩም   በኢኮኖሚ ችግር ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለው እንደነበር   በድረ ገጻቸው አስነብበዋል::

ጠንካራዋ ሴት ግን ከሥራ አልቦዘኑም፤ በተለይ ጥቁሩ አሜካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊሶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ተከትሎ በፍትሕ ሥርአቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት በአደባባይ ታግለዋል:: በወቅቱም ብዙዎች ለጥቁር መብት ድምጻቸውን በማሰማታቸው ቢያደንቋቸውም አንዳንዶች  ደግሞ ”ለፓለቲካዊ ጥቅሟ ትኩረቱን ፈልጋ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል::

በአሜሪካ የተስፋፋውን ዘረኝነት ለመዋጋት ጆባይደን ካማላ ሀሪስን ለምርጫ አጋር አድርገው እንዲወዳደሩ በርካታ ዲሞክራቶች ግፊት እንዳደረጉባቸው ይነገራል:: ባይደንም የበርካታ አጋሮቻቸውን ምክር በመቀበል በምክትል ኘሬዝዳንትነት ማዕረግ ካማላ ሀሪስ እንዲወዳደሩ መረጧቸው:: ይህን ተከትሎም ካማላ ሀሪስ 49ኛ የአሜካ ምክትል  ኘሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል::

ከህንዳዊት እናታቸው እና ከጃማይካዊ አባታቸው የተገኙት   ካማላ ሀሪስ ለ47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ  ምርጫ  ቅስቀሳ ሲጀምሩ ስለተፎካካሪያቸው ትራምፕ ዓላማ አቃቢ ሕግ በነበሩበት ወቅት ብዙ እንደሚያውቁ ተናግረዋል፤ “በአሜሪካ ሴናተር እና ምክትል ኘሬዘዳንት ከመሆኔ በፊት በካሊፎርኒያ ሴቶችን የሚጋፋ፣ አጭበርባሪዎችን እና አታላዮችን  ብዙ  ነገሮችን ሲፈፅሙ አይቻለሁ:: ሁሉንም ሕገወጦች አይቻለሁ:: ሴቶችን የሚያስጨንቁ፣ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ደንበኞችን የሚያጭበረብሩ እንዲሁም አታላዮች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚሠሩትን ሁሉ አይቻለሁ:: የዶናልድ ትራምፕን ቢጤዎች አውቃቸዋለሁ” በማለት ነበር::

የ59 አመቷ ኢዥያዊት አሜካዊቷ ሀሪስ ከጋዛ፣ ሩሲያ፣ ከቻይና፣ ህንድ በጥቅሉ ለዓለም ፖለቲካ ያላቸው ምልከታ ምን ይሆን? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው:: ይሁን እንጅ ከግዛት  አስተዳዳሪዎች፣ ከመራጮች፣ ከተወካዮች እና በግዛት ደረጃ ባሉ መሪዎች ድጋፍ ጎርፎላቸዋል:: እስካሁን ሀሪስ መንገዳቸው መልካም ነው:: ተቀናቃኝ የተባሉ ዴሞክራቶችም እምብዛም አልተጋፏቸው:: የቀድሞዋ  አፈ ጉባኤ ቁልፍ ዴሞክራት የ84 ዓመቷ ናዚ ፖሎቪ፣ የፔንሲልቬኒያው ገዥ ጀርሽቶና፣ የሚችጋን ገዥዋ ትሬች ዌትነርን የመሳሰሉ የቁልፍ ዴሞክራቶችን ድጋፍ ማግኘታቸው በፓርቲያቸው ውስጥ ተቀባይነታቸውን እያገኙ መምጣታቸውን ያመላክታል::

ለምርጫ ቅስቀሳ ከለጋሾቻቸውም 81 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ለካማላ ሀሪስ  በታሪክ ትልቅ  እና ወደ ምርጫ ፍክክሩ ለመቅረብ ጥርጊያ መንገድ ሆኖላቸዋል::

ሀሪስ  ቀድሞ ከሚያስፈልጋቸው ተወካይ ድምጽ በላይ አግኝተዋል:: የቴክሳስ እና የትውልድ ግዛታቸው ካሊፎርኒያ ድጋፍ አድርገውላቸዋል:: በመጀመሪያው የድምጽ ሂደት ከሚያስፈልገው አንድ ሺህ 976 ተወካይ ውስጥ ከሁለት ሺህ 500 በላይ የተወካዮችን ድጋፍ አግኝተዋል:: ሮይተርስ የዜና ወኪል በሰበሰበው የሕዝብ ድምፅም  ካማላ ከተቀናቃኛቸው ትራምፕ ሁለት በመቶ ቀድመው በ42 በመቶ እየመሩ ነው።

ካማላ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቅድሚያ እሰጣቸዋለሁ ያሏቸውን ሐሳቦች ለደጋፊዎቻቸው ይፋ አድርገዋል። የጦር መሣሪያ ቁጥጥር፣ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት፣ የሕፃናት ድኅነት ቅነሳ፣ የሠራተኞች ማሕበራት መብት እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ከተጠቀሱት ፖሊሲዎች መካከል ናቸው::

የጆባይደንን ከፉክክሩ መውጣት እንዲሁም ካማላ ቀጣይዋ ዕጩ መሆናቸውን ተከትሎም በደቡባዊቷ ሕንድ ከተማ ቻናይ ግዛት 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አነስተኛዋ መንደር ቴላሴንድድራፑራም ነዋሪዎች የአሜሪካዋን ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስን ”የእኛ ናት” እያሉ ነው። ከዋሽንግተን ዲሲ በ14 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች አነስተኛ መንደር የካማላ ሀሪስ የእናታቸው የትውልድ ስፍራ እና የአያቶቻቸው መኖሪያ ነበረች::

በመንደሯ ማዕከል የ59 ዓመቷ ካማላ ሀሪስ ፎቶ በትልቅ ተሰቅሎ ይታያል። የዲሞክራቶች ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የሆኑት ካማላ እንዲሳካላቸውም የመንደሯ ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው::

ካማላ ሃሪስ በተለይም ለሕንዳውያን ሴቶች ኩራት ሆነዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቷን እንደ ራሳቸው ማኅበረሰብ አካል አድርገው የሚመለከቷቸው ሲሆን፣ በየትኛውም ቦታ ሴቶች መድረስ የሚችሉበትን ስፍራ ተምሳሌት ሆነዋል።

“ሁሉም ሰው ያውቃታል፣ ልጆች ጭምር፤ ‘እህቴ፣ እናቴ’ እያሉ ነው የሚጠሯት” ሲሉ የመንደሯ አስተዳደር ተወካይ አሩልሞዝሂ ሱድሃካር ገልጸዋል። “መሠረቷን ስላልዘነጋች ደስ ብሎናል። ደስታችንንም እየገለጽን ነው” ብለዋል።

“እናቴ ሻይማላ ከሕንድ ወደ አሜሪካ የመጣችው በ19 ዓመቷ ነበር። ኃያል ሴት፣ ሳይንቲስት፣ የሲቪል መብት ተሟጋች እንዲሁም ሁለት ሴት ልጆቿ በኩራት እንዲያድጉ ያደረገች እናት ናት” ሲሉም ካማላ  የሕይወት ታሪካቸውን በሚተርከው ‘ዘ ትሩዝስ ዊ ሆልድ’ የሚል ርዕስ በተሰጠው መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

ሀሪስ “በመጭው ሕዳር ወር በሚደረገው የምርጫ ቅስቀሳ ”ምን ማድረግ እንዳለብን አውቀናል፤ የምናኳኳቸው በሮች አሉ፣ የምናወራቸው ሰዎችም አሉ፣ ስልክ የምንደውልላቸው አሉ” ሲሉ ተደምጠዋል:: ታዲያ ዲሞክራቶችን ለመወከል የሚያስችለቻውን ቁመና የያዙት ሀሪስ ጉባኤው ሲያፀድቅላቸው በአሜሪካ ኘሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያዋ  ሴት ተፎካካሪ ይሆናሉ::

በአሜሪካ በ256 ዓመታት ታሪክ 46 ጊዜ በተካሄደ ምርጫ አንድም ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን አልታደለችም:: በ47ኛው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ  ካማላ ሀሪስ ካሸነፉ በአሜሪካ አዲስ ምእራፍ ይፈጠራል:: ይሁንና  “በታሪኳ እንኳን ጥቁር ሌላ ሴት መሪ አይታ የማታውቀው አሜሪካ ሀሪስን ኘሬዝዳንት ታደርጋለች ወይ? የመራጩስ ተቀባይነት ምን ያህል ነው?” የሚለው አወዘጋቢ መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል::

ከአቃቢ ሕግ እስከ ካሊፎርኒያ ሴናተርነት፣ ከምክትል ኘሬዝዳንትንት እስከ ኘሬዝዳንታዊ እጩነት እየገሰገሱ ያሉትን ሀሪስ የሚከብዳቸው የዴሞክራቶች ተመራጭ ሆነው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ጉዞ ማድረግ ሳይሆን ከሥር ከሥራቻው ስህተታቸውን እየለቀሙ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሳጧቸውን ሪፐብሊካኑን ትራምፕን ማሸነፍ እንደሆነ ጠቁመዋል::

ካማላ በ2014 ከአሜሪካዊው ጠበቃ ጋር ትዳር መስርተዋል:: ሀሪስ ባለቤታቸው ከቀድሞ ትዳራቸው   ያፈሯቸውን ሁለት ልጆች እንደ ልጆቻቸው  አድርገው  ማሳደጋቸውንም የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል::

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here