ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ

0
154

ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ አፍሪካ በ1926 እ.አ.አ ነው ህጋዊ ሆኖ የተመሰረተው:: ፓርኩ በግምት 360 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም አማካይ ወርድ ወይም የጐን ስፋቱ 65 ኪሎ ሜትር ተለክቷል፤ ጠቅላላ ስፋቱ 19,485 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ነው::

በፓርኩ ውስጥ 1800 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መጓጓዣ ጠጠር የለበሰ መንገድ፣ 21 የማረፊያ ጣቢያዎች (ካምኘ)፣ 17 የግል ሎጂዎች አሉት:: የፓርኩን ክልል በውኃ የሚያረሰርሱ ስድስት ወንዞች ቢኖሩትም የሚደርቁበት ወቅት በመኖሩ በሰው ሰራሽ መንገድ ውኃ ማቅረብን ግድ እንደሚል ነው ድረ ገፆች ያስነበቡት::

ክሩገር ፓርክ ሳር ከተሸፈነ ገላጣ ክልል  እስከ ጥቅጥቅ የደን ምድርን ያካተተ ነው:: በፓርኩ ከሚገኙ በመጠን ግዝፈት ካላቸው የዱር እንስሳት ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦ ሸማኔ፣ ጐሽ፣ አውራሪስ፣ የሜዳ አህያ የዱር ውሻ (ተኩላ)፣  ተጠቃሽ ናቸው::

በግዝፈቱ በአፍሪካ ቀዳሚ በሆነው ፓርክ በግምት የአፍሪካ ጐሽ 27 ሺህ፣ አንበሳ 1500፣ አውራሪስ 350፣ የሜዳ አህያ 18 ሺህ፣ አቦሸማኔ 200፣ ቀጭኔ  አምስት ሺህ፣ ጉማሬ ሦስት ሺህ ነብር አንድ ሺህ  ዝሆን 12 ሺህ፣ “wild beest’’ 12 ሺህ፣ የአፍሪካ የዱር ውሻ 300፣ ነጭ አውራሪስ ከሰባት ሺህ እስከ 12 ሺህ፣ ዥንጉርጉር ጅብ ሁለት ሺህ እንደሚገኝ  ተመላክቷል::

ፓርኩ ከትልልቅ ዛፍ እስከ ሳር የተለያዩ 24 የእፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙበት ነው  የተዘረዘረው:: ከሁሉም በላይ ግን አብዛኛው የፓርኩ ክልል በሳር የተሸፈነ ነው:: ይህም በክልሉ በሚፈሱ ወንዞች እንደየወቅቶቹ ልምላሜን ሲላበስ በግጦሽ የሚኖሩትን ያሰባስባል፤ ሲደርቅ ደግሞ ሳር በል እንስሳቱ  በወንዞች ወደ ሚለመልምበት ቀጠና ያመራሉ:: ሳር በል የዱር እንስሳቱን መፍለስ ተከትለው ስጋ በል አዳኞቹም ከቦታ ቦታ ይከተሏቸዋል::

በክሩገር ብሔራዊ ፓርክ በሚገኙት ወንዞች 49 የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጧል:: ዓሣዎችን የህልውናቸው መሰረት ያደረጉ እንስሳት ደግሞ በነሱ ላይ ህይወታቸውን ያራዝማሉ::

በአጠቃላይ ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ ድንቅ ድንቅ የአራዊት ፍልሚያ፣ የተፈጥሮ ውበት ፍንትው ብሎ የሚታይበት ምድራዊ ገነት ነው ለማለት እንደሚያስደፍር አብዛኞዎቹ የተመለከቱት እማኝነታቸውን አስፍረዋል::

የክሩገር ፓርክን ለመጐብኘት የቦታና የጊዜ ምቹነቱን፣ ያሉትን ተለዋዋጭ ወቅቶች፣ የዱር አራዊቶቹን እንቅስቃሴ በሚገባ ማወቅ ግድ ይላል:: ይህም የዱር አራዊቱ ከቦታ ቦታ ወይም ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ስለሚንቀሳቀሱ ወይም ስለሚፈልሱ መሆኑን ልብ ይሏል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ፣ ሆምስ አፍሪካ፣ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here