ህገ ወጥ ቀለሞች

0
179

በዚሁ  አምድ ሰኔ ሶስት ቀን 2016  ዓ.ም እትም “የማስታወቂያ ቦታዎችን እንለይ” በሚል ርዕስ ዳንኤል ሙሉጌታ ቅጥ ያጣ የማስታወቂያ አለጣጠፍን በተመለከተ አስነብቦናል:: እርግጥም ጸሐፊው እንዳለው በየአውራ መንገዱ እና በግለሰቦች የግቢ በር ማንም እየተነሳ የሚለጥፋቸው ቅጥ ያጡ ማስታወቂያዎች የከተማን ውበት የሚያጎድፉ፣ የግለሰቦችን መብትም የሚጋፉ ናቸው::   ማስታወቂያዎችን በተመለከተም በሃገራችን የህግ ድንጋጌ ወጥቶለታል:: ከድንጋጌው ውጭ የሆነ አሰራርም ተጠያቂ እንደሚያደርግ ይገልጻል፤ ታዲያ ይህ ሆኖ ሳለ አስፈፃሚ መጥፋቱ ህግ ወጥነቱን ህጋዊ አሰራር አስመስሎታል::

ነሃሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣው የኢፌዲሪ የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004 በአንቀጽ 21 ስለ ውጭ ማስታወቂያ፦

1-  ማንኛውም ሰው አግባብ ካለው የመንግሥት አካል ፈቃድ ሳያገኝ እና እንደ አግባብነቱ ባለቤቱ ወይም ባለ ይዞታው ሳይስማማ፦

ሀ- በማንኛውም ሕንፃ፣ ግድግዳ፣ አጥር፣ የአውቶቡስ ፌርማታ፣ ምሰሶ፣ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሳሪያ ወይም ሌሎች መሰል ነገሮች ላይ፤

ለ- በማንኛውም መንገድ፣ አውራ ጎዳና፣  የባቡር ሀዲድ ወይም የሕዝብ መጓጓዣ ላይ፤ ወይም

ሐ- በማንኛውም የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥ ስፍራ ላይ የውጭ ማስታወቂያ መለጠፍ፣ መስቀል፣ መትከል ወይም በሌላ መንገድ ማስቀመጥ አይቻልም ሲል ይደነግጋል::

በአንቀጽ 36 ተራ ቁጥር ሶስት ላይ ደግሞ ክልሎች የውጭ ማስታወቂያን በሚመለከት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ሊያወጡ ይችላሉ ይላል::

እንዲያው የጸሐፊው ትዝብት የኔም ሆኖ ዘው ብዬ ቅጥ ያጡ ማስታወቂያዎች ላይ ተመስርቸ፤ የጸሐፊው ትዝብት የኔም ድጋፍ እንዳለው ገለጽሁ እንጂ   የዛሬው የኔ ብዕር ትኩረት ማስታወቂያዎች ላይ አይደለም:: ይልቁንስ በየሕንጻዎች ግድግዳ፣ በር እና መስኮት ላይ በቀለም መርጫ ፣ ሌሎች ቀለሞችን በቡርሽ እና ፓርከር ለተለያዬ ተግባር በሚለቀልቁት ላይ የታዘብሁትን ለውድ አንባቢያን እንካችሁ ለማለት እንጂ::

መነሻዬን በቅርቡ በእኔ ላይ የደረሰውን አድርጌአለሁ:: እንደምንም ብዬ /ጥሬ ቆርጥሜ አለማለቴን ይረዱልኝ/ ለመኖሪያ ቤቴ ደረጃውን የጠበቀ የግቢ በር ለመግጠም የበቃሁት በቅርቡ ነው:: ይህም በመሆኑ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ በወጣን በገባን ቁጥር ዓይናችን ትኩረቱን እዚሁ አዲሱ የግቢ በር ላይ አድርጓል:: ከግቢ ውጭም በሩ አካባቢ ቆመን የተመለከተም ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ “የግቢያችሁ በር በጣም ያምራል” ስለሚለን ደስታችን እጥፍ ሆኗል፤ አዲሱ የግቢ በር በሚያስቸረን አድናቆት በጥቂቱም ቢሆን ኮራ፣ ጀነን የሚያስብል ስሜት አድሮብናል::

አዲሱ የግቢ በራችን የህገ ወጦች እጅ እንዳያርፍበትም በየቀኑ የቻልነውን ያህል ጥበቃ እናደርጋለን:: ምናልባት ሳናየው “ዲሽ እንሰራለን፤ አስጠኝ ይፈልጋሉ? የኤሌክትሪክ ምጣድ እንሰራለን፤ ፍሪጅ እንጠግናለን … ሌላም ሌላም አይነት ማስታወቂያዎች ተለጥፈው ስናገኝ ወዲያውኑ ከተለጠፈበት ልጠን እናነሳለን:: ይህ በመሆኑ የግቢ በራችን እስካሁን የህገ ወጥ ማስታወቂያ ለጣፊዎች ሰለባ እንዳይሆን አድርገነዋል::

ህገ ወጥ ቀለሞች የሚል ርዕስ ይዠ ይህን ትዝብት እንድሞነጫጭር ያስቻለኝ መነሻ ድርጊት ደግሞ የተፈጸመው ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር:: ሁላችንም የቤተሰቡ አባላት ቤት ውስጥ እያለን ከቀኑ 8:30 የግቢው በር ተንኳኳ፤ ሴቷ ልጀ  ከፈተች፤ ከበር ላይ ከቆሙ ሰዎች ጋር ረዘም ያለ ቆይታ በማድረጓ የቤቱ እማዎራ /የኔዋ ባለቤት/ የልጇን መዘግየት ምክንያት አድርጋ እሷም ወደ በር አመራች:: ልክ እንደ ልጃችን ሁሉ እሷም ከመጡት እንግዶች ጋር ስትነጋገር ቆይታ ተመለሰች::

ምን ገጥሟችሁ ነው? ብዬ ለባለቤቴ ጥያቄ አቀረብሁ:: “ኧረ ተወዉ! ‘ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል’ አይደል የሚባለው፤ እነዚህ ደግሞ ሞፈር ባይቆርጡም ቀለም ሊቀቡኝ! አለማፈራቸው” አለች::

የምን ቀለም ነው ደግሞ የሚቀቡሽ በማለት ተከታይ ጥያቄ አቀረብሁላት፡፡ “ከጤና ጣቢያ ነው የመጣን፤ ከአምስት ዓመት በታች ልጅ እዚህ ግቢ አለ ብለው ጠየቁኝ:: ህጋዊ መረጃ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን አረጋግጨ፤ የለም ብዬ መለስሁላቸው:: ከሶስቱ መረጃ ሰብሳቢዎች መካከል አንደኛው ቀለሙን ይዞ ወደ በሬ እጁን ሰነዘረ:: በህግ አምላክ! ምንም ነገር መጻፍ አይቻልም አልሁት:: እንዴት? ተከራከረኝ፤ እንደማይሆን አስረግጨ ነገርሁት:: እያጉረመረመ ወደ ቀጣዩ የጎረቤት ቤት አመሩ:: ከኔ ጋር የነበራቸው ቆይታ በዚሁ ተጠናቀቀ አለች” ባለቤት በመገረም::

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ከግቢ ወጥቼ ፍቅሬ ካልተለየው የግቢ በሬ ላይ ዓይኔ ትኩረት አደረገ:: በሩ በቀለም ዳክሯል፤ በጣም ተናደድሁ:: ምን ይሆናል ትናንት የመጡት መረጃ ሰብሳቢ ነን ባዮች ህገ ወጥ ቀለማቸውን በሬ ላይ አሳርፈው ለመሄዳቸው እርግጠኛ ነበርሁ::

ባለቤቴን ጠርቼ፤ አየሽ! እነዚያ መረጃ ሰብሳቢ ነን ባዮች በሬን ቀቡት እኮ! የአንችን ወደ ግቢ መግባት አይተው ህገ ወጥ ቀለማቸውን፤ በህጋዊው የግቢ በሬ ላይ ለቅልቀው ሄደዋል አልሁ:: አሷም አይሆንም ያልሁት፤ በህገ ወጦች ተፈፀመ! ብላ በጣም ተናደደች:: በቃ! ተይው አንዴ ሆኗል ብዬ ቀለሙን ለማስለቀቅ ሞከርን፤ አልተቻለም:: የህገ ወጥ ቀለሞች አሻራ በእኔ በር ላይም አረፈ::

በባህር ዳር ከተማ ህገ ወጥ ቀለሞች በንግድ ሱቆች እና መኖሪያ ቤቶች በር ላይ በየጊዜው ይለቀለቃሉ:: ቀለም ለቅላቂዎች ደግሞ አንደ ህገ ወጥ ማስታወቂያ ለጣፊዎች የማይታወቁ ግለሰቦች አይደሉም:: ከመንግሥት ተቋማት የመጣን ነን የሚሉ ህጋዊ ተልዕኮ ይዘው ህገ ወጥ ተግባር ፈፃሚ ናቸው::

በባህር ዳር ከተማ የሚከናወነው ንግድ ህጋዊ ሆኖ መፈጸም ይችል ዘንድ፤ የንግድ ፈቃድ ያለውና የሌለውን መለየት እንዲችሉ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ መምሪያ ባለሙያዎችን ያሰማራል:: ባለሙያዎቹ ተዘዋዉረው ሲያረጋግጡ፤ የታየ እና ያልታየውን መለያ በሚል የያዙትን ቀለም በቡርሻቸው እያጠቀሱ የንግድ ቤቶችን ቀለም በቀለም ያደርጓቸዋል::

መቸ በዚህ ያበቃል:: የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ጽ/ቤትም ግብር የከፈለ እና ያልከፈለውን ለዩልኝ ብሎ ያሰማራቸው ባለሙያዎችም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም የንግድ ሱቆችን ቀለም በቀለም ያደርጓቸዋል::

የምነግድበት ሱቅ ይህን አይነት ቀለም ቢቀባ መልካም ነው ብሎ ባለቤቱ ያሳመረው ግድግዳ አልያም በር እንግዲህ በዚህ መልኩ በህገ ወጥ ቀለሞች እየተዥጎረጎረ ውበቱን ሲያጣ መመልከት በባህር ዳር የተለመደ ሆኗል::

በተለያዬ ምክንያት መረጃ ለመሰብሰብ ከከሌ መስሪያ ቤት የተላክን ነን ባዮችም በከተማዋ መኖሪያ ቤቶች እየዞሩ ተመሳሳይ ህገ ወጥ ቀለሞችን በግለሰቦች ቤት ላይ ይለቀልቃሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሃይ ባይ በመጥፋቱ ህገ ወጡ ድርጊት ህጋዊ መስሎ ይፈጸማል::

በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ሃገራችን ማስታወቂያዎች እንዴት ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ህግ ደንግጋለች:: የክልል መንግስታትም ለህጉ ተፈጻሚነት መመሪያ እና ደንቦችን ማውጣት አንደሚችሉ ህጉ ላይ ሰፍሯል:: ይሁን እንጂ በተለይ በባህር ዳር ከተማ ህገ ወጥ ማስታወቂያ ለጣፊዎችን እና ቀለም ለቅላቂዎችን ሃይ የሚል ጠፍቷል:: ይህም  የውቢቱን ባህር ዳር ውበት የሚያጎድፍ እና የግለሰቦችን መብት የሚጋፋ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እላለሁ:: እኔ ይህን ታዘብሁ:: እናንተም የታዘባችሁትን እንድታካፍሉን እየጋበዝሁ በዚሁ አበቃሁ፡፡

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here