ቀውሱ አሁንም እንዳይቀጥል ንግግሩ ይጀመር!

0
128

ቀውስ፣ ሁከት፣ ግጭት፣ ጦርነት ካለ ልማት ይቅርና በሕይዎት መኖርም ከባድ መሆኑን እኛ በዚህ ወቅት የምንኖር ሁሉ የምንረዳው እና የምንኖረው ሀቅ ነው። ከልማትም ሆነ ከሌላ መልካም ሥራዎች ሁሉ የሚቀድመው ሠላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ካለሠላም  ልማት  በተበሳ እንስራ ላይ ውኃ እንደማጠራቀም አይነት ተግባር ነው። ሠላም ከሌለ መስራት ይስተጓጐላል፣ የተሠራው ይፈርሳል። የተመረተው አይሸጥም፣ የተሸጠውም ይነጠቃል።

ባለፉት ወራት ውስጥ የተመረተው ምርት በአንዳንድ አካባቢዎች ገበያ ሳይደርስ ተበላሽቷል።። መንገዶች ዝግ በመሆናቸው  ሻጭ እና ገዥም ለመገናኘት   ተቸግረው ታይተዋል። በገበያው ብቻ ሳይሆን ወላድ እናቶች ሳይቀሩ ሕክምና ለመድረስ ፈተና ውስጥ ወድቀው ባጅተዋል። ነግቶ እስኪመሽ፣ መሽቶም እስኪነጋ ውሎ ለማደር  እርግጠኛ መሆን አዳግቶ ነበር። የተኩስ ድምፅ እንደተራራ ላይ ናዳ ከየት መጣ ሳይባል ደርሶ ይፈነዳል።  በዚህ ምክንያት ዘመድ ከዘመዱ፣ ሠራተኛ ከሥራ ቦታው ለመገናኘት ችግር ሆኖ ባጅቷል። በዚህ ላይ ከመሬት ተነስቶ ፍረጃው ከባድ ነው። አንተ እንዲህ ነህ፣ አንቺ እንዲያነሽ በሚል በርካታ ተስፈኛዎች ሕይዎታቸውን ተነጥቀዋል። በፍረጃ ምክንያት የተገለሉ፣ የተሰደዱ እና የተገደሉ ጥቂቶች አይደሉም። ማህበረሰባዊ ትምምኑ (Trustship) ላልቷል።

የትምምን መላላቱ ግለሰብ ከግለሰብ፣ መንግሥት ከሕዝብ፣ ተቋም  ከተቋም ሁሉ ያለ ነው።  ያለትምምን ሰላም፣ ዕድገት እና ልማት  ሊረጋገጥ አይችልም። ትምምን ለማምጣት ደግሞ ሰጥቶ መቀበልን መርሕ ያደረገ ሃቀኛ እና አካታች ንግግር እና ድርድር አስፈላጊ ነው። ንግግር እና ድርድር የመሣሪያ ድምፅን ከማቆሙ በላይ ለትምምን፣ ለአብሮነት እና ለዘላቂ ሰላም ማዕከል ነው። አንድ ቀን ከመታኮስ ብዙ ዓመታትን መወያየት ውድመትን ያስቀራል።  ከልብ፣ ከቅንነት፣ የሕዝብን ፍላጎት  መሠረት ያደረገ ድርድር ካልተጀመረ ቀውሱ እየቀጠለ፣ ፍረጃው እየከረረ፣ ጡዘት ላይ ደርሶ ሀገር እና ሕዝብም አንገት እየደፉ መሄዳቸው የማይቀር ይሆናል።

ይህ ፀረ ሰው ቀውስ እንዲቋጭ ከጦርነት ንግግር፣ ከውጊያ ድርድር፣ ከተኩስ ውይይት ሊቀደም ይገባል። አባት እና ልጅ በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው የሚዋጉበትን አሳዛኝ  ክስተት ለመቀልበስ  ሃቀኛ የንግግር መስኮት ተከፍቶ  ይቅረብ፡፡ ለዚህም ሁሉም ወገን  ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ተነሳሽነትን መውሰድ ይገባዋል፡፡ ግጭቱ አብሮን ባጅቶ አብሮን ከርሞ በጋውንም አብሮን ከቀጠለ ሰባዊ እና ቁሳዊ ኪሳራው ተጨማምሮ ዳግም ለማንሰራራት እንኳን  አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሰላምን  ለማምጣት የሚቀድም ምንም አይነት ተግባር የለም፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የሰላም መሠረቱ በንግግር እና በድርድር እንዲጸና ሁሉን አቀፍ እና አካታች ርብርብን ወቅቱ ይጠይቃል፡፡

 

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here