በየጊዜው የሚቀያየረው የመንግሥታት ሥርዓት በሕዝብ ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን ፈጥኖ ባልመለሰበት ሁኔታ የክልል ልዩ ኀይል መዋቅርን በማፍረስ በክልል፣ በፌዴራል እና በመከላከያ የጸጥታ መዋቅሮች ውስጥ እንዲካተት መደረጉ የአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ በተሻገር የጸጥታ ቀውስ ውስጥ እንዲያልፍ ሆኗል:: የተፈጠረውን የሰላም መናጋት በአጭር ጊዜ በመቀልበስ ክልሉን ወደ ቀደመ የሰላም ሁኔታው ለመመለስ በክልሉ መንግሥት ይሁንታ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተደርጓል:: በዚህም ክልሉ እስከ ሰኔ ወር 2016 መጀመሪያ አሥር ወራትን ባስቆጠረ ይፋዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጓል::
ክልሉ ምንም እንኳ በኮማንድ ፖስት ሥር ቢተዳደርም አሁንም ድረስ አንጻራዊ እንጅ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዳልቻለ የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል:: እልባት ሳያገኝ አንድ ዓመትን የተሻገረው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ለበርካታ ሰብዓዊ ጉዳት፣ ለማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ ለምጣኔ ሐብታዊ ድቀት… ዳርጎታል::
የክልሉ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ግጭቱ በተቋማት ላይ ብቻ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንዳደረሰ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወርሀ ሚዚያ ማስታወቁ አይዘነጋም:: አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ ያላገኘው ግጭት ከዚህ በላይ ጉዳት አድርሶ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል::
በዓመቱ ያጋጠመው የሰላም መናጋት አርሶ አደሩ ከበጋ እስከ ክረም ባልተቋረጠ ማምረት ውስጥ ሆኖ በምግብ ራሱን እንዳይችል፣ ገበያ አጥግቦ እንዳይጠግብ እክል መፍጠሩ በተለያዩ የሰላም የውይይት መድረኮች ተነስቷል:: ለችግሩ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉም የግብርና ግብዓት በወቅቱ እና በሚፈለገው መጠን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ ፈተና መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ እና አርሶ አደሮች በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል::
በዓመቱ መማር ማስተማር ተስተጓጉሏል፤ የጤና ሥርዓቱ እና አገልግሎት አሰጣጡ ተፈትኗል፤ እንደ ኮሌራ እና ወባ ያሉ የማኅበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመቆጣጠር በዓመቱ ያጋጠመው የጸጥታ መታወክ ፈተና ሆኖም ይነሳል:: የሰላም ችግሩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴን መገደቡን ተከትሎ ማኅበራዊ መስተጋብሩ ላልቶ መቆየቱም አይዘነጋም:: የአማራ ሕዝብ ነባር እሴቶች ተሸርሽረዋል::
የጸጥታ መታወኩ በክልሉ ሕዝብ እና የልማት እንቅስቃሴ ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ እና የቀጣይ የእልባት መንገዱ ከግለሰብ እስከ ክልል ምክር ቤት ትኩረትን አግኝቷል:: በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የመንገድ ግንባታ ሥራውን ስለመፈተኑም ይገለጻል:: ለአብነት በሰሜን ጎጃም ዞን ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸው ግንባታ ላይ የነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መቋረጣቸውን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ለአሚኮ ገልጸዋል:: ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገርላቸው እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ቀውስ መቋረጣቸው ዞኑን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረገው አስታውቀዋል::
ከአዴት ከተማ – ሰከላ – ፈረስ ቤት የሚያገናኘው 62 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መቆሙን ዋና አሥተዳዳሪው ለአብነት አንስተዋል:: ከዱር ቤቴ – ሻውራ – ደለጎ መተማ ዮሐንስን የሚያገናኘው 260 ኪሎ ሜትር መንገድም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መቆሙን አቶ አሰፋ አስታውቀዋል::
በመንገድ ግንባታዎቹ መቆም ምክንያት በግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ ሠራተኞች እና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወገኖች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም ተመላክቷል:: በመሆኑም በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ግጭቱ በክልሉ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ በመረዳት ልዩነቶቻቸውን በድርድር መፍታትን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል::
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሐምሌ 22 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት መነጋገሪያ የነበረውም የክልሉ የሰላም ጉዳይ ነው:: ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ የክልሉን አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በዓመቱ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ሕዝብ እና ልማት ላይ ያደረሰውን ጫና ጠቁመዋል:: በክልሉ 10 ሺህ 874 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ:: በዓመቱ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያለፉት 6 ሺህ 588 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው::
ስድስት ሚሊዮን 292 ሺህ 241 ተማሪዎችን በመመዝገብ ማስተማር የ2016 ዓ.ም ዕቅድም ነበር:: ይሁን እንጂ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ሦስት ሚሊዮን 705 ሺህ 539 ተማሪዎች ብቻ እንደሆኑ ከርእሰ መስተዳደሩ ሪፖርት መረዳት ተችሏል:: በአጠቃላይ በዓመቱ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ 4 ሺህ 286 ትምህርት ቤቶች እና 2 ሚሊዮን 586 ሺህ 702 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል::
ለክልሉ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት 3 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር አበርክቶ እንዳለው የሚነገርለት የጤና ዘርፉም በዓመቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ክፉኛ መፈተኑንም ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል::
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በክልሉ ላለፈው አንድ ዓመት የዘለቀው ግጭት የክልሉ ሕዝብ ነባር እና ክቡር እሴት እንዲሸረሸር ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል::
መጠነ ሰፊ ጥፋት እያስከተለ ያለውን ቀውስ ማክሰም ደግሞ አሁናዊ የትኩረት አጀንዳ ሊሆን ይገባል:: በእርግጥ የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት የቀጣይ ዋና ትኩረት የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ ተመላክቷል:: አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ድርድር ምርጫ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል::
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከአባላቱ በስፋት የተነሱ ሐሳቦች ከሰላም እና መልማት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል:: በክልሉ የተፈጠረው ግጭት አሁናዊ አሰላለፍ ለክልሉ አንድነት አደገኛ መሆኑንም ጠቁመዋል:: ውስጣዊ የሕዝብ አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮች መፈጠራቸውን የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ በሕዝብ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ጥያቄ ስም የክልሉን አንድነት ለመሸርሸር የሚመጡ ኀይሎችን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል::
የክልሉ መንግሥት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን፣ ካውንስሉም ያቀረበውን ጥያቄ መንግሥት መቀበሉን ገልጸዋል:: ነገር ግን “የታጠቁ ኀይሎች መንግሥት ለሚፈልገው ውይይት እና ሕዝብ ለሚጠይቀው ሰላም ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል” ማለታቸውን አንስተዋል:: ያም ሆኖ መንግሥት አሁንም የሰላም ችግር ዘላቂ መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ ለሰላማዊ ውይይት እና ንግግር ቁርጠኛ መሆኑን በግልጽ ጠቁመዋል::
የሰላም ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከመሥራት ጎን ለጎን የክልሉ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት እና ሕልውና እንዲከበር፣ ከድህነት እንዲወጣ እና የመልማት ጥያቄው እንዲመለስ እየተሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ እንደሆነ አስታውቀዋል::
ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ተከትሎ የሚፈጠረው የሰላም መናጋት ዜጎችን ለከፋ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ከመዳረግም ባለፈ የሀገርን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት በእጅጉ ይገድባል:: ይህንን የተረዱ በግጭት ውስጥ ያለፉ ሀገራትም ልዩነቶቻቸውን በድርድር እና በንግግር ፈተዋል::
ልዩነቶችን በሰላማዊ ምክክር እና ድርድር መቋጨት የጥል ምክንያቶች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችላል:: የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት የሚያስገኘውን ውጤት በምክክር ሂደት ሰላማቸውን ካረጋገጡ ሀገራት ያገኘውን መረጃ አጋርቷል::
ምክክር የፓለቲካ ሥርዓት ማሻሻያ ለማድረግ በር ይከፍታል:: ምክክሩ የፓለቲካ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ሲያቀርብ ሀገራት የቀረቡትን ምክረ ሀሳቦች መሰረት ባደረገ መልኩ አዳዲስ የፓለቲካ አስተሳሰቦችን፣ አሰላለፎችን ብሎም መዋቅሮችን አስተናግደዋል:: ሀገራዊ ምክክር ከሚያስገኛቸው ውጤቶች አንዱ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ነው::
በሂደቱ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ሀገራቱ ሕገ መንግሥቶቻቸውን ሽረው በአዲስ መልክ መቅረፅን ጨምሮ በተመረጡ አንዳንድ አንቀጾች ላይ ማሻሻያዎችን አድርገዋል:: ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ለውጦች እንዲደረጉ እና የጥል መንገዱ እንዲያጥር ምክክር ወሳኝነት ይኖረዋል:: በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች በምክክር እንዲታዩ ዕድልን በመፍጠር የእልባት መንገድ ተግባራዊ ርምጃዎች እንዲወሰዱ እና መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል::
በሕይወት የመኖር እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጨምሮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶችን ማስጠበቅ የሀገራዊ ምክክር ተጠቃሽ ውጤት ሆኖ በተሞክሮ ካለፉ ሀገራት ተወስዷል::
በግጭት ውስጥ የቆዩ የተለያዩ ጎራዎች (አካላት) ስላሳለፉት የግጭት እና የቅራኔ ኩነቶች በግልፅ ተነጋግረው ወደ መፍትሔ መሄዳቸው ነው:: የተለያዩ ሀገራት በሂደቱ የተፈጠሩ ጉዳቶች እና በደሎች መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገዶች በማመቻቸት፣ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ዘላቂ እና ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዲመሰረት ማስቻላቸው ልዩነቶችን በውይይት የመፍታትን ኃያልነት በግልጽ ያሳየ ሆኖ ይወሰዳል:: በመሆኑም ኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያጋጠሟትን የሰላም መናጋቶች በሀገራዊ ምክክር በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብሎ በመነጋገር የልዩነት ምክንያቶችን ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ለዜጎች የተመቸች ማድረግ ላይ ሁሉም ሊተባበር ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም