የመጪው ዘመን ፈርጥ

0
169

ከ68 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ከተሳተፈችባቸው የአትሌቲክስ ዘርፎች መካከል የ800 ሜትር ርቀት አንዱ ነበር። ምንም እንኳ በወቅቱ ሀገራችን ውጤት ባይቀናትም በርቀቱ ወንድ አትሌቶች መሳተፋቸውን ታሪክ ያወሳል።

እ.አ.አ በ1980 በተከናወነው የሞስኮ ኦሎምፒክ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች የተሳተፉበት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። በ800 እና 1500 ሜትር ርቀት እንደተሳተፉም መረጃው ይነግረናል። በ800 ሜትር ርቀት ፈንታዬ ሲራክ መሳተፏን በታሪክ ተመዝግቧል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት የተለያዩ ኦሎምፒያዶች በሁለቱም ፆታዎች ሀገራችን በ800 ሜትር ርቀት ብትሳተፍም አሜሪካውያንን፣ ጃማይካውያንን፣ ደቡብ አፍሪካውያንን እና ሌሎችንም ሀገራት በመብለጥ ሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ መግባት ሳትችል ቆይታለች።

በወንዶች ሙሀመድ አማን በርቀቱ በዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ቢችልም በተሳተፈባቸው የኦሎምፒክ ውድድሮች ግን ማጣሪያውን እንኳ ማለፍ አልቻለም። በተመሳሳይ በዚህ ርቀት ስትሳተፍ የምናውቃት ሀብታም ዓለሙም በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮናው ስኬታማ መሆን አልቻለችም።

ዘንድሮ ግን ይህ እርግማን ተነስቶ በፓሪሱ ኦሎምፒክ አዲስ ውጤት ተመዝግቧል።   እርግማኑን በመስበር የብር ሜዳሊያ ያሸነፈችው አትሌት ደግሞ ፅጌ ዱጉማ ነች። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ የተገኘችው አትሌት ጽጌ፤ ገና ወጣት መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ የአልሸነፍ ባይነት እና ወኔዋ ከወዲሁ ብዙ ርቀት እንደምትጓዝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አትሌት ፅጌ ዱጉማ ውልደቷ እና እድገቷ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን ነው። በልጅነቷ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ እና ሌሎችንም ስፖርቶች ታዝወትር እንደነበረ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ዋቢ አድርጎ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ድረገጽ መረጃ ያስነብባል።

በትምህርት ቤት፣ በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አቅሟን አጎልብታለች። ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ባለተሰጥኦዋ አትሌት፤ አምስት እህቶች እና አንድ ወንድም አላት። አባቷን በልጅነቷ በሞት በማጣቷ ከእናቷ ላለመለየት የአትሌቲክስ ስፖርቱን ችላ ብዬው ነበር ብላው እንደነበር ተናግራለች።

“ትምህርት ቤት እንኳ ከእናቴ ርቄ መሄድ አልፈልግም፤ ነገር ግን አስገዳጅ ነገር ስለገጠመኝ ወደ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ተቀላቀልኩ። በወንድሜ አበረታች እና ጎትጓችነት ነበር አካዳሚ የገባሁት።  ሁሉም እህቶቼ ትዳር ይዘው ከቤት ስለወጡ እናቴን ለብቻ መተውን  አልተስማማሁም ነበር፤ ወንድሜ በሩጫው እንድበረታ  ያግዘኛል፤  ይገፋፋኛል። በአሰላ የሚገኝውን የጥሩነሽ ዲባባን አካዳሚ ካልተቀላቀልኩ ድጋሚ እንደማያናግረኝ ስረዳ  ተቀላቀልኩ” ፅጌ በዚህ መንገድ ከትውልድ መንድሯ ወጥታ  የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን  እንደተቀላቀለች ድረ ገጹ ያስነብበናል ።

በ2009 ዓ.ም የአትሌቲክስ አቅሟን እና ክህሎቷን ለማጎልበት በተለይ አጭር ርቀት ላይ ትኩረት በማድረግ ስልጠና መጀመሯን የታሪክ ማህደሯ ያሳያል። በዚሁ ዓመት በአልጀሪያ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ በተሳተፈችበት 200 ሜትር ርቀት የብር ሜዳሊያ ማሸነፍ ችላለች። በ2011 ዓ.ም  ደግሞ  ወደ 400 ሜትር ርቀት ፊቷን በማዞር ብቃቷን አሳይታለች።

በ2014 ዓ.ም ይካቲት ወር ላይ በሀዋሳ ከተማ በተደረገው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ400 ሜትር ማሸነፏም የሚታወስ ነው።  ጽጌ ዱጉማ በአጠቃላይ ከ100 ሜትር እስከ 400 ሜትር ርቀት አምስት ዓመታት ያህል አሳልፋለች። በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ወደ 800 ሜትር ርቀት በመሸጋገር አስደናቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።

ባሳለፍነው የ2015 የውድድር ዘመን በቤልጂየም በተደረገ ውድድር የመጀመሪያዋን ዓለም አቀፍ ውድድሯን ስታሸንፍ የግሏን ምርጥ ስዓት በማስመዝገብ ጭምር ነበር። ከአምስት ወራት በፊትም በስኮትላንድ ግላስኮ በተደረገው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ውድድር በበላይነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም።

አትሌቷ በማጣሪያው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር የራሷን ስዓት በማሻሻል ጭምር ነበር ወደ ፍጻሜ ተሸጋግራ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈችው። አትሌቷ በ800 ሜትር ርቀት በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትም መሆን ችላለች። በዘንድሮው የአፍሪካ ጨዋታዎች በተወዳደረችበት 800 ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

በረጅም ርቀት የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የሆኑ ሀገራት ጭምር እምብዛም ውጤታማ በማይሆኑበት በዚህ የውድድር መድረክ፤ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠንካራ ተፎካካሪ እየሆኑ መጥተዋል።ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፓሪሱ ኦሎምፒያድ በመካከለኛ ርቀት ያላትን አቅም በግልጽ ያሳየችበት ሆኖ አልፈል።

ሀገራችን በረጅም ርቀት ብቻ ሳይሆን በመካከለኛ ርቀትም ትልቅ አቅም እንዳላት አትሌት ፅጌ ዱጉማ በ33ኛው የፓሪሱ ኦሎምፒያድ አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን በአጭር እና በመካከለኛ ርቀት ተፎካካሪ መሆን አይችሉም የሚለውን እሳቤ እና ግምትም ፉርሽ አድርጋለች። የመጪው ዘመን ኮከቧ አትሌት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የኦሎምፒክ መድረክ በ800 ሜትር ርቀት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበታ ጊዜ አንድ ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ክ90 ማይክሮ ሴኮንድ ነው።

የታላቋ ብሪታኒያ አትሌት ኬሊ ሆጅኪንስ በበላይነት ባጠናቀቀችበት ፉክክር ኬኒያዊቷ ሜሪ ሞራ ደግሞ ሦስተኛ ሆና መጨረሷ አይዘነጋም። ወጣቷ ባለተሰጥኦ ኢትዮጵዊት በርቀቱ ሀገራችንን ለመጀመሪያ ጊዜ የሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ አስገብታታለች።

ባሳለፍነው ዓመት በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና የፀረ አበረታች መድሀኒት ምርመራውን ባለማለፏ በውድድሩ አለመካፈሏን የኦሎምፒክ ድረገጽ መረጃ አስነብቧል። ታዲያ በትልቅ የዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሯን በመወከል እና ሰንደቅ አለማዋን ከፍ ለማድረግ ጊዜን ስትጠብቅ ነበር። እንሆ ከአንድ ዓመት በኋላ ዘንድሮ ወርቃማውን የኦሎምፒክ አጋጣሚ በመጠቀም ታሪክ ሠርታለች።

በመካከለኛ ርቀት ውጤታማነት በኢትዮጵያ ያልተለመደ ቢሆንም አቅሙ እንዳለ ግን ፅጌ ዱጉማ ማሳያ ነች። ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለያዩ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ያሉ ታዳጊ እና ወጣት አትሌቶች በርቀቱ ተሳታፊ ቢሆኑም ለውጤታማነት የእነሱ ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ከጠንካራ ስራ ባለፈ ፌዴሬሽኑም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘችው ጽጌ ሥፍራው በርካታ ተተኪ አትሌቶች ሊወጡ የሚችሉበት በመሆኑ ባለሙያዎች አካባቢውን ተደራሽ ማድረግ ይገባቸዋል። በክልሉ  በወምበርማ ወረዳ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ያለ ቢሆንም እሷ በተወለደችበት የካማሽ ዞን ግን ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን መክፈት አስፈላጊ መሆኑን በቃለ መጠይቋ መናገሯ የሚታወስ ነው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here