በሰዓታት ለሞት የሚዳርገዉ

0
244

እንደ ዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ  ኮሌራ  ቫይብሮ ኮሌራ በተባለ ተዋሲ አማካኝነት  አንጀትን የሚያጠቃ በሽታ ነው። በሽታው በዚህ ተዋሲ  በተበከለ ምግብ እና ውኃ አማካኝነት ይከሰታል::  በድንገት የሚጀምር አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ምልክቶቹ ናቸው።  የሰውነት ፈሳሽን በማሟጠጥ አቅም ስለሚያሳጣ ተገቢው ህክምና ካልተደረገ በጥቂት ስዓታት ውስጥ ለሞት እንደሚዳርግም መረጃው አመላክቷል::

ባደጉት ሀገራት ውኃን በዘመናዊ መንገድ አጣርተው ስለሚጠቀሙ  የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ተችሏል:: ይሁን እንጂ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት  በድህነት፣ በንጽሕና ጉድለት፣ በጦርነት፣ በስደት እና በተፈጥሮአዊ አደጋዎች ምክንያት ኮሌራ በተደጋጋሚ ይከሰታል:: ለአብነት አፍሪካ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ  ተጠቃሽ ናቸው::

ኮሌራ በሽታ በተያዘው ዓመት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል:: እስከ ሀምሌ 30/2016 ዓ.ም ድረስ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሰዎች መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል::

ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች የተበከለ ውኃ መጠጣት፣ የተበከለ ምግብ መመገብ፣ የግል እና አካባቢ ንጽሕና ጉድለት፣ ሜዳ ላይ መጸዳዳት፣ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም እንደሆኑ የገለፁት የኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ ናቸው::

ባለሙያዋ እንዳሉት  ኮሌራ ከመጋቢት 27/2016 ዓ.ም በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር  ሦስት ወረዳዎች ነበር:: በመቀጠል አጎራባች በሆኑት በደቡብ ወሎ ዞን ሁለት ወረዳዎች፣ በኮምቦልቻ እና በደሴ ከተሞች እንዲሁም በሰሜን ጎጃም ባሕርዳር ዙሪያ   እና ይልማና ዴንሳ ወረዳዎች መስፋፋቱን  አረጋግጠዋል::

ከሰኔ 5ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ጎንደር ከተማ መከሰቱን ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: በሽታው አድማሱን በፍጥነት በማስፋት በማዕከላዊ ጎንደር ሰባት ወረዳዎች ፣ በምዕራብ ጎንደር ሁለት ወረዳዎች፣ በደቡብ ጎንደር አራት ወረዳዎች፣ በምሥራቅ ጎጃም አንድ ወረዳ፣ በሰሜን ጎንደር አንድ ወረዳ፣ በምዕራብ ጎጃም ሁለት ወረዳዎች፣ በወልይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አራት ወረዳዎች፣ በሰሜን ወሎ አንድ ወረዳ እንዲሁም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አንድ ወረዳ ተከስቷል:: በክልሉ አጠቃላይ በ32 ወረዳዎች የተከሰተው ኮሌራ ለ30 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል::

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ከ32 ወረዳ በስምንቱ  ላይ በሽታውን መቆጣጠር ተችሏል:: ቀሪ 24 ወረዳዎች በተለይ ማዕከላዊ ጎንደር፣  ሰሜን ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ስርጭቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል::

በሽታው በዋናነት ተቅማጥ እና ማስመለስ ምልክቶቹ እንደሆኑ ባለሙያዋ አስገንዝበዋል:: ኅብረተሰቡ እነዚህን የህመም ምልክቶች ከታዩበት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መታከም እንዳለበት ባለሙያዋ መክረዋል::  ከባድ የሆነ የኮሌራ ህመም የያዛቸው ሰዎች የሩዝ ውኃ የመሰለ አጣዳፊ ተቅማጥ ይከሰትባቸዋል። ተቅማጡ ህመም የሌለው/ማያስምጥ/እንደሆነ   ሲስተር ሰፊ ጠቁመዋል:: ተቅማጥ እና ትውከቱ ቀጣይነት ያለው ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ የሰውነት ፈሳሽ እና ንጥረ ነገር መሟጠጥ ስለሚኖር በአጭር ጊዜ ሞት ሊያስከትል ይችላል::

በመጀመሪያዎቹ በሽታው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከቀበሌ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር እንደተቻለ ባለሙያዋ ገልጸዋል:: ይሁን እንጅ ኮሌራ የሚተላለፈው በኮሌራ ባክቴሪያ የተበከለ ውኃ ስንጠጣ ወይም ስንመገብ ቢሆንም  የውኃ እጥረት እና የንፅህና ጉድለት ባለባቸው ቦታዎች የመከሰቱ እና የመዛመት እድሉም ሰፊ እንደሆነ ሲስተር ሰፊ አብራርተዋል።

ባለሙያዋ እንደሚሉት ባሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር 26 የሕክምና ማዕከላትን በማቋቋም፣ የጤና ባለሙያዎችን በማሠማራት፣ ግብዓት በማሟላት፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን/ሚዲያዎች/ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶችን በማስተላለፍ እና በአጠቃላይ ቅንጅታዊ አሠራርን በመከተል ርብርብ እየተደረገ ነው::

በሽታው በዋናነት ከተበከለ ውኃ እና ምግብ ባለፈ  ከሕመምተኛ ወደ ጤነኛ ሰው በንክኪ እንደሚተላለፍም ሲስተር ሰፊ አስገንዝበዋል:: ኅብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ/እጅን ምግብ ከማብሰል በፊት፣ ልጆችን ከመመገብ በፊት፣ መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ (ወይም ልጆች መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ)፣ ኮሌራ የታመመን ሰው ከነኩ በኋላ በሳሙና እና በንፁህ ውኃ መታጠብ ዋናው የመከላከያ ዘዴ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል::

“ለመመገቢያም ሆነ ለመታጠቢያ ንፁህ ውኃ መጠቀም የግድ ነው:: የውኃው ደህንነት የተጠበቀ ላይሆን ይችላል ብለው የሚያስቡ ከሆነ ደግሞ የውኃ ማከሚያ ኬሚካሎችን መጠቀም፣  ማከሚያ ምርቱ ከሌለ ደግሞ ማፍላት ውኃን አስተማማኝ ለማድረግ ውጤታማ መንገድ ነው።  ውኃውን ለአንድ ደቂቃ ያህል በማፍላት በንፁህ እቃ አጠራቅሞ ለ24 ሰዓታት ብቻ ጥቅም ላይ በማዋል በሽታውን በቀላሉ መከላከል እና መቆጣጠር ይቻላል” በማለት ሲስተር ሰፊ  ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል::

እንደ ውኃ ሁሉ ምግብን በደንብ አብስሎ እና  በትኩሱ መመገብ፣ የመፀዳጃ ቤት ንፅህናን መጠበቅ፣  ባክቴሪያው እንዳይሰራጭ ለመከላከል ከታመሙ እና ከሌሎች ሰዎች የሚወጣ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ እና ቆሻሻ አካባቢን፣ ውኃን እና ምግብን እንዳይበክል በጥንቃቄ ማስወገድ እንደሚገባም ነው ባለሙያዋ ያሳሰቡት።  የሞተ ሰው በቀላሉ በሽታውን ስለሚያስተላልፍ ከንክኪ መራቅ እና የጤና ባለሙያ እርዳታን መጠየቅ   ተገቢ እንደሆነም  መክረዋል::

ከዚህ ባለፈ የበሽታው ምልክቶች ከታዩ በአካባቢ በሚገኙ ጤና ተቋማት በመሄድ የባለሙያ ድጋፍ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ወሳኝ እንደሆነም ነው  ሲስተር ሰፊ ያስገነዘቡት::  ወደ ጤና ተቋም እስኪደርሱ ደግሞ ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው እና ስድስት የሻይ ማንኪያ ስኳር በመበጥበጥ መስጠት ይገባል::

በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት ባይኖሩ እና ለሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ማድረስ ባይቻል በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነጻ የስልክ መስመር 6981 በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻል አሊያም 24 ሰዓት የባለሙያ ምክር ማግኘት እንደሚቻል ባለሙያዋ አስገንዝበዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here