አውሮኘላን ጎታቹ ባለክብረወሰን

0
130

ጣሊያናዊዉ ሦስት አውሮኘላኖችን በገመድ አቆራኝቶ ወገቡ ላይ አስሮ እግሮቹን ሽቅብ ሰቅሎ በእጆቹ አስፋልት ላይ እየተራመደ አምስት ሜትር በመጐተቱ ለዓለም ክብረወሰን መብቃቱን ዩፒአይ ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል::

ማቲዮ ፓቮኒ የተሰኘው ጣሊያናዊ በካስቴልኖቮ ዶን ቦስኮ እጆቹን እንደ እግር ተጠቅሞ ወይም ተገልብጦ በመራመድ ሦስት ቀላል አውሮኘላኖችን በገመድ አቆራኝቶ ወገቡ ላይ አስሮ በመጐተት ክብረወሰን መስበር ችሏል::

ራሱን “በእጆቹ የሚቆመው ተሽከርካሪ” ሲል የገለፀው ማቲዮ በሚያስደንቅ ጥንካሬ ክብደታቸው ከ5,669 ኪሎ ግራም የሚበልጥ አውሮኘላኖችን አምስት ሜትር ርዝመት በመጐተት ተሳክቶለታል::

ማቲዮ – ከከበቡት አድናቂዎች እና ጎደኞቹ በተደረገለት የሞራል ድጋፍ ተጨማሪ አራተኛ አውሮኘላን አቆራኝቶ ለመጐተት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል::

ማቲዮ ለሦስተኛ ጊዜ ያደረገው ሙከራም ባለመሣካቱ መሬት ላይ ተዘርሮ እንደተኛ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን አሳልፏል:: ያንጊዜ እንደተኛ በእልህ ሌላ ጊዜ ለማሳካት ጥረቱን እንደማያቆም በውስጡ እያሰበ እንደነበር ነው ሲጠየቅ መልስ የሰጠው::

ጥቂት ቆይቶ የድንቃድንቅ ክብረ ወሰን መዝጋቢ ባለሙያዎች በተኛበት ከላይ ወደታች እየተመለከቱት በመጀመሪያው ሙከራ የዓለም ክብረወሰን መስበሩን ነገሩት:: የሰማውን ለማመን ቢቸገርም እውነታው ግን ይሄው ነው::

የሁለተኛ እና የሦስተኛው ሙከራ የአዉሮኘላኖቹ ጐማ ከአስፋልቱ ጋር ሲገናኝ በሚፈጠረው ሰበቃ (friction) ምክንያት በሚፈለገው ርቀት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሆነበት ነው ማቲዮ የተናገረው::

ያም ሆኖ  ማቲዮ ሲያልመው የነበረውን በቤተሰቡ እና ጓደኞቹ የሞራል ድጋፍ ለስኬት መብቃቱ እንዳስደሰተው ነው ያስታወቀው::  በቀጣይም በሥሙ የተያዘውን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚጥር ይህንንም እንደሚያሳካ ሙሉ እምነቱ መሆኑን ነው  ያብራራው::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here