የታራንጊር ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ማንያራ ክልል ውስጥ ይገኛል። የፓርኩ ስም ፓርኩን እያቆራረጠ ከሚያረሰርሰው ታራንጊር ወንዝ የተቀዳ ነው፡፡
በ1900 እ.አ.አ መጀመሪያዎቹ ዓመታት ሀገሪቱን ቅኝ የገዛት የእንግሊዝ መንግሥት የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ እና አደንን ለመከላከል በ1951 የታራንጊር የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋምን አቋቁሞ ነበር፡፡ ተቋሙም ፓርኩ አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ የለውጥ ተግባራትን ከውኗል፡፡
በ1970 እ.አ.አ ቀደም ብሎ የተቋቋመው የጥበቃ ተቋም የከወናቸው ተግባራት ደርጅተው በ1970 እ.አ.አ ታራንጊር ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ከሚገኙ በቀዳሚነት ከተመሠረቱት አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡
ታራንጊር ብሔራዊ ፓርክ በያዘው ብዝኃ ሕይወት ብዛትና ዓይነት እንዲሁም በስነ ምህዳሩ ታዋቂነትን አትርፏል፤ ፓርኩ የዱር እንስሳት ፍሰትን መመልከት ለሚሹ የሚመረጥ መዳረሻ መሆኑንም በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡
የፓርኩ የግጦሽ መሬት በውስጡ ከሚገኙ የዱር እንስሳት ባሻገር በቀጣናው ለሚኖሩ የማሳይ ጐሳዎች መተዳደሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ታራንጊር ብሔራዊ ፓርክ 2,850 ካሬ ኪሎ ሜ ትር ስፋት አለው፡፡ ከ80 በላይ በመጠን ከፍ ያሉ፣ ትልልቅ አጥቢ እንስሳት እንዲሁም ከ500 በላይ የዓእዋፍ ዝርያዎች መኖሪያም ነው፡፡
ፓርኩ በአካል ግዝፈት ትልልቅ ከሚባሉት አራቱ ማለትም አንበሳ፣ ነብር፣ ጐሽ፣ ዝሆን ይገኙበታል፡፡
ታራንጊር ወንዝ በፓርኩ ክልል የሚፈስ በመሆኑ ሰፊ ረግረጋማ ቀጠናን ፈጥሯል፡፡ የፓርኩ ቀጠና በድርቅ ወቅት ማለትም ከሰኔ እስከ ሕዳር ባሉት ወራት በርካታ የዱር እንስሳት ከየአቅጣጫው በወንዙ ዳርቻ ይሰባሰቡበታል፡፡
ትእይንቱ ለጐብኚዎች ከአዕምሮ የማይጠፋ ነው፡፡ በመሆኑም ያዩት ላላዩት በሚሄዱበት ሀገራት እያሰራጩ ቀጠናው ቋሚ የጐብኚ ፍሰት እንዲኖር ማስቻሉን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በታራንጊር ፓርክ ቀኑ ሞቃት ሌቱ ቀዝቃዛ ነው፡፡ በተለይ ዓእዋፍን ለመመልከት ከህዳር እስከ ታህሣስ አጭር የዝናብ ወቅት እንዲሁም ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ረዘም ያለው የዝናብ ወቅት ተመራጭ ናቸው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም