አይረሴዎች

0
182

በ2016 ዓ.ም ዓለማችን አያሌ አዎንታዊ እና አሉታዊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። አንዳንዶቹ ብስራት እና መርዶ፣ አስደሳች እና አሳዛኝ፣ አስገራሚ እና አስደንጋጭ፣ አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ፣ አስፈንዳቂ እና አሸባሪ፣ ተስፋ ሰጪ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ።

በታሪክ ውስጥ ወደፊት ጎልተው የሚነሱ የዚህን ዓመት በርካታ አበይት ክስተቶች ዘርዝሮ መጨረስ ባይይቻልም ዋና ዋናዎቹን በተለይ ከሀገር መሪዎች እና ቁልፍ ሰዎች ጋር የተያያዙ ክስተቶችን ማስታወስ መልካም ነው። በዚህ ዓመት መንገድ ዳር ተኮልኩሎ የሚጠብቅ ሕዝባቸውን ቀርበው በእጅ እየጨበጡ ሰላምታ በመስጠት ላይ የነበሩት የስሎቫኪያው መሪ ድንገት ከሕዝብ መሀል በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ለጥቂት የመትረፋቸው ዜና ብዙዎችን አስደንግጧል።

ኢራናውያንን በሀዘን ፅልመት ውስጥ ያስገባው፣ መላውን ዓለም ያስደነገጠው፣ እስካሁን መንስኤው ያልታወቀው የኢራኑን መሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን የቀጠፈው የሄሊኮፍተር አደጋን ያስረሳው ክስተት ደግሞ ከወደ ኃያሏ አሜሪካ የተሰማው ነበር።

የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ባሉበት በጆሯቸው ያለፈው የሞት ሹክሹክታ  የአሜሪካውያኑን ጆሮ ጭው ያደረገው ይህ ሌላው የዓመቱ አብይ ወሬ የዓለምንም ትኩረት የሳበ አወዛጋቢ እና አስደንጋጭ ክስተት ነው። እኛም በዚህ ዓመት የተፈፀሙ የመሪዎችን ግድያ እና የግድያ ሙከራዎች አስታከን ታሪክን ወደ ኋላ ልናስታውስ የዚህ ሳምንት የበኩር ጋዜጣ የታሪክ አምዳችን ትኩረት ልናደርግ ወድደናል።

ብዙ ፅሀፍት እንደሚናገሩት በአንድ ፕሬዝደንት፣ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ንጉሥ፣ ወይም በሌላ አይነት የዓለም መሪ ላይ የሚፈፀም ግድያ በመላው ዓለም ላይ ሊያስተጋባ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የአንድ መሪ ግድያ፣ የስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በአንድ ሀገር ዜጎች ላይ ትዝታን የሚያጭር አስደንጋጭ እና ጥልቅ ነው። ብዙዎቹ የመሪያቸውን መገደል በሰሙበት ጊዜ የት እንደነበሩ እና ምን ይሰሩ እንደነበር ሁልጊዜ ያስታውሳሉ። በታሪካቸው ከተፈጠሩ አሳዛኝ ልምዶች በመነሳት፣ አሁን አሁን መንግሥታት  መሪዎቻቸውን በግል ጠባቂዎች ወይም በተደራጀ የደህንነት ቡድን ከብበው ከማንኛውም የግድያ ሴራዎች ይጠብቃሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ እንዲህ ያለ ጥብቅ የደህንነት ጥበቃ እየተደረገላቸውም ከተደገሰላቸው የግድያ ወጥመድ ያልተረፉ ብዙ ገጠመኞች በታሪክ ውስጥ ተመዝግበው እናገኛለን። እስኪ ከ1857 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካ እንዲሁም በህንድ ከተፈፀሙት ጥቂቶቹን እናስታውስ።

ዶናልድ ትራምፕ እድል አተረፋቸው እንጅ ይህን እድል ያልታደሉ አራት የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንቶች መኖራቸውን ታሪክ ያስታውሰናል። በአሜሪካውያን ልብ ውስጥ ድንቅ ስፍራ ያላቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንከን የዚህ ታሪክ ተጋሪ ናቸው። ከ1853 እስከ 1857 ዓ.ም የቆዩት አስራ ስድስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንከን በአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት ወቅት የአሜሪካን ህብረት ያስጠበቁ እና ለባሮች ነፃነትን እውን ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ።

ከአሜሪካ ብሔራዊ ጀግኖች መሀል፣ አብርሃም ሊንከን ለሀገራቸው ልጆች እና ለሌሎች ሀገር ሰዎች የተለየ ሞገስ እንደያዙ ቀጥለዋል። ይህ የተለየ ግርማ ሞገስ ከሰውየው አስደናቂ የሕይወት ታሪክ የሚነሳ ነው፦ ይኸውም ከድሃ ቤተሰብ መውጣታቸው፣ አስደናቂው አሟሟታቸው እንዲሁም ከተለየ ሰብዓዊነት የተላበሰ ሰእብናቸው፣ እንዲሁም  የአሜሪካን ሕብረት በመታደጉ እና ባሮችን ነፃ በማውጣት በታሪክ ውስጥ ካለው ሚና ይመነጫል። የሊንከን አስፈላጊነት የፀናው እና ያደገው በተለይም ለዲሞክራሲ አፍ የሆኑበት አንደበተ ርትኡነታቸው የተነሳ ነው።  በእርሳቸው አመለካከት ሕብረቱን ማዳን የሚጠቅመው ለራሱ ለሕብረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር  ህሳቤን በማካተቱም ጭምር ነው። በቅርብ ዓመታት፣ ከሊንከን ባህሪ በኩል ያለው የፖለቲካ አዝማሚያ እና በዘር ላይ ያላቸው እይታ በተለይ፣ በቅርበት እየተመረመረ ነው፣ ምክንያቱም ግለሰቡን የበቃ የምርምር ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ማግኘታቸውን ስለቀጠሉ።

ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንከንን የገደለው ግለሰብ፣ ጆን ዊልክስ ቡዝ የሚባል ሰው ሲሆን የ19ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ የተከበረ ቤተሰብ አባል ነበር። ቡዝ ጥቅሙን ላጣው የደቡባዊው ዋነኛ ደጋፊ እና ባርነትን በመደገፍ እና ለአብርሃም ሊንከን ባለው ጥላቻ የሚሰማውን ይገልፅ ነበር።

በ1850 ዓ.ም ባርነት እንዲያበቃ የሚታገለውን ጆን ብሮውን የተባለውንና ታጋይ የገደለው የራይሞንድ ሚሊሺያ ወዶገብ አባል ነበር። ቡዝ በ1856 ዓ.ም ፕሬዚደንት ሊንከንን የማጥመድ የወጣለት እቅድ ማሴር ጀመረ። በርካታ የሴራው ተባባሪዎችን መለመለ እና ቡድኑ ሙሉ ክረምቱን በዋሽንግተን ዲሲ በተደጋጋሚ እየተሰበሰቡ በርካታ የማጥመጃ አማራጮችን ይተልሙ ነበር። አያሌ ሙከራዎች ከተጨናገፉ በኋላ፣ ቡዝ የከፈለው ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ ፕሬዚደንቱን እና ባላስልጣኖቻቸውን ለማጥፋት ይወስናል።

ሚያዚያ 6 ቀን 1857 ዓ.ም ፕሬዚደንቱ ምሽት ላይ በአንድ የኮሜዲ ቲያትር ላይ እንደሚታደሙ፣ ቡዝ በጧት መረጃ ደርሶት ነበር። ቡዝ በፍጥነት ቡድኑን አሰባሰበ እና ለእያንዳንዱ አባል ስራ አከፋፈለ፣ ይህም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ዊሊያም ሲዋርድን መግደል ይጨምር ነበር። እርሱ አብርሀም ሊንከንን ይገድላል። ቡዝ አስቀድሞ ወና በሆነው የቲያትር አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ፕሬዚደንቱን ማግኘት የሚያስችለውን ቦታ አመቻችቶ አድፍጦ ቆየ።

ፕሬዚደንቱን ጨምሮ ታዳሚው በአዳራሹ ተገኝቶ ቲያትሩ መታየት ጀምሯል፤ በዚህ መሀል ሶስተኛውን ገቢር በሚታይበት ወቅት ቡዝ ፕሬዚዳንቱ ወደ ተቀመጡበት ተጠግቶ ሽጉጡን በማውጣት ተኩሶ ጭንቅላታቸውን ከኋላ በኩል መታቸው። “ሁልጊዜ ለአምባገነኖች እንዲህ ነው የሚገባቸው!” እና “ደቡቡ ተበቀለ!” የሚል የቨርጂኒያን መፈክር እያሰማ ጮኸ። ከአንድ ጠባቂ ጋር ለአፍታ ሲታገል ቆየ፣ ከዚያም ከሰገነቱ ላይ ወደ ስቴጁ ዘልሎ ሲወርድ የግራ እግሩ አጥንት ተሰበረ። ያም ሆኖ እያነከሰም ቢሆን በጠባቡ መንገድ ማምለጥ ቻለ እና ፈረሱ ላይ ወጥቶ ተሰወረ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የመግደል እቅዱ ከሸፈ፣ ነገር ግን አብርሃም ሊንከን ብዙም ሳይቆዩ በቀጣዩ ቀን ሕይወታቸው አለፈ።

ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ፤ ሚያዚያ 18 ቀን 1857 ዓ.ም  ነበር፤ ቡዝ ተደብቆበታል በተባለ ቨርጅኒያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእርሻ ማሳ ላይ የፌዴራል ወታደሮች የደረሱት። ዴቪድ ሃሮልድ የተባለ የሴራው አካል በእርሻው ውስጥ ከቡዝ ጋር አብሮ ነበር። ሃሮልድ ማሳው በእሳት ከመያያዙ በፊት እጁን ሰጠ፣ ነገር ግን ቡዝ እጅ አልሰጥም አለ። በወታደሮች ወይም ራሱን በራሱ ይመታ ባይታወቅም ቡዝ በጥይት ከተመታ በኋላ ወደ እርሻ ማሳው መኖሪያ ቤት ተወሰደ፣ እናም እርሱም ብዙ ሳይቆይ ሕይወቱ አለፈ። አስከሬኑ የቡዝ መሆኑ ከዓመት በፊት ቀዶ ሕክምና ባደረገለት ሀኪም ተረጋግጠ፣ ከዚያም በሚስጢር ተቀበረ። ከአራት ዓመታት በኋላም እንደገና ቀብሩ ተፈፅሟል። በወቅቱ፣ የተገደለው በትክክል ቡዝ አይደለም እየተባለ ሲወራ የነበረውን አሉባልታ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም።

ጆን ኤፍ ኬኔዲ የተገደሉባት እለት አሜሪካውያን የሀዘን ማቅ ያለበሰች ነበረች። ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከ1953-55 ዓ.ም ድረስ የቆዩ 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩ፣ ዓለም የሚያስታውሳቸው ወጣቱ መሪ ናቸው። በምርጫ አሸንፈው ነጩን ቤተመንግሥት ከተረከቡ ጀምሮ በርካታ የውጭ ጉዳይ ቀውሶችን የተጋፈጡ ሲሆን፣ በተለይ በኩባ እና በበርሊን ውስጥ  የገጠሟቸው ዋነኞቹ ነበሩ። ይሁን እንጂ የኒውክሌር ሙከራን የሚከለክል ስምምነት እና የልማት አጋርነትን የመሳሰሉ ስኬቶችን በማረጋገጥ ቀውሱን መፍታት የቻሉ ናቸው። ኬኔዲ ታዲያ በዳላስ ከተማ በመኪኖች አጀብ በጎዳና እያለፉ ባሉበት ተገድለዋል።

ኬኔዲ በአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ታሪክ ውስጥ የተመረጡ ወጣቱ እና የመጀመሪያው የሮማ ካቶሊክ ተከታይ ነበሩ። የአስተዳደር ዘመናቸው የቆየው ለ1,037 ቀናት ብቻ ነበር። ከመነሻው በውጭ ነክ ጉዳዮች ላይ ተወጥረው ነበር። ሁሌም በሚታወሱበት የቃለመሀላ ንግግራቸው፣ “በሰው ልጅ የጋራ ጠላት በሆኑት ጭቆና፣ ድህነት፣ በሽታ፣ እና በራሱ በጦርነት ላይ ለሚደረግ የረጅም ትግል ሸክምን ለመመሸከም ተዘጋጁ…” በማለት ለአሜሪካ ሕዝብ ጥሪ ያቀረቡበት ነበር። ኬኔዲ በመቀጠል “በረጅሙ የዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አደጋ የተጋፈጠውን ነፃነት የመከላከል ሚና የተሰጣቸው ጥቂት ትውልዶች ብቻ ናቸው። እኔ ከዚህ ሀላፊነት ሸብረክ አልልም-በደስታ እቀበለዋለሁ። …ለዚህ ጥረት የምናውለው ጉልበት፣ እምነት፣ እና መሰጠት ሀገራችንን እና ለነፃነት የሚተጉትን ሁሉ በብርሃን ያደምቃል። እንዲሁም ከዚያ እሳት የሚፈነጥቀው ነበልባል የእውነት ዓለምን ሊያበራት ይችላል። እናም ውድ አሜሪካውያን ወገኖቼ፣ ሀገራችሁ ለእናንተ የምታደርግላችሁን አትጠይቁ፣  እናንተ ለሀገራችሁ ምን ማድረግ እንደምትችሉ ጠይቁ።” በማለት መናገራቸው አይረሳም።

ፕሬዚደንት ኬኔዲን በመግደል የተጠረጠረው ሊ ሃርቨይ ኦስዎልድ ነበር። በታሪክ እንደተመዘገበው፣ ሊ ሃርቨይ ኦስዎልድ ሕዳር 11 ቀን 1955 ዓ.ም  ከምሽቱ 12:30 ላይ(በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር) በአንድ መጋዘን ሕንፃ ስድስተኛው ፎቅ መስኮት ላይ በመሆን ጠብመንጃውን አነጣጥሮ ሶስት ጥይቶችን ተኩሶ ፕሬዚደንት ኬኔዲን በመግደል እና የቴክሳሱን ገዢ ጆን ቢ ኮናሊን በማቁሰል ተከስሶ ነበር። ኦስወልድ ከነበረበት ክፍል ወጥቶ የሕዝብ አውቶቡስ እና ታካሲ ተጠቅሞ ከቦታው ተሰወረ፣ እና አንድ ማይል ያህል እንደራቀ ጄ ዲ ቲፔት የተባለ ኬላ ጠባቂ፣ በፖሊስ ሬዲዮ የተሰራጨውን ተጠርጣሪ እንደሚመስል ስላመነ ያስቆመዋል። ኦስወልድም ወዲያው ሽጉጡን አውጥቶ ቲፔትን ገደለው። ይህ ሲሆን ሰዓቱ ከምሽቱ 1:15 ይል ነበር። ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ በ1:45 ላይ ኦስወልድ በቴክሳስ ቲያትር ውስጥ በፖሊስ ኦፊሰሮች ተያዘ። ሕዳር 12 ቀን 1955 ዓ.ም ከጧቱ 1:30 ሰዓት ላይ በሕጉ መሰረት በፕሬዚደንት ኬኔዲ ግድያ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ሕዳር 13 ቀን 1955 ዓ.ም በጧት ከታሰረበት ክፍል ወደ ምርመራ መስሪያ ቤት እየተወሰደ በነበረበት ስሜቱ በተረበሸ ጃክ ረቢ በተባለ አንድ የዳላስ ናይትክለብ ባለቤት ተገደለ። የኦስዎልድ ገዳይ ረቢ፣ መጋቢት 5 ቀን 1956 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ በግድያ ወንጀል ጥፋተኛነቱ ተረጋገጠ እና ሞት ተፈረደበት። ጥቅምት ወር 1958 ዓ.ም ላይ በቴክሳስ የተጠራው አንድ ችሎት ፍርዱን ቀየረ፣ ነገር ግን አዲሱ ችሎት ከመካሄዱ በፊት ራቢ፣ የካንሰር ችግሩ ተባብሶ በደም ግፊት ሕይወቱ አልፏል፣ ታህሣሥ 14 ቀን 1959 ዓ.ም። በመሆኑም የኬኔዲ ሞት እስከዛሬ ምክንያቱ ሚስጥር እንደሆነ ቀርቷል።

… ይቀጥላል

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here