ኢትዮጵያ ለሁሉም ዐይነት ሰብሎች ልማትም ሆነ ለእንስሳት እርባታ ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የውኃ ሀብት እና ለም መሬት የሚገኝባት ሀገር ናት። የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንትም ግብርና ነው፤ ከ85 በመቶ በላይ ሕዝቧም በግብርና ሥራ ይተዳደራሉ።
ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈም በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት በሚውሉ ሰብሎች ላይ በማተኮር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል። በቂ እና ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለማምረት ባለሀብቶችን ወደ እርሻ ከማስገባት ባሻገር ለእርሻ ሜካናይዜሽን ትኩረት ተሰጥቷል።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሀገራዊ ምርት የአማራ ክልል ከ33 በመቶ በላይ ድርሻን ይይዛል።
በሀገራዊ የምርት ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ያለው የአማራ ክልል ለሁሉም ዐይነት ሰብሎች ተስማሚ የአየር ንብረት እና ለም መሬት ባለቤት ነው::
በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚውሉ የሰብል ምርቶችን በስፋት በማምረት ከሚታወቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንዱ ነው። ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ጥጥ እና ሌሎች ሰብሎች የሚመረቱበት እንደሆነ ከዞኑ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ዞኑ በማዕድን (ለአብነት ወርቅ) እና በእንስሳት ሀብትም ይታወቃል። በርካታ ባለሀብቶች ታዲያ በዘርፉ በስፋት መሰማራታቸውን ነው መረጃው የሚያመላክተው፤ በዚህም ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ምንዛሬን ያስገኛሉ።
አስራት ሙሉዓለም በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በማይካድራ ባናት አካባቢ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብት ናቸው። በሰፊው ማሳቸው ሀገር የምትፈልገውን ሰብሎች እያመረቱ እንደሆነ ለበኩር በስልክ ተናግረዋል። በ2016/2017 የምርት ዘመን በሁለት መቶ ሄክታር መሬታቸው ሰሊጥ እና ማሽላ ዘርተዋል። ሰብሉም በተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል። ወቅቱ ለሰብል ምቹ እንደሆነ የተናሩት ባለሀብቱ አሁን ላይም አረም በማረም እና ሰብሉን ከተባይ በመከላከል ላይ መሆናቸውን አክለዋል።
ባለሀብቱ እንዳሉት ምርታማትን ለማሳደግ፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርትም ለማምረት ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂ ማቅረብ ይገባል። ለአብነትም በእርሻ ወቅት ለአፈር መከስከሻ ማሽን እና በአረም ወቅት ደግሞ ለጸረ አረም መድኃኒት መርጫ መሣሪያዎች በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሌላው በዚሁ ዞን አብርሃጂራ ከተማ ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን ባለሀብት ጌታቸው ግደይ ናቸው። የመኸር እርሻን በማረስ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ማሾ እና አኩሪ አተር ዘርተዋል። በይዞታ መሬታቸው እና በተከራዩት ሁለት መቶ ሃምሳ ሄክታር መሬት ላይ ለበረሃማ የአየር ንረት ተስማሚ ሰብሎችን ዘርተዋል። በብዛት ሰሊጥ እንደሚያመርቱ ነው የተናገሩት። በተጓዳኝ ደግሞ ከብቶችን እና በጎችን ያረባሉ።
ባለሀብቱ እንደነገሩን በአሁኑ ወቅት የአረም ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን በማንሳት በተለይ የሰሊጥ ማሳ እስከ ሦስት ጊዜ እንደሚታረም አስረድተዋል። በአካባቢው የተሻለ የጉልበት ሠራተኛ እንዳለም ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት አምስት መቶ ኩንታል የጥጥ ምርት እንዳገኙ ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ቡቃያው ያማረ እና ከባለፈው ዓመት የተሻለ በመሆኑ ከፍ ያለ ምርት ይጠብቃሉ።
በዞኑ በ2016/2017 የምርት ዘመን ለኢንዱስትሪ፣ ለምግብ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ሰብሎች በስፋት እየተመረቱ ይገኛል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድልቃድር ለበኩር በስልክ እንዳስታወቁት በ2016/2017 የምርት ዘመን 562 ሺህ ያህል ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ነው:: እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ነሐሴ 02 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስም 534 ሺህ ያህል ሄክታር መሬት በሰብል እንደተሸፈነ ቡድን መሪው ተናግረዋል::
በምርት ዘመኑ 70 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ በዕቅድ ተይዟል። እስካሁን 16 ሺህ ያህሉ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ገብቶ ጥቅም ላይ እንደዋለ ተናግረዋል። በዞኑ ዐሥራ አምስት አይነት ሰብሎች እየተመረቱ እንደሆነ ጠቁመዋል። በዋናነት ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ ጤፍ እና ዳጉሳ ይመረታሉ።
ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ለእርሻ ሜካናይዜሽን እና ክላስተር (ኩታ ገጠም) ትኩረት እንደተሰጠ አክለዋል።
ወቅቱ አረም በስፋት የሚታረምበት መሆኑን የገለጹት አቶ ኑርሁሴን ለዚህም ከ80 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ባለሀብቶቹ ሰብላቸውን እያሳረሙ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት:: የለማው ሰብል ውጤታማ እንዲሆን የጉልበት ሠራተኞች ወደ አካባቢው በመምጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በተደረገው የጉልበት የሠራተኞች ጥሪ መሠረት በርካታ የጉልት ሠራተኞች ከተለያዩ ቦታዎች እየመጡ ነው ብለዋል። ወደ ዞኑ ለሚመጡ የጉልበት ሠራተኞችም አቀባብል እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።
በአካባቢው ያሉ ባለሃብቶች ለጉልበት ሠራተኛው የሚሆን መጠለያ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ ምግብ፣ የወባ መከላከያ አጎበር፣ መድኃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ማዘጋጀታቸውን አክለዋል።
እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ በምርት ዘመኑ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በዕቅድ ተይዟል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው በ2016/2017 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እስካሁንም ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ታርሷል። ከአራት ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።
ምርታማነቱን ለማሳደግ ለክልሉ ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ የቢሮው መረጃ ያሳያል። እስካሁን ከስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ወደ ዮኒየኖች ደርሷል። ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጠው ደግሞ ወደ ማሕበራት ገብቷል። በአጠቃላይ ወደ ክልሉ ከገባው 98 በመቶ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ማሰራጨትም ተችሏል። እየተሰራጨም ይገኛል።
የምግብ፣ የኢንዱስትሪ እና የኤክስፖርት (ወደ ውጪ የሚላኩ) ሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ የኩታ ገጠም እርሻን በመተግበር፣ በወቅቱ እና በመጠን የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ፣ አሲዳማ አፈርን በማከም እና ሌሎችንም ግብዓት እና ቴክኖሎጂ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም