የመሬት መንሸራተት አደጋ በአሳሳቢነቱ ቀጥሏል

0
131

ከአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (geological survey) ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ መቀነስ አለፍ ሲልም መከላከል ይቻላል:: ይህንንም ሐሳብም “ተፈጥሯዊ አደጋ፣ ነገር ግን አደጋውን በሰው ሠራሽ ብልሃት መከላከል ወይም መቀነስ ይቻላል” በማለት ነው የሚያብራራው::

ይሁን እንጂ በትኩረት ማነስ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት፣ በገንዘብ እጥረት እና ተያያዥ ምክንያቶች አደጋው ለሚሊዮኖች ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው:: በየዓመቱም የብዙ ሺዎችን ሕይወት እየነጠቀ ይገኛል:: ለአብነትም በቅርቡ በሀገራችን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት በልቷል፣ ብዙ ሺዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሁለት ወራት በፊት ባሰራጨው የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የክረምትን መግባት ተከትሎ ጉዳት ሊከተል እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር:: ሀገራችንም ስጋቱ ሊበረታባቸው ከሚችሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ድርጅቱ አስታውቋል::

ዳሩ የተፈጥሮ አደጋው ሊከሰት እንደሚችል ቀደም ብሎ ቢገመትም አስፈላጊው የቅድሞ አደጋ ጥንቃቄ ተግባር ባለመሠራቱ ከባድ ጉዳት ደርሷል:: እየደረሰም ነው:: ነገሩም “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ይሉት ብሂል ሆኖ አደጋው ከተከሰተ በኋላ ነው ሁሉም ሩጫውን የጀመረው:: ይህ በመሆኑም የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ሳይቻል ቀርቷል:: ይባስ ብሎም አደጋ የደረሰባቸውን ዜጎች ለመርዳት የሄዱ በጎ አድራጊዎች የአደጋው ሰለባ ሆነው ቀርተዋል::

በአማራ ክልል የመሬት መንሸራተት አደጋ  በተደጋጋሚ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ይጠቀሳሉ:: ወልድያ እና ደሴ ከተሞች ደግሞ ዋነኛ የችግሩ ሰለባዎች ናቸው:: የከተሞቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ (ተዳፋት የበዛበት) ደግሞ የችግሩ አባባሽ ምክንያት ነው:: ዘንድሮም ታዲያ በደሴ ከተማ አደጋው ተከስቷል:: በአደጋው በሰው ሕይወት ላይ ችግር ባያስከትልም ከባድ የንብረት ውድመት አስከትሏል ተብሏል:: ተፈጥሯዊ አደጋው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ታዲያ በበጋ ወቅት አስፈላጊው የቅድመ መከላከል ተግባር ሊከናወን እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠይቀዋል::

በተመሳሳይ ክረምት በገባ ቁጥር በጎርፍ መጥለቅለቅ የሚቸገሩ በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች ዘንድሮም ለተመሳሳይ ችግር ተጋልጠዋል::

ሐሳባቸውን ለበኩር በስልክ ያካፈሉን የአካባቢው ነዋሪ እንዳሉት ተገቢው የቅድመ መከላከል ተግባር ባለመሠራቱ ዘንድሮም ለተመሳሳይ ችግር (በጎርፍ መጥለቅለቅ) ተጋልጠዋል:: በመሆኑም የሚመለከተው ክፍል አስፈላጊውን የቅድመ መከላከል ሥራ በማከናወን እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል::

የአየር ንብረት መዛባት የመሬት መንሸራተት አደጋ ዋነኛ መንስዔ መሆኑን የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ማዕከሉ መረጃ ያስረዳል:: የመሬት አቀማመጥንም በተጨማሪነት ያነሳል::

የመሬት መንሸራተት አደጋ ተፈጥሯዊ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ማቆም እንደማይቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ:: ይሁን እንጂ አደጋውን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ወይም ሊያደርስ የሚችለውን ውድመት ማስቀረት ይቻላል::

የመሬት መንሸራተት ሊከሰት እንደሚችል ጠቋሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶች (መሣሪያዎች) አሉ:: እነዚህም አደጋው ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት የሚያስችሉ ስልቶችን ቀደም ብሎ ለመተግበር እና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላሉ:: ተፋሰሶችን በመሥራት ውኃ ወደ መሬት ውስጥ ገብቶ ግፊት እንዳይፈጥር ማድረግ፣ ችግኞችን መትከል፣ ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው አካባባቢዎች ደግሞ ሁሉንም ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ጉዳት ለማስቀረት የሚመከሩ ቢሆኖች ናቸው::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here