ታላቁ ግድግዳ

0
197

ግዙፉ ግድግዳ ወደ ምእራብ አቅጣጫ  እየተጠማዘዘ በመዘርጋት በሰፊው የቻይና ወሰኖችን ያካልላል። ከያሉ ወንዝ ዳርቻ ይጀምርና በበረዶ በተሸፈኑት የቂሊያንሻን  እና ቲያንሻን ተራሮች ላይ ያበቃል። ቀጥ ያሉ ተራሮችን ይወጣ እና የእርሻ መሬቶችን እና በረሀዎችን ያቋርጣል። ግዙፍ የሆነ የግንብ አጥር፤ አስቸጋሪ የምህንድስና ስራ የተካተተበት እና ረጅም ታሪክ ያለው ከፀሀይ በታች ከሰው ልጅ የእጅ ስራዎች መካከል አንዱና አስደናቂው ነው። የቻይና ትልቁ ግድግዳ።  እኛ እስከምናውቀው፣ ግድግዳ፣ አንድም ለመኖሪያ ቤት፣ አልያም ለትላልቅ ሕንጻዎች የተለመደ ነው፤ ነገር ግን አንድ ሀገር ሙሉ በግድግዳ አጥር ሲታጠር ማየት ለአሁኑ ዘመን ሰው የማይታሰብ ሊመስል ይችላል፤ ለጥንታዊው ዓለም ሰው ግን አዲስ አይደለም። የቻይናው ጥንታዊ እና ረጅሙ የግንብ አጥር ሕያው ማሳያ ነው። እንዲህ አይነቱ ግዙፍ ቅርስ በቻይና ወይንም በሌላው የዓለማችን ክፍል የሚታየው አልፎ አልፎ ነው።

የቻይና ገዥዎች የየራሳቸውን ትልቅ ግድግዳ ገንብተው ከጠላት ራሳቸውን የመከላከል የቆየ ልምድ ወይም ታሪክ አላቸው። ታላቁ ግንብ ወይም ግድግዳን የመሰለ መላ ሀገሪቱን ያካለለ፤ ብዙ ማይሎችን ሳይቆራረጥ የተገነባ የለም። አንዳንድ የከተማ ቅጥሮች ቢኖሩም ሙሉ ከተማዋን የሚያካልሉ አይደሉም።

በጥንት ዘመን በሰፊው የቻይና ድንበር በሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ እና ምእራብ ትልቁ ግድግዳ ተገንብቷል። እያንዳንዱ በርካታ መቶ ኪሎሜትሮችን ተዘርግቶ ይታያል። ረዥሙ ግድግዳ ወይም በቻይንኛ ቻንግ ቸንግ በርዝመቱ የተነሳ ሕያው ሆኗል።  በሰሜን ቻይና በኩል የሚያልፈው ታላቁ ግድግዳ፣ በጣም አስደናቂ ነው። ትልቁ ግድግዳ እንደገና በተገነባባቸው የቂን፣ የሐን እና የሚንግ ስርዎ መንግሥታት የግንባታው ስራ እየቀጠለ በተገነባባቸው ጊዜያት ሁሉ ርዝመቱ 5,000 ኪሎ ሜትሮችን ይጨምር ነበር። በዚህ ምክንያት ስሙ ዋን ሊ ቻንግ ቸንግ ወይም 5,000 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ግድግዳ ሊባል እንደቻለ ታሪክ ይናገራል። በርግጥም የ5,000 ኪ.ሜትር ግድግዳ ርዝመቱ ከተገለፀውም በላይ ያልፍ ነበር። በሚደግፉ ስርወ መንግሥት ወቅት የተገነባው ግድግዳ ብቻውን 7300 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። የሚንግ ሰራሽ ታላቅ ግድግዳ ፍርስራሽ መጋዝኖች እስከዛሬ ይገኛሉ።

በቻይናውያን ስነፅሁፎች ተከትቦ እንደሚገኘው ትልቁን ግድግዳ በመገንባቱ ስራ ላይ ከሀያ በላይ አውራጃ አስተዳደሮች እና ስርወ መንግሥታት ተሳትፈውበታል። በየአንዳንዱ ስርወ መንግሥት የተገነቡት አንድ ላይ ቢደመሩ የታላቁ ግድግዳ ርዝመት በአጠቃላይ 50,000 ኪሎ ሜትሮች ይረዝማል። በቻይና ሰሜንምእራብ፣ ሰሜንምስራቅ፣ በበርካታ የሰሜን ቻይና አውራጃዎች እንዲሁም በየሎው እና ያንግዚ ወንዞች መካከል ባለ ሰፊ አካባቢ የታላቁ ግድግዳ ቅሬቶች ተገኝተዋል። በሞንጎሊያ መሀል ላይ ያለው ግድግዳ እስከ 15,000 ኪሎ ሜትሮች ይረዝማል።

በሚንግ ስርወ መንግሥት ወቅት ግድግዳውን ለመገንባት ጥቅም ላይ ከዋሉት ጡቦች እና ድንጋይ አንፃር ባለሙያዎች ሲያሰሉት በዚህ ግብአት በመጠቀም  አንድ ሜትር ውፍረት እና አምስት ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ግንብ መገንባት ብንችል መሬትን አንድ ዙር አካልሎ ይተርፋል። ይህንኑ ግብአት ብንጠቀም እና አምስት ሜትር ስፋት እና 35 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለው አውራጎዳና መንገድ ብንገነባበት መሬትን ሦስት ወይም አራት እጥፍ ሊያካልላት ይችላል። በተከታታይ የቻይናውያኑ ስርወ መንግሥታት የተገነባውን የታላቁን ግድግዳ አጠቃላዩን ርዝመት ለመገንባት የተጠቀሙበትን ግብአት በሙሉ ብንጨምረው ደግሞ መሬትን 30 ወይም 40 እጥፍ ያካልላታል።

ሊዎ ዋን፤ ኤ ሂስትሪ ኦፍ ዘ ግሬት ወል ኦፍ ቻይና በተሰኘው መፅሀፉ ላይ እንዳስቀመጠው፣ የታላቁን ግድግዳ ገንብቶ ለመጨረስ ከመነሻው እስከ ሚንግ ስርወ መንግሥት ድረስ 2000 ዓመታትን ፈጅቷል። በ213 ቅድመ ዓለም፤ በጦረኞቹ መንግሥታት እና በተባበረች ቻይና መካከል በነበረው ጦርነት ባለ ድል ሆኖ ብቅ ያለው የቂን ስርወ መንግሥት የመጀመሪያው ንጉሥ ግድግዳውን በመገንባት የመጀመሪያው አይደለም። ከእርሱ በፊት በሰሜንምእራብ ውስጥ በነበሩት የቂን መንግሥታት፣ በሰሜን የዣኦ መንግስታት እና በሰሜንምስራቅ የየን መንግሥታት ገንብተዋቸው የነበሩትን ምሽጎች ማስፋት እና የማገናኘት ሚና ብቻ ነው የነበረው። የግድግዳ ማቆሙ ስራ ዋና ዓላማ ቻይናን በዙሪያዋ ካሉ የሞንጎል ሕዝቦች እና ቁጡ ዘላኖች ለመጠበቅ የተገነባ ነው።

ትልቁ የቻይና ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው የዣንግ ንጉሥ በተዳከመ ጊዜ፣ በርካታ ራስ ገዝ አውራጃዎች ገንነው በወጡበት እና ሀገሪቱንም እርስ በርስ የሚፎካከሩ ወደ በርካታ ራስ ገዝ መንግሥታት በተከፋፈሉበት ጊዜ ነበር። ራስን ከጎረቤት መንግሥት ለመከላከል አውራጃዎቹ በየግዛታቸው የራሳቸውን ግዙፍ እና ቁመተ ረጅም ግድግዳ ገንብተዋል። ከዚህ ዓላማ አኳያ በተናጠል የተገነቡት ግድግዳዎች በጊዜ ሂደት አግድም አንድ ወጥ የሆነ ታላቅ ግድግዳ እና የመጠበቂያ ማማ ያለው ቅጥር ሆኖ ተዋሃደ። ከዚያ በፊት እያንዳንዱ ራስ ገዝ የየራሱን ድንበር ጠባቂ በራሱ የግዛት ክልል የሚያቆምባቸው ብዙ ግንብ ቤቶች ወይም ካስትሎች ነበሩ። የመጨረሻው እና ረጅሙ ግድግዳ የተገነባው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሚንግ ስርወ መንግሥት ነበር።

በ1996 ዓ.ም ብቻ ከ40 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደጎበኘው የቱሪዝም መረጃዎች ያሚያሳዩ ሲሆን በዩኔስኮ ዓለማቀፍ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የገባ ድንቅ ስራ ነው።  ታላቁ ግድግዳ በወሳኝ ቦታዎች ላይ በመገንባቱ ማለፊያ የሆነ የጥቃት መከላከያ ሆኖ ቻይናን አገልግሏታል።

የሚንግ ስርወ መንግሥት የተለያዩ ነገሥታት አሁን የያዘውን ቅርፅ እና ጥራት እንዲይዝ በማድረግ ከፍተኛውን የግንባታ ስራ ማከናወን ችለዋል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here