አውራ አምባ

0
332

“የአውራምባ ማህበረሰብ አመሠራረትና የሚከተለው ፍልስፍና”  በሚል ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ፌዴራሊዝም መምህር በ2008 ዓ.ም  ባቀረቡት ጥናት ማህበረሰቡን በሚመለከት ብዙ ብለዋል። “ድህነት በተንሠራፋባት፣ ኋላቀር አስተሳሰብ ሥር በሰደደባት፣ የሃይማኖት እና የባሕል ተጽእኖ ጠንክሮ በሚታይባት ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ  እና  በመሰረቱ የተለየ አስተሳሰብ በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ ‘እንደ ነውር’ የሚቆጠር የለውጥ ሀሳብ እና ተራማጅ ፍልስፍና ይዞ ብቅ ማለት ምን ያህል  አስቸጋሪ  እንደሆነ  የሚታወቅ ጉዳይ ነው” ብለው የሚጀምሩት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ማህበረሰቡ የለውጥ ሐሳቦችን ይዞ  መምጣቱን ይናገራሉ።

የአውራምባ ማህበረሰብ የተመሠረተው በ1964 ዓ.ም  በዙምራ ኑሩ አማካኝነት ነበር። መገኛውም በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ነው።ከወረታ ከተማ 12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ዙምራ ኑሩ  ትውልዳቸው ደቡብ ጎንደር እስቴ ወረዳ ውስጥ ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰው ልጆችን እኩልነት ፍቅር እና መከባበርን የሚፈልጉ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል። ገና በወጣት እድሜያቸው ወደ ጎጃም፣ጎንደር እና ወሎ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ በሚኖርበት ዓለም እኩልነትን ይሰብኩ ነበር። ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንዲቀረፉ ይመክሩ ነበር። ጠንክሮ ስለ መሥራት፣ ብክነትን ስለ መቀነስ፣የሴቶችን እኩልነት ስለ ማረጋገጥ፣ ሕጻናትን እና አረጋዊያንን ስለ መንከባከብ እንዲሁም ዝርፊያ እና ስርዓትን ስለመጸየፍ እየተዘዋወሩ አስተምረዋል።

ይህን  የለውጥ  ፍልስፍና ሐሳብ የሚቀበላቸው ሰው ማግኘት ለዙምራ ኑሩ ከባድ ነበር። ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ እንደሚሉት “ሠው ሲያፈላልጉ ደቡብ ጎንደር አስተዳደር አካባቢ ፎገራ ወረዳ ውስጥ ስንቆ መድሀኒዓለም ቀበሌ ውስጥ ሸህ ሠይዴ የተባሉ ሰውና ተከታዮቻቸውን አግኝተው የለውጥ ሃሳባቸውንና የሚከተሉትን ፍልስፍና ሲያካፍሏቸው የመቀበል አዝማሚያ ያዩባቸዋል” ብለው ይቀጥላሉ። በዚህም ምክንያት ይበልጥ እየቀረቧቸው ሲመጡ አርብ ቀን በአካባቢው የሚኖሩት ሙስሊሞችን ስለ ሥራ እና ጊዜ አጠቃቀም ማስተማሩን ቀጠሉ። “በወቅቱ ሐሳባቸውን የሚቀበላቸው ሰው ሲያገኙ ከሀይማኖታዊ ጸሎት ማድረግ ጎን ለጎን ሠርቶ በማግኘት ራስን የመቻልንም አስፈላጊነት ለእነዚህ ሰዎች በሰፊው ማስተማር ይጀምራሉ” ይላሉ ዶክተር ሲሳይ። በዚህ ጊዜ በቋሚነት የሚኖሩበትን እስቴን በመተው የአሁኗን አውራምባን መርጠው መኖር ጀመሩ። የሚከተሏቸው ሰዎች በማግኘታቸውም የአባላቱን ቁጥር ማሳደግ ጀመሩ።

ይህ ማህበረሰብ በ1978 ዓ.ም የህብረት ስራ ማህበር በመመሥረት የቀድሞውን አርባአምባ የአሁኗን  አውራምባ  መንደር መኖሪያው አደረገ።  ዙምራ  በወቅቱ በተዛባ መረጃ ምክንያት  ከወያኔ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል በወረታ ከተማ ለስድስት ወራት እንዲታሰሩ ተደርጓል። ዙምራ ማስፈራሪያ እና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተለቀቁ። ሁኔታው ያስፈራቸው ዙምራ በ1980 ዓ.ም ተከታዮቻቸውን ይዘው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ቦንጋ ተሰደዱ። አምስት ዓመታትን ቆይተውም ተመለሱ።

“የሰላም ጉዞ በአውራምባ ማህበረሰብ” በሚል የማህበረሰቡን ታሪክ እና እሴት የጻፉት አባ ግርማ ፋሪስ “ የአውራ አምባ ማህበረሰብ ዙምራ የተነሳባቸውን መሰረታዊ ሀሳቦች ማለትም የሴቶችን እኩልነት አረጋግጦ፣ የህጻናትን መብት አስከብሮ፣ ለስራ ብቁ ያልሆኑ አቅመ ደካሞችን ተንከባክቦ፣ መጥፎ አነጋገርን እና አሰራርን አስወግዶ፣ በራስ ላይ እንዲሆኑ የሚፈለጉትን ነገሮች በሰዎች ላይ እንዲሆኑና በራስ ላይ እንዳይደርሱ የሚፈለጉ ነገሮችን በሰዎች ላይ እንዳይደርሱ አርቆ አስወግዶ፤ ነጭ ጥቁር ማድረግ የአንድ ፈጣሪ ስራ ሆኖ ሁሉም የሰው ልጆች የዘር ሀረጋችን የአንድ አዳምና ሄዋን ልጆች ነን ብሎ በማመን ሁሉንም ወንድም እህት በማድረግ ለሁሉም እኩል ክብር ሰጥቶ የሚኖር ማህበረሰብ ነው” ሲሉ አስፍረዋል።

በዚሁ ጽሑፍ ላይ ዙምራ ኑሩ የማህበረሰቡን እውነታ እንዲመሠርቱ ምክንያት የሆናቸውን ሐሳብ ሲናገሩ “መነሻዬ የሴቶች እኩልነት ነው” ይሉና  ሴት በሴትነቷ እናት ናት፤ወንድ በወንድነቱ አባት ነው። አባት እና እናት ሆነው ሴቷ እንደ ሞግዚት ወንዱ እንደ አዛዥ የሆነበት ምክንያት በጉልበት ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። እንግዲያው ወንዱ በጉልበቱ ጠንካራ ከሆነ ይህንን ትርፍ ጉልበት ለሥራ እናውለውም ይላሉ።

ዙምራ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው የሴቶች እና የወንዶችን እኩልነት ጥያቄ በማንሳት ሲታገሉ ኖረው፤ይህንን ሐሳባቸውንም አክብሮ የሚኖር ማህበረሰብን ፈጥረዋል። “እናት እና አባቴ ገበሬዎች ነበሩ:: በእርሻ ስራ ላይ አብረው ይውላሉ:: በጉልጓሎው፣ በአረሙ፣በአጨዳው፣ በነዶው ሸክም አብረው ይውላሉ:: ማታ ላይ ሲመለሱ ያባቴ ስራ ዱር ቀርቷል:: የእናቴ ስራ እቤት ይቀጥላል:: የእናቴ ስራ ምንድነው? ድስቱ፣ ምጣዱ እንጨት ማቅረቡ፣ ውሃ መቅዳቱ፣ ልጅ ማጫወቱ፣ እግር ማጠቡ፣ ወፍጮው፣ ወፍጮው ደግሞ እንደዛሬው ዘመናዊ ወፍጮ የለም፤ እናቴ በእጇ ፈጭታ ነው ቤተሰቡን የምታስተዳድረው:: ይህ ሁሉ ስራ የእናቴ መደበኛ ስራዋ ነው” በማለት ሴቶች ላይ የተጫነውን የቤተሰብ ሕይወት ወንዱም እንዲጋራ ሠርተዋል። ለዚህም ዋና መፍትሔ አድርገው ያመጡት የስራ ክፍፍልን ከጾታ ገደብ ውጪ ማድረግን ነው። በአውራምባዎች መንደር ሥራ የሴት እና የወንድ አይባልም። ከለመድነው በተቃራኒ ሴቷ እርሻም ታርሳለች ቤት ውስጥም ታበስላለች።እንዲሁ ወንዱም ቤት ውስጥ እንጀራ ይጋግራል እርሱም ያርሳል።ጥጡንም አባዝቶ ይፈትላል። ልጁንም በጀርባው ያዝላል። ይህ አሠራር ሴት እና ወንድ በቤተሰብ ውስጥ ያላቸውን የሥራ ድርሻ ተመጣጣኝ አድርጎታል።

በመቀጠልም “ጠብን እስከነአካቴው ማስወገድ ይገባል” የሚል ሐሳብን ይዘው ተነሱ።ይህም ሐሳብ ዓለም እና ተፈጥሮ ከግጭቶች ባልተለየችበት ሁኔታ እንዴት ጠብ ይጥፋ ትላለህ የሚል ሙግትን አምጥቶባቸዋል። እሳቸው ግን ሁሉንም ማድረግ ለሰው ልጆች የሚቻል ነው ይላሉ። “ጠብ ስር የለውም:: ጠብን እኛ ካወቅንበት ማስወገድ የኛ ነው:: ጠብን ከመሳል ይልቅ ፍቅርን እየሳልን ብንሄድ የኛ ነው:: ፍቅርንም ጠብንም እምንስለው እኛ ነን:: ምርጫችን ሰላምና ፍቅር ከሆነ ጠብ የለም:: ጠብን የሚያነሳሱ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ናቸው:: እነሱም መጥፎ አሰራር እና መጥፎ አነጋገር ናቸው:: መጥፎ ቢናገሩን እንደማንወድ፣ መጥፎ ቢሰሩብን እንደማንወድ፣ በራሳችን ላይ እንዲደረግብን የማይገባንን ነገር በሰው ልጆች ላይ ማስወገድ ነው:: ያን ጊዜ ጠብ የለም” በማለት ይመልሳሉ።

… ይቀጥላል

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here