የሕግ የበላይነትን ማስፈን

0
166

የአማራ  ክልል ፍትሕ ቢሮ የመደበኛ ወንጀሎች ዐቀቤ  ሕግ  አቶ ዘነበ አበጋዝ የወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክር  ጥበቃ እና ከለላ ሕግን በተመለከተ   መረጃ ሰጥተውናል::

የወንጀል ጠቋሚዎች እና የምስክሮች ጥበቃ ማለት ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ በወንጀል ጉዳይ ጥቆማ የሚሠጡ ሰዎች  እንዲሁም  ፍርድ ቤት ቀርበው በተፈፀመው የወንጀል ጉዳይ ላይ ምስክርነት የሚሰጡ ሰዎችን ማለት ነው::

ወንጀለኞች የወንጀል ድርጊት ከፈፀሙ በኋላ ተደብቀው እንዳይቀሩ እና ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ  የወንጀል ድርጊትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው::

የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ይህን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ታዲያ በምስክርነታቸው ወይም በጠቋሚነታቸው ምክንያት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከሚደርስባቸው አደጋ እና ጥቃት መከላከል አስፈላጊ ነው::

ይህንኑ አስፈላጊነት በመረዳት የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ ሕግ  ሥራ ላይ ውሏል::

የወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክር ጥበቃ አዋጅ ከ2003 በፊት በሕግ ሥርዓታችን ውስጥ ጥበቃ (ከለላ) ያልነበረው ሲሆን፤ በ2003 ዓ.ም ግን በኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው የወንጀል ፍትሕ ፓሊሲ ጉዳዮችን በዝርዝር የዳሰሰ ነበር::

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጅ ቁጥር 699/2003 አፅድቋል::

የወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክር  ጥበቃ እና ከለላ አዋጅ ዓላማ  ምስክሮችን መጠበቅ እንዳለ ሆኖ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ተአማኒነት እንዲኖረው የሕግ የበላይነትን በማስፈን የሕዝብ እና የመንግሥትን ጥቅም ማስከበር ማለት ነው::

ወንጀል ተፈፅሞ ፍርድ ቤት ቀርቦ በአግባቡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቀርበው ምስክርነት ካልሰጡ እና ፍርድ ቤት ተገቢ ውሳኔ ካልሰጠ በምስክሮች ላይ የሚደርስ ማስፈራራት፣ በአካላቸው ላይ ጉዳት፣ የንብረት ጉዳት፣ ግድያ ካለ እና መዝገብ የሚዘጋ ከሆነ በሌላ ጊዜ ሌሎች ምስክሮች በፍትሕ ሥርዓቱ እምነት ስለማይኖራቸው ምስክርነት ይሰጣሉ ተብሎ ስለማይታመን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ወስዶ ተገባራዊ ተደርጓል::

የወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክር  ጥበቃ እና ከለላ  ለማድረግ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ወጪን የሚጠይቁ በመሆኑ ከሀገራችን እድገት እና የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ለሁሉም ምስክሮች እና የወንጀል ጠቋሚዎች ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ አይቻልም:: በመሆኑም የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ማግኘት የሚቻለው ከፍተኛ ወንጀሎች 10 ዓመት እና ከዛ በላይ የሚያሳስሩ፣ የሞት ፍርድ የሚያስፈርዱ እና ከባድ ሙስና ወንጀሎች ሲሠሩ ብቻ ሲሆን ነው የሚሠጠው::

የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን እና በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በምስክሩ ወይም በጠቋሚው ቤተሰብ ሕይወት፣ አካላዊ ደህንነት፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ነው::

መንግሥት የምስክሩን ሕገ መንግስታዊ መብት የማስጠበቅ ግዴታም አለበት:: በአዋጁ አንቀፅ አራት ሥር ለወንጀል ተጎጂዎች የሚሰጠው ጥበቃ በምን መንገድ እንደሆነ በዝርዝር ተቀምጧል::

እነዚህ የአካልና ንብረት ደህንነት ጥበቃ፣ የመኖሪያ ስፍራ መቀየር፣ ከቀየረው አካባቢ ደህንነቱ የተጠበቀ መኖሪያ ቤት መስጠት፣ ሲጓዝ ደግሞ የንብረት ማጓጓዣ መሸፈን፣ ማንነቱን እና ባለንብረትነቱን መደበቅ፣ ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት፣ ድንገት የድርጊቱ ተሳታፊ ሆኖ ከነበረ የሚሰጠው መረጃ ከሚጠቁመው ወንጀል ከፍ ያለ ከሆነ መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ መብት፣ መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የሥራ ቦታ ወይም ት/ቤት አካባቢ አንዳይደርስ ማገድ፣ የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማደረግ፣ ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማደረግ፣ ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነት አንዳይገለጽ ማድረግ፣ ማስረጃ በኤሌክትሮኒክ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ፣ በምስጢር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት፣ እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞ እና የውሎ አበል መስጠት፣ የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን፣ በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ ማካካሻ እርምጃ መስጠት፣ በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የሕክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት፣ በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ ገቢ ማጣት ወይም በበቀል እምርጃ ለደረሰ የመሥራት ችሎታ ማጣት የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን፣ በጥበቃ ሥር እያለ ለደረሰ ሞት የቀበር ማስፈፀሚያ ወጪ መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማደረግ፣ የጥበቃ ተጠቃሚው የሥራ፣ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ መርዳት፣ የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግ። ይህ ሁሉ ተደርጎ መጠበቅ ካተቻለ የጤንነቱ ሁኔታ በሕክምና ተረጋግጦ  ማንነቱን መቀየርን (ፕላስቲከ ሰርጀሪ) ያጠቃልላል::

የወንጀል ተጎጂውም ከላይ ከተቀመጡት ጥበቃ ዓይነቶች ተጎጂው ላይ ሊደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን የአደጋውን ሁኔታ፣ የተጎጂውን ጤና እና ኑሮ ሁኔታ፣ ጥበቃው በሌላ ሰው መብት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲሁም የሚያስወጣውን ወጪ ታሳቢ ተደርጎ በተናጠል ወይም በጣምራ  ሊሰጠው ይችላል ሲል አዋጅ 699/2003 አንቀጽ አምስት ላይ ተቀምጧል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here