ዕያየነው ወደ መሬትነት በመቀየር ላይ ያለዉ ጣና ሐይቅ

0
170

ጣና ሐይቅ ከታመመ በትንሹ አሥራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል:: ዋናው ሕመሙ ደግሞ እምቦጭ የተሰኘ መጤ አረም ነው:: በተጨማሪም በያቅጣጫው ወደ ሐይቁ የሚገባ ደለል እንዲሁም ቆሻሻ፣ የነባር ተክሎች  መመናመን… ችግሮች ተጋርጠውበታል::

በኲር ጋዜጣ የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ  አያሌ ተከታታይ ዘገባዎችን ሠርታለች:: በዘገባዎቿም መጤ አረሙ ሐይቁን እያደረቀው ስለመሆኑ፣ በሐይቁ ውስጥ በሚገኝ ብዝሀ ሕይዎት ላይ ስለሚያደርሰው ተፅዕኖ፣ ዓባይ ወንዝ እንዲሁም ግድቡ ያለ ጣና ሐይቅ ኅልውናቸው አደጋ ላይ የሚወድቅ ስለመሆኑ፣ አረሙ በዓሳ ሀብት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት፣ የመርከብ እና ጀልባዎችን መጓጓዣ ስለማገዱ፣ በዓየር ጠባይ ለውጥ ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ፤ በሐይቁ ውስጥ በሚገኙ ገዳማት እና በውስጣቸው በሚገኙ ቅርሶች ላይ ስለሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ችግር፣ ችግሩን ለመፍታተ መወሰድ ስላለበት ርምጃ … ነዋሪዎችን፣ ባለሙያዎችን፣ ምሁራንን፣ የፖለቲካ ሰዎችን፣ ጣናን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት የተጣለባቸውን ተቋማት… እያነጋገረች ሀሳባቸውን ለውድ አንባቢያን አጋርታለች::

ላብነት ያህል በታህሣሥ 13 ቀን 2007 ዕትሟ “ሀምሳ ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የጣና ሐይቅና ዙሪያው በእምቦጭ አረም ተወሯል” የሚል ዘገባ አስነበብባለች:: በዚህ ዘገባ በጣና ሐይቅ እና ብዝሀ ሕይዎቱ ላይ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ አደጋ ማንዣበቡን፣ አረሙን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት እና ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ውይይት  በባሕር ዳር ከተማ መካሄዱን ዘግባለች:: አረሙን ማስወገድ ካልተቻለ ዓባይ ግድብ ነገ ሰለባ የማይሆንበት  ምክንያት እንደሌለ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህርና የሥነ ሕይዎት ተመራማሪ ዋሴ አንተነህ (ዶ/ር) ስለመግለጻቸውም በዚሁ ዘገባዋ ጠቁማለች:: በወቅቱ የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጣና ሐይቅን የወረረውን የእምቦጭ አረም አመራሮች እና አርሶ አደሮች ባይዘናጉ ኖሮ አድማሱን ሳያሰፋ መከላከል ይቻል እንደነበር ስለመጠቆማቸው እንዲሁም፣ “ባለሙያዎች ትንሽ ሠርተው የተጋነነ ሪፖርት በማቅረብ አዘናግተውናል” በማለት ስለመናገራቸውም በዚሁ ዘገባ አውስታለች:: በኲር በማያያዝም የአካባቢ እና ደን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም አረሙን በመከላከሉ ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ የኃላፊዎችን ዓይን መመለሻ ብቻ ነበር ማለታቸውን ጠቅሳለች:: ሚኒስትር ዴኤታው በተጨማሪም  በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ከዚህ የበለጠ ያንዣበበ አደጋ የለምና በመከላከሉ ረገድ ከሪፖርት በዘለለ የተግባር ሰዎች ልንሆን ግድ ይለናል ሲሉ ስለማሳሰባቸውም ዘግባለች::

በየካቲት 9 ቀን 2007 እትሟም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውኃ ሳይንስ እና ውኃ አዘል መሬቶች ተባባሪ ፕሮፈሰር እና ተመራማሪ  አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) አረሙ በ2004 በጐንደር ዙሪያ፣ ሊቦ ከምከም እና ደንቢያ አካባቢ በአራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተከስቶ እንደነበር፣ ሆኖም  በ2005 አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላ በ20 ሺህ ሄክታር ስለማደጉ መግለጻቸውን ጠቅሳለች:: በ2007 መስከረም ላይ በተደረገ ጥናትም  በ40 ሺህ ሄክታር ተስፋፍቶ ስለመገኘቱ ፕሮፌሰሩን ዋቢ አድርጋ ገልጻለች::

“ጣና ሐይቅን ከተደቀኑበት አደጋዎች ለመታደግ ምን መደረግ አለበት?” በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄም “መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ሊኖረው ይገባል፤ ምሁራን ችግር አመላካች ብቻ ሳንሆን ችግር ፈቺ መሆን አለብን፤ ዳር ሆኖ መታዘብም ሆነ መተቸት አይበጅም፤ የጣና ጉዳይ የአካባቢ ጥበቃ፣ የግብርና፣ የኢንቨስትመንት፣ የውኃ ልማት፣ የቱሪዝም … ምን አለፋህ የሁሉም ቢሮ ጉዳይ ነው፤ እስካልተቀናጀን ድረስ ግን ከጥፋት ልንታደገው አንችልም:: ስለዚህ መንግሥትና ጠቅላላው ሕዝብ ተረባርበን ጣናን እንታደግ እላለሁ” በማለት መልስ እንደሰጧት በኲር በዘገባዋ አስፍራለች::

ሐምሌ ስድስት 2007፣ “ጣና ሐይቅ በፈሳሽ ቆሻሻ እየተበከለ ነው” በሚል ርዕስ ባሰፈረችው ዘገባ ደግሞ የአማራ ክልል  የአካባቢ ጥበቃ እና መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ባይህ ጥሩነህን ዋቢ አድርጋ ጣና በደለል እንዳይሞላ 22 ወረዳዎችን ያካተተ እና አንድ ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሸፈነ ጥናት ስለመጠናቀቁ፣ በቀጣይም በጥናቱ መሠረት የጣና ዙሪያ  መሬት ወሰን ተበጅቶለት እርሻ እና መሰል ተግባራት  እንዳይካሄዱበት እንደሚደረግ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕብረተሰቡ ጋርም መግባባት ላይ ስለመደረሱ ጠቅሳለች::

በኲር በመስከረም 3 ቀን 2008 እትሟም፣ አርሶ አደሮች በመቶ ሜትር ርቀት ያሰግሩት የነበረውን አሳ የእምቦጭ አረም በመስፋፋቱ ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ለማስገር እየተገደዱ እንደሆነ ስለመግለጻቸው ዘግባለች::

“በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በተናጠል ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤታማ ባለመሆኑ በቀጣይ ሥራው በተቀናጀ መንገድ መከናወን እንዳለበት ተጠቆመ” ስትል የዘገበችው ደግሞ በሰኔ 26 ቀን 2009 እትሟ ነበር:: “የእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅን ህልውና እየተፈታተነው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአረሙ መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ አገራዊ ዐውደ ጥናት ተካሂዷል” ስትል የጠቆመችው በኲር በዐውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የአካባቢ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃ እና ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  በላይነህ አየለ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የምርምር ተቋማት እና ግለሰቦችም አረሙን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት እና ምርምር እያደረጉ እንደሆነ፣ ሆኖም  የጥናት እና ምርምር ሥራዎች በተናጠል የሚካሄዱ ከመሆናቸው ባለፈ በበጀት እና በሀሳብ ባለመደገፋቸው እንዲሁም በባለቤትነት የሚመራቸው ተቋም ባለመኖሩ ችግሩን በዘላቂነት ማስወገድ እንዳልተቻለ ስለመናገራቸው አስነብባለች:: በኲር በዘገባዋ በመቀጠልም በቀጣይ አረሙን ለመከላከል የሚካሄዱ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት እና በባለቤትነት እንዲያዝ ለማድረግ መሥሪያ ቤታቸው ኃላፊነት እንደተሰጠው ስለማውሳታቸው ገልጻለች::

“ጣና ሐይቅን ለመታደግ ሀገራዊ ርብርብ ያስፈልጋል” በሚል ርዕስ የዘገበችው ደግሞ በሐምሌ 17 ቀን 2009 እትሟ ነበር:: በዚህ ዘገባዋም “የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ከአምስት ዓመታት በፊት በጣና ሐይቅ ላይ መከሰቱ የሚነገርለትን የእምቦጭ አረምን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶት ተከታታይ ርምጃ ባለመወሰዱ የስርጭት አድማሱን በማስፋት የሐይቁን ህልውና አደጋ ውስጥ ጥሎታል ስለማለታቸው አስነብባለች:: በማያያዝም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የምርምር ሥራ በበጀት ችግር  ወደ ተግባር አለመግባቱን ለአብነት በማንሳት በምርምር ጣቢያዎች እና በዩኒቨርሲቲዎች መዘናጋት እንደሚታይ ስለመግለጻቸውም አስረድታለች::

በኲር ጥቅምት 27 ቀን 2010 ለንባብ በበቃው እትሟም “እምቦጭን የመከላከል ሥራው በእውቀት እና ቴክኖሎጅ ሊታገዝ ነው” ስትል ዘግባለች:: በተጨማሪም በኅዳር 25 ቀን 2010 እትሟ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ክልሉ ለጣና የማይመድበው በጀት የለም” ስለማታቸው አውስታለች::

ይሁንና በሚያዝያ 1 ቀን 2010 እትሟ “ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት የሆነው ጣና ተንከባካቢ ባለቤት አጥቶ በፀና ታሟል እንድረስለት” ስትል ጥሪ አቅርባለች:: በሚያዝያ 8 ቀን 2010 እትሟ ደግሞ  “የጣናን ደለል ለማውጣት ታስቦ የተገዛው ማሽን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም” የሚል ዘገባ ይዛ ወጥታለች::

በኲር ስለጣና መወትወቷን በመቀጠል በጥቅምት 12 ቀን 2011 እትሟ ደግሞ፣ “ጣና ህልውናውን እያጣ ነው” በሚል ርዕስ ይዛው በወጣችው ዘገባ “385 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው የጣና ዳርቻ ውስጥ ከ120 ኪሎ ሜትር በላዩ በእንቦጭ ተወሯል” ስትል ጣናን ከእምቦጭ ነጻ ለማድረግ  የተገባው ቃል ሁሉ ተግባር ላይ አለመዋሉን፣ በዚያው ልክ ደግሞ የጣና ሕመም የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጽ ልብ ያለው ልብ እንዲል አሳስባለች:: በሳምንቱም “ጣና እስኪሞት ነው የምንጠብቀው?” ስትል ጠይቃለች::

በኲር ከሰባት ወራት በኋላ ግንቦት 26 ቀን 2011 ባስነበበችው ዘገባም  የእምቦጭ አረምን ለስምንት ዓመታት ያህል በሰው ጉልበት ለማስወገድ ተሞክሮ አወጋገዱ ሳይንሳዊ ባለመሆኑ እና የአወጋገድ ጥራት ችግር ስላለበት ጥረቱ ውጤት ስላለማምጣቱ አውስታለች:: በዚሁ ዘገባዋ አክላ እንደገለጸችው እምቦጭን ለማስወገድ ከሰው ኃይል ቀጥሎ (የሰው ኃይል ጊዜያዊ መፍትሄ በመሆኑ) ያለው አማራጭ  በማሽን ማስወገድ ነው ተብሎ ቢታመንም ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ውኃ የሚያስፈልግ በመሆኑ እንቅስቃሴውን አስቸጋሪ እንዳደረገው እንዲሁም በሰው ጉልበት ማስወገዱን የገቢ ምንጭ አድርጎ የመመልከት ነገር ስላለ የጥቅም ግጭቶችን ያስከትላል የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁማለች::

“እምቦጭ ከጣና አልፎ ዓባይን እየወረረ ነው” ስትል ያስነበበችው ደግሞ በኅዳር 22 ቀን 2012 እትሟ ነበር:: በዚህ ርዕስ ስር ካሰፈረችው ጽሑፍ፣ “ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሐይቅ ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ የተከሰተው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የተንሰራፋው እምቦጭ አረም ከሐይቁ አልፎ ዓባይ ወንዝን እየወረረ ነው:: አረሙ ዓባይ ላይ በታየ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በ200 ሄክታር ላይ መስፋፋቱ የአደጋውን አሳሳቢነት ፍንትው አድርጐ እያመላከተ ይገኛል:: ይህን የተገነዘበው የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም እንደሚያስፈልግ በማመን በቅርቡ የጣና እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲን አቋቁሟል” የሚል ይገኝበታል::

ይህን ጽሑፍ ያነበበ ሰው በወቅቱ አሁን ገና ለችግሩ መላ ተዘየደለት ብሎ አስቦ ይሆናል:: ነገር ግን ከዚህ በኋላ በበኲር ጋዜጣ  የወጡ ተከታታይ ዘገባዎች የሚጠቁሙት ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየተቃለለ አለመሄዱን ነው:: ለምሳሌ በሰኔ 8 ቀን 2012 እትሟ በጣና ሐይቅ እና በዙሪያዉ ጥናት ካደረጉ ምሁር ጋር  ቆይታ አድርጋ ነበር:: ምሁሩ  “በጣና ላይ የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ቢደረግ ከልካይ የለም፤ ምን እንደሚሠራም ተቆጣጣሪ የለም፤  ጣና ጥበቃ የለውም፤ ባለቤት የለውም” ሲሉ ነበር የገለጹት። ይህ ሀሳብ ባጥኚው ምሁር የተሰነዘረው የክልሉ መንግሥት ለጣና ሐይቅ ሲል “የጣና እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ” ን ካቋቋመ ከስምንት ወራት በኋላ ነው::

በኲር ስለጣና መወትወቷን በመቀጠል መስከረም 4 ቀን 2013 “ከሕመሙ ጋር የሚታገለው – ጣና ሐይቅ” በሚል ርዕስ ሰፊ ትንታኔ ይዛ ወጥታለች፤ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይዎት ከፍተኛ ሳይንቲስት እና የዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማኅበር ሊቀ መንበር ከሆኑት ከሰለሞን ክብረት (ዶ/ር) ጋር ቃለ ምልልስ በማድረግ:: ሊቀ መንበሩም “ጣና ሐይቅ ባለቤት አጥቷል” ነው ያሉት:: ከጎርጎራ ፕሮጀክት በፊት ለጣና ደኅንነት ሊታሰብ ይገባል፤ መንግሥትም ቢሆን በውጤት የሚለኩ ተቋማትን ማቋቋም፣ ጣናን የሚታደግ ትክክለኛ ፖሊሲ እና ሕግ ማውጣት፣ በጣና ሐይቅ እና ዙሪያው ላይ ብቻ የሚሠሩ የብዙኃን መገናኛዎችን ማቋቋም አለበት ስለማለታቸውም አስነብባለች::

በኲር “የጣና ሐይቅ 43 ሺህ ሄክታር የውኃው አካል በእምቦጭ አረም ተወርሮ ጣናን ወደ የብስነት ለመቀየር እየተንደረደረ መሆኑን ኅብረተሰቡ፣ የፖለቲካ አመራሩ እና ምሁራን ተናገሩ” ስትል የዘገበችው ደግሞ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ነበር:: በዚሁ ዘገባዋ እንዳወሳችው ሐይቁ እንዲህ በስፋት በመጤ አረም ከመወረሩ በፊት የድረሱለት ጥሪ ያቀረቡ የዘርፉ ተመራማሪዎች ነበሩ:: ይሁንና ጥሪው ጆሮ ዳባ ልበስ መባሉን  አውስታለች::

በኲር ለጣና ይህን ያህል የጮኸችው በየጊዜው በሠራቻቸው ዘገባዎች እንደተገለጸው ያለ ጣና ዓባይ ወንዝም ሆነ ዓባይ ግድብ፣ ያለጣና የጎርጎራ ፕሮጀክት፣ ያለ ጣና ታሪክ፣ ያለ ጣና የባሕር ላይ ጉዞ ወይም ሽርሽር፣ ያለ ጣና ሕይዎት ስለሌለ ወይም ጣና የባሕር ዳር፣ ከባሕር ዳር አልፎም የኢትዮጵያ ሳምባ ስለሆነ ነው::

ይሁን እንጂ፣ ጩኸቷ ሰሚ አላገኘም፤ አረሙን ማስወገድ ካልተቻለ የዓባይ ግድብ ነገ ሰለባ የማይሆንበት  ምክንያት እንደሌለ  ተመራማሪዎች ቢያስጠነቅቁም ሰሚ አላገኙም፤ የጣና ሐይቅን የወረረውን የእምቦጭ አረም አመራሮች እና አርሶ አደሮች ባይዘናጉ ኖሮ አድማሱን ሳያሰፋ መከላከል ይቻል እንደነበር ከመገለጹም በላይ ባለሙያዎች ትንሽ ሠርተው የተጋነነ ሪፖርት በማቅረብ አዘናግተውናል፤ አረሙን በመከላከሉ ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ የኃላፊዎችን ዓይን መመለሻ ብቻ ነበር ቢባልም የእርምት ርምጃ አልተወሰደም፤ በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ ያንዣበበ አደጋ የለምና በመከላከሉ ረገድ ከሪፖርት በዘለለ የተግባር ሰዎች ልንሆን ግድ ይለናል የሚል ድምጽ ቢሰማም ቃል ተግባር ላይ አልዋለም::

የተወራው ሁሉ ወሬ ብቻ ሆኖ በመቅረቱ እምቦጭ ዓይናችን ዕያየ ጣናን ወደ መሬትነት እየቀየረው ይገኛል:: ይሀንን አሳሳቢ እውነታ በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓም “ሐይቁን እንዳናጣው” በሚል ርዕስ በሠራችው ዘገባ ገልጻለች:: የጣና ሐይቅ ቀድሞ ከነበረበት 6 ሺህ 602 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት በግማሽ ቀንሶ 3 ሺህ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እንደደረሰ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በ2013 ዓ.ም በሠራው ጥናታዊ ዘገባ ስለማሳየቱም በዚሁ ዘገባዋ አውስታለች::  ወደ ጣና ሐይቅ በሚገቡ ገባር ወንዞች አማካኝነት በየዓመቱ ከ37 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን በላይ ደለል አፈር ሐይቁን እንደሚቀላቀልም ጠቁማለች:: በየዓመቱም ሐይቁ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊ ሜትር ጥልቀት እንደሚቀንስም በኲር በዘገባዋ አውስታለች::

ውኃ አዘል መሬቶች በሙሉ እየታረሱ እንደሆነም ጠቁማለች፡፡ በ2016 ዓመተ ምሕረትም አረሙ  በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋ ስለመሆኑ በመጠቆምም የችግሩን አሳሳቢነት ለማሳየት ሞክራለች፤ በኲር::

ውድ አንባቢያን ጽሑፋችንን የምንቋጨው የዛሬ ሦስት ዓመት የተሠራ ጥናት የጣና ሐይቅ ስፋት በግማሽ መቀነሱን ካረጋገጠ፣ ዛሬም የእምቦጭ አረም በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ሳይቀር  እየተስፋፋ ነው ከተባለ ነገ የሚጠብቀን ምን ሊሆን እንደሚችል እንድታጤኑት በማሳሰብ ጭምር ነው:: በተረፈ የሳምባችን የጣና ሐይቅ ሕመም ያመናል የምንል ወገኖች ሁሉ መለስ ብለን የበኲርን ዘገባዎች ልንመረምር፣ ቢመሽም ዛሬም አልጨለመምና ጣናን ለማዳን በዘገባዎቹ በየጊዜው ሲጠቆሙ የኖሩት የመፍትሄ ሀሳቦች ተግባር ላይ ይውሉ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

 

(ቦረቦር ዘዳርአገር)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here