ሀገር ያለግብር …

0
159

በኢትዮጵያ የግብር እና የቀረጥ አጀማመር ከመንግሥታት አመሠራርት ጋር የተቆራኘ ነው። ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማዕከላዊ መንግሥት እየተጠናከረ እና ቅርፅ እየያዘ እስከመጣበት ጊዜ የነበረው የግብር አሰባሰብ የተበታተነ እንደነበር ድርሳናት ያትታሉ። ይህን ለማስተካከል አፄ ቴዎድሮስ ጥረት ቢያደርጉም ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል። በወቅቱ ግብር የሚከፈለውም በዓይነት፣ በጉልበት ወይም አገልግሎት በመስጠት፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በገንዘብ ነበር።

ግብር ለስልጣኔ የሚከፈል እና ለልማት የሚውል የሀብት ምንጭ ነው። የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር በየዓመቱ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ንግድ ቀረጥ ገቢ ይሰበስባል።  በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና በታክስ ሕግጋት መሠረት መንግሥት የተለያዩ የግብር ዓይነቶችን በመጣል ገቢ ይሰበስባል። እነዚህም የገቢ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የኤክሳይዝ ታክስ በመባል ይታወቃሉ።  ግብር መንግሥት በሕግ እና ደንብ ላይ ተመሥርቶ ከሕዝብ እና ከድርጅት ገንዘብ የሚያገኝበት መንገድ ነው። ግብር ወይም ታክስ ለሀገር ልማት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን እና ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ቁልፍ መሣሪያ ነው።

ዜጎች ቤት እና ንብረት በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ፣ በሥራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው አሠራር መሠረት ግብር ይከፍላሉ። የተሰበሰበው ግብር በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ደግሞ ለመሠረተ ልማት መስፋፋት ወሳኙን ሚና ይጫወታል። ለአብነትም  ለምጣኔ ሀብት እድገት፣ ለማሕበራዊ አገልግሎት መስፋፋት፣ ለትምህርት  ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች፣ ለመንገዶች፣ ለድልድዮች፣ ለጤና ጣቢያዎች ግንባታ እና ለኃይል አቅርቦት መስፋፋት … አገልግሎት ይውላል።

በሀገራችን የግብር ሥርዓት በአፄ ዘርዕያቆብ ተጀምሮ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አዋጅ ወጥቶለት ማሻሻያዎች እየተደረጉለት ወጥ ሆኖ እንደመጣ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ ያስረዳሉ።

ግብር መሰብሰብ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የቃል ኪዳን ማህተም ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ “ሕዝብ መንግሥት አለኝ፣ ለሚያስተዳድረኝ መንግሥት ግብር እከፍላለሁ ይላል። መንግሥትም ከማስተዳድረው ሕዝቤ ገቢ እሰበስባለሁ ብሎ ያመነበት፤ በሁለቱ መካከል ያለ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው” ብለዋል።

እንደ አቶ ፍቅረማርያም ማብራሪያ ለማሕበረሰቡ የመሠረተ ልማት ፍላጎት ማሟያ መነሻው ከግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ ነው። በመሆኑም ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ሀገራዊ  ኃላፊነታቸውን እና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የአማራ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ሳያገግም ዳግም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በግብር አሰባስብ ሂደት ፈታኝ አድርጎት እንደቆየም አስረድተዋል። በ2016 ዓ.ም ገቢ ለመሰብሰብ አስቻይ ሁኔታዎች አልነበሩም ብለዋል። በዚያው የበጀት ዓመት ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ልብ ይሏል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለፉት ዓመታት ይደረግ የነበረውን የገቢ አሰባስብ የንቅናቄ መድረክ ማስጀመሪያ ዝግጅት ተቀዛቅዞ እንደነበር ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለዋል።

በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ተከስቶ የነበረው ግጭት በታቀደው እና በታሰበው ግለት ልክ  እንዳይሄድ ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።  ይሁን እንጅ ባለሙያዎቹ አስቻይ ሁኔታ ባልነበረበት ችግሩን በመቋቋም እና በይቻላል መንፈስ በመሥራት የተሻለ አፈጻጸም መፈፀም እንደቻሉ አስረድተዋል።

አቶ ፍቅረማርያም እንዳሉት የግብር አሰባሰብ ለገቢ ተቋማት ብቻ የሚተው አይደለም። በየደረጃው ያሉ ተቋማት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። የድርሻቸውን በመወጣትም ለሀገር ውለታ መዋል ይጠበቅባቸዋል።

ማሕበረሰቡም ደረሰኝ የመቀበል  ልምዱን ማዳበር እንዳለበት አመላክተዋል። በግብይት ሥርዓት ውስጥ ደረሰኝ አለመቀበል ለግለሰቡ ዋስትና ያሳጣል። ለመንግሥትም ገቢውን የሚያሳጣ እንቅፋት መሆኑን ነው ያስረዱት። በቀጣይ ደረሰኝ ያልተቆረጠበት ዕቃ በየትኛውም ቦታ እንዳይንቀሳቀስ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል። በቂ ግብር ሰብስቦ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እና ሌሎች ጉዳዮችን ለማከናወን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

አመራሩ፣ ባለሙያው እና ማሕበረሰቡ ተቀራርቦ መሥራት ግድ ይላል ያሉት አቶ ፍቅረማርያም፣ ማሕበረሰቡ በሚሰበሰበው ገቢ መሠረተ ልማቶች ስለሚገነቡ በወቅቱ መክፈል እንዳለበት ተናግረዋል። የንግዱ ማሕበረሰብ በተቻለው መጠን ህሊናው ዳኛ ሆኖት፣ ኃላፊነት ተሰምቶት ያለማንም ጎትጓች ግብር እንዲከፍል ጥሪ አቅርበዋል።

ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ ገብተው እንዲሠሩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በ2017 ዓ.ም የክልሉን ገቢ ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ሥራ ላይ እንደሚውሉ አስታውቀዋል።

የታቀደውን ግብር ለመሰብሰብ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የግብር ከፋይ የመረጃ አያያዝ መሆኑን በማንሳት አሠራርን ማዘመን ይጠይቃል ብለዋል። የግብር ከፋዮችን ፋይል ወይም መረጃ በሶፍት ኮፒ እና በተሻለ የመረጃ አያያዝ ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነም ገልፀዋል።

የአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ ነበር። መሰብሰብ የተቻለው ደግሞ ከ42 ቢሊዮን ብር በታች ነው።

እንደ አቶ ፍቅረማርያም ገለፃ ከሐምሌ 01 እስከ ሐምሌ 30 የደረጃ “ሐ” (ከአምስት መቶ ሺህ ብር በታች ካፒታል) ግብር ከፋዮች ግብራቸውን የሚከፍሉበት ወቅት ነው።

በክልሉ ከ359 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ”  ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረዋል። ባለው ነባራዊ ሁኔታ 262 ሺህ 735 ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን ይወጣሉ ተብለው ተለይተው 165 ሺህ 193 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብር ከፍለዋል። የአከራይ ተከራይ ከ89 ሺህ 866  ለማስከፈል በዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ 44 ሺህ 713 ያህሉ የኪራይ ገቢ ግብር ከፋለዋል። በአዲሱ በጀትዓመት (2017) በድምሩ 209 ሺህ 906 ግብር ከፋዮች በሐምሌ ወር ያለምንም ቅጣት እና ወለድ ግብራቸውን ከፍለዋል ብለዋል፡፡

ከደረጃ “ሐ” ይሰበሰባል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ነው። እስካሁንም ከሁለት  ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here