ሩሲያን ከካዛኪስታን ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ በአልታይ ክልል በሚገኘው ሀምራዊ ቀለም ባለው የቡርሊንስኮይ ኃይቅ ላይ የሚያልፈው ባቡር በሃዲድ ላይ ሳይሆን የሃይቁን ውኃ እየቀዘፈ የሚጓዝ ይመስላል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል።
በምእራባዊ ሳይቤሪያ የሚገኘው ቡርሊንስኮይ ኃይቅ በከፍተኛ መጠን የጨው ክምችት አለው፡፡ የሃይቁ ጨዋማነት ከሙት ባህር ጋር የሚወዳደር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ለጨዋማው ኃይቅ በውስጡ የሚገኙት ጥቃቅን “ብራይን ሽሪምኘ” የተሰኙ የዓሣ ዝርያዎች ሀምራዊ ቀለም አጐናፅፈውታል፡፡ በዚህም ሀምራዊ ቀለም ያለው ኃይቅ ለሚመለከተው ልዩና አስደናቂ ሊሆን ችሏል። በተጨማሪም በኃይቁ ላይ በየቀኑ የሚመላለሰው የጭነት ባቡር ከሌሎች ኃይቆች የተለየ አድርጐታል፡፡
የቡርሊንስኮይ ሀምራዊ ቀለም የተላበሰውን ኃይቅ መሀል ለመሀል ከፍሎ የሚመላለሰውን ባቡር መጠኑ ከፍ ያለው ጨዋማ ውኃ የሚያንሳፍፈው ነው የሚመስለው፡፡ የባቡር ሀዲዱ ሶቬየት ህብረት ከመከፋፈሏ በፊት በነበሩ ዓመታት ነው የተዘረጋው፡፡
የባቡር መስመሩ የተዘረጋበት ዓላማ አጭር እና አቋራጭ፣ ወይም ተመራጭ ሆኖ ሳይሆን የጨው ሀብትኔ ለመሰብሰብ ነበር፡፡
በኃይቁ ላይ በየእለቱ የሚመላለሰው ባቡር በልዩ ሁኔታ በታችኛው ክፍል የብረት ማማሰያዎች ተገጥመውለታል። ይህም ጨዋማውን ውኃ በመበጥበጥ ወደ ባቡሩ ወለል በመሳብ በየተጐታቾቹ (ፉርጐዎች) ይጭናል፡፡ በዚህ መልኩ በየእለቱ የሚመላለሰው ባቡር በየዓመቱ 65 ሺህ ቶን ወይም 65 ሚሊዬን ኪሎ ግራም ጨው ወይም የዓለምን ህዝብ የአራት ቀን ፍጆታ መሸፈን የሚያስችል መጠን እንደሚሰበሰብ ጽሁፉ አስነብቧል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም