ከትምህርት ላለመራቅ

0
154
Open book and education isolate on white background.

 

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሟት በመጡ የሰላም እና ደኅንነት መናጋቶች የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ ተፈትኗል:: የትምህርት ቤቶች በጦርነት መጎዳት፣ የግብዓቶች መዘረፍ እና መውደም፣ የትምህርት ግብዓትን በወቅቱ እና በሚፈለገው ቦታ ለማድረስ መገደብ፣ የተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆን የግጭቶች ዳፋ ውጤት ነው:: በአማራ ክልል ከወርሀ ሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ያጋጠመው የሰላም መታጣት ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሳይከፈቱ እንዲባጁ አድርጓል::

ተማሪዎችም ዓመቱን ሙሉ ከዛሬ ነገ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርታቸውን ለመከታተል ተስፋን ሰንቀው ተጉዘዋል:: በዓመቱ ትምህርታቸውን መከታተል የቻሉት ከ2 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚበልጡት ከትምህርት በር እንዳልደረሱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል::

የሥነ ልቦና ባለሙያው የሺዓምባው ወርቄ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለበኲር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተማሪዎች ከትምህር ውጪ በሚሆኑበት ወቅት የሚያጋጥማቸው አዕምሯዊ መረበሽ እና የሐሳብ መበተን በሕይወታቸው ተስፋ ካደረጉበት ቦታ እንዳይደርሱ፣ በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። ድብርት፣ ጭንቀት እና ወደተለያዩ ሱሶች እንዲገቡም ሊያደርጋቸው ይችላል:: የስሜት ዝቅታ ማጋጠም፣ የመኖር ጉጉት ማጣት፣ ተስፋ ቢስነት መሰማት፣ ራስን መውቀስ፣ ከሰው የመነጠል ስሜት መገለጫቸው ይሆናል::  የመረበሽ፣ በቀላሉ የመቆጣት፣ ብቸኛ መሆን፣ የትምህርት አፈጻጸማቸው መቀነስ… ሊስተዋል ይችላል::

የክልሉ የሰላም ሁኔታ አሁንም ባልተመለሰበት፣ ይልቁንም መንግሥት በሕግ ማስከበር እርምጃ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ባለበት 2017 ዓ.ም በክልሉ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በዕቅድ መያዙን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል:: ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ግማሽ ያህሉን እንኳ ማሳካት አልተቻለም:: በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ትምህርት ቤቶች  ያልተከፈቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የባከነው ጊዜ ለሁለተኛ ዓመት እንዳይደገም አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች በመሄድ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው::

ተማሪ ወንድም ደመቀ ነዋሪነቱ በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ነው:: ባለፈው ዓመት እንደ ክልል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ አንድ ዓመትን ከትምህርት ውጪ ሆኖ እንዲያሳልፍ አድርጎታል። ተማሪ ወንድም ደመቀ የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዳለው ተናግሯል፤ በ2015 ዓ.ም ያስመዘገበው ውጤት ለዚህ ምስክርነትን ይሰጣል። ተማሪዉ በ2015 ዓ.ም ወደ 12ኛ ክፍል ሲሸጋገር 4ኛ ደረጃ መውጣቱ የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዳለው ማሳያ ነው።

ተማሪ ወንድም ደመቀ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኝ መሆኑን ቀድሞ በመረዳቱ በ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት በመጠኑ ሲዘጋጅ ከርሟል:: ይሁን እንጂ የ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመት ከመግባቱ አንድ ወራት ቀደም ብሎ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ዝግጅቱን እንደገታበት ያስታውሳል። የሰላም መደፍረሱ ግን የገታበት ቅድመ ዝግጅቱን ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቶች ዓመቱን ሙሉ ተዘግተው ከርመዋል::

ተማሪ ወንድም ደመቀ ግጭቱ በሕይወቱ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስታውሰው እንዲህ በማለት ነው፤ “በ2016 ዓ.ም ትምህርት ባይቋረጥ ኖሮ ዛሬ ዩኒቨርሲቲ ነበርኩ፤ በዚህ ዓመትም ከትምህርት ውጪ ሆኘ መክረምን ስላልፈለግሁ ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመሄድ ትምህርቴን እየተከታተልሁ እገኛለሁ።” ከቤተሰብ ርቆ መኖር የጀመረው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተናግሯል:: ይህም ከጸጥታ ስጋቱ መፍትሄ አለማግኘት ጋር ተደማምሮ ለጊዜው ትምህርቱን ተረጋግቶ እንዳይማር ሊያደርገው እንደሚችል ያምናል:: ነገር ግን ከቀዬው እንዲወጣ ያደረገው ትምህርት በመሆኑ ሁሉንም ተቋቁሞ በዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት አስመዝግቦ የሕይወት ግቡን ለማሳካት እንደሚተጋ አስታውቋል::

በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሥራ ተጀምሯል፤ አሁንም የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ተማሪዎች ግን ዳግም ከትምህርት ውጪ ሆኖ ላለመክረም ትምህርት ወደተጀመረባቸው አካባቢዎች በመሄድ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ::

የሥነ ልቦና ባለሙያዉ የሺዓምባው ወርቄ ተማሪዎች ከጦርነት በኋላ ወደ ትምህርት በሚመለሱበት ወቅት ያሳለፉት ፈታኝ የችግር ወቅት ከአዕምሯቸው ስለማይጠፋ በተለየ መንገድ ሊታዩ እንደሚገባ መክረዋል:: ይህም ወጣ ያሉ ባህሪያትን እንዲያሳዩ ሊያደርጋቸው ይችላል::

እናት ወይም  አባቱ ሲገደል ያየ ታዳጊ አዕምሮው የሚያስበው የተጠቂነት እና የአቅመ ቢስነት ሥነ ልቦና በመሆኑ ከመጠቃት ይልቅ ማጥቃትን (በቀል) ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ሊነሳ እንደሚችል ባለሙያው ያስረዳሉ:: ይህም ሁኔታ በሰዎች ላይ በሚስተዋልበት ወቅት ያለፉ ታሪኮችን በመጠየቅ ስሜታቸውን መጋራት፣ ችግራቸውን መካፈል፣ አለሁልህ/ሽ/ በማለት ወደ ነበሩበት ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ ላይ መጣር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል::

ተማሪዎች ከግጭት ወይም ጦርነት መልስ ለትምህርት ቤት ሕግ እና ደንብ ተገዥ የማይሆኑበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል:: ታዲያ በዚህ ወቅት መምህራን እና የትምህርት አመራሩ ተማሪዎችን በጥፋተኝነት ከመፈረጅ ይልቅ አቅርቦ ህመማቸውን መረዳት ይገባል:: በዚህ ወቅት እያንዳንዱ መምህራን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሆኖ ተማሪዎች ከገቡበት ያልተገባ ባህሪ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል::

ተማሪዎችም አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሲደረግ ከእነሱ የሚጠበቀውን ለተነሱለት ዓላማ ስኬት የሚያበቃቸውን  ብቻ ከመከወን ውጪ ስለሌላ ነገር ሊያስቡ እንደማይገባቸው ባለሙያዉ መክረዋል:: በተለይ “ዛሬ የተከፈተው ትምህርት ነገ ይዘጋ ይሆን፣ ለፈተናስ እንደርሳለን፣ ይዘቱስ በወቅቱ ይሸፈን ይሆን?” የሚሉ ጉዳዮች ተማሪዎችን ሊያስጨንቁ እና ሊያሳስቡ የሚችሉ ጉዳዮች አለመሆናቸውን አስታውቀዋል:: ምክንያቱም እነዚህን ክስተቶች ተማሪዎች የሚቆጣጠሯቸው እና ተጽእኖ የሚያደርጉባቸው አይደሉም ይላሉ:: ከተማሪዎች የሚጠበቀው፤ የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተል፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ጊዜያትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለነገ ግብ አወንታዊ ምልከታ ማድረግ ብቻ ነው::

 

(ስማቸው አጥናፍ  )

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here