ከሩዋንዳ ምን እንማር?

0
157

እ.አ.አ 1994 ለመላው ሩዋንዳዊያን በመጥፎነቱ ይታወሳል። በወቅቱ በሃገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት የሁቱ ብሔር ተወላጅ አባላት በሚጠሏቸው እና በሚንቋቸው የቱትሲ ብሎም ለዘብተኛ ብሔርተኛ ናቸው ባሏቸው የራሳቸው ጎሳ አባላት ላይ ለተከታታይ መቶ ቀናት ያክል በፈፀሙት ዘር ተኮር ጥቃት እስከ አንድ ሚሊዮን ዜጎቿን አጥታለች። አሳዛኝ ክስተቱ ለሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ የብሔርተኝነትን ጦስ ማስተማሪያ ሆኖ ይጠቀሳል።

በሌላ በኩል ሩዋንዳ የሺህ ኮረብታማ ስፍራዎች ምድር (The land of a thousand hills) በሚል ትታወቃለች። በሰሜን አቅጣጫ ኡጋንዳ፣ በደቡብ ብሩንዲ፣ በምሥራቅ በኩል ታንዛኒያ እና በምዕራብ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚያዋስኗት ጎረቤት ሀገሮች ናቸው።

ኪጋሊ የሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ስትሆን በቤልጅየም ቅኝ ግዛት ውስጥ በነበረችበት ወቅት እ.አ.አ ከ1907 ጀምሮ የአስተዳደር ከተማ ሆና ማገልገል እንደጀመረች ይነገርላታል።

ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ 24 ሺህ 670 ካሬ ኪሎ ሜትር (km2) የቆዳ ስፋት ያላት ስትሆን እንደ ወርልድ ሜትር መረጃ ደግሞ ከ14 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ   አላት። ፈረንሳይኛ፣ ኪንያ፣ ሩዋንዳ፣ እንግሊዝኛ እና ስዋህሊ የሀገሪቱ ሕዝቦች የመግባቢያ ቋንቋዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። 50 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ከ20 ዓመት በታች ነው። ሩዋንዳ የወንዶች ዜጎቿ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 64 ሲሆን የሴቶች ደግሞ 69 ዓመት እንደሚደርስ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።

የሀገሪቱ ዋና ከተማ ኪጋሊ በቆዳ ስፋቷ አነስተኛ ብትሆንም አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎች አሏት። ከተማዋ የሀገሪቱ ርዕሰ መዲና ከመሆን ባለፈ የሩዋንዳ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የባሕል ማዕከል በመሆንም ጎልታ ትጠቀሳለች።

እ.አ.አ በ1994 የተከሰተው እና አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሩዋንዳዊያን ካለቁበት የእርስ በእርስ ጦርነት ማግስት ሀገሪቱን የተቆጣጠረው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር በሚል የሚጠራው አማፂ ኃይል (RPF) የዛሬውን የሀገሪቱን ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜን ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመከላከያ ሚኒስትር አድርጎ ሾማቸው። በመቀጠልም የሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እ.አ.አ በ2000 ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጣቸው። ፖል ካጋሜ አሁንም ድረስ በምርጫ እያሸነፉ ሩዋንዳን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።

የባሕር በር አልባዋ ሩዋንዳ ዋነኛ የኢኮኖሚ መሠረቷ ግብርና ሲሆን ቡና እና የሻይ ምርቶች ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው። በተጨማሪም የማዕድን ማውጣት ሥራ፣ የኃይል አቅርቦት፣ ንግድ እና የቱሪዝም ዘርፉም ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ጠቅላላ የሀገራዊ ምርት መጠኗ 13 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው። ቱሪዝምን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ዘርፉ እ.አ.አ በ2021 ከሃገሪቱ ጠቅላላ ምርት ውስጥ 47 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍን ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛል።

የሩዋንዳ መንግሥት ሃገሪቱን በቀጣናው የንግድ፣ የሎጅስቲክስ፣ የአይ ሲ ቲ፣ የፋይናንስ እና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ለዚህ ይረዳው ዘንድ የሩዋንዳ መንግሥት በዋና ከተማዋ ኪጋሊ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን፣ የስብሰባ ማዕከሎችን፣ ደረቅ ወደብን እና መጋዝኖችን ለመገንባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በተጨማሪም ሩዋንዳ ባለችበት ቀጣና በቴክኖሎጂ መስክ ቀዳሚ ለመሆን ባላት ፍላጎት በአይ ሲ ቲ ዘርፍ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ‘ኪጋሊ የፈጠራና ምርምር ከተማ (kigali innovation city)’ በሚል ትልቅ ማዕከል ከፍታለች።

ለማዕከሉም የሃገሪቱ መንግሥት ድጋፍ በማድረግ ሥራ ፈጣሪዎችን እና ምርምርን እያበረታታ ይገኛል። ለሁሉን አቀፍ እድገት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ያለችው ሩዋንዳ ሃገሪቱን የፋይናንስ ማዕከል ለማድረግም ‘ኪጋሊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ማዕከል (kigali international finance center) እና አይረም ኢንቨስት (ireme invest)’ የሚባሉ ተቋማትን እስከማቋቋም ድረስ ተጉዛለች።

የሙስና ተግባር በስፋት በሚስተዋልባት አፍሪካ ሩዋንዳ ብዙም የሙስና ወንጀል የሌለባቸው ተብለው ከሚጠሩ የአህጉራችን ሃገራት መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ ያመላክታል፡፡ ሃገሪቱ በአነስተኛ እና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሚሰማሩ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የገቢ ግብር እፎይታ  እንዲያገኙ ታደርጋለች። ለራሳቸው የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ባለፈ በቀላሉ ፈቃዶችን መስጠት መቻሏ የቢዝነስ ሥራ ለመሥራት ምቹ ከሚባሉ የአፍሪካ ሃገራት መካከል የዓለም ባንክ በሁለተኛ ደረጃነት አስቀምጧታል። ይህም የምጣኔ ሀብት ዕድገቷን ከፍ እንዲል አስችሏታል።

ሩዋንዳዊያን ሕብረታቸው፣ አርበኝነታቸው፣ የጠበቀ ማሕበራዊ መስተጋብራቸው እና ጠንካራ የሥራ ባሕላቸው የጋራ ሃገራዊ እሴቶቻቸው ናቸው። እ.አ.አ በ1994 የሁቱ ጎሳ አባላት የራሳቸው ወገን በሆኑት የቱትሲ ጎሳ አባላት ላይ የተፈፀመውን አይረሴ የዘር ማጥፋት ድርጊት ጠባሳ እንዲሽር ለማድረግ ሃገሪቱ ያላትን ባሕል እና ዕሴት ተጠቅማበታለች። ለአብነትም ማሕበረሰቡን ያሳተፉ ሥራዎችን በደቦ እንዲሠሩ በማድረግ፣ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም እና የማሕበረሰቡ ዕሴት የሆነውን የሽምግልና ሥርዓት በመተግበር በሃገሪቱ እና በማሕበረሰቡ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ስሜት ለማጥፋት ጥረት አድርጋለች ውጤታማም ሆናበታለች።

ሩዋንዳ ስትጠራ ሌላው አብሮ የሚነሳላት መገለጫዋ የፅዳት ሁኔታዋ ነው። ሃገሪቱ ፅዱ ከሚባሉት የአፍሪካ ሃገራት መካከል ቀዳሚ መሆኗ ይነገርላታል። ፅዱ ለመሆኗ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ወደ ብስባሽነት ሊቀየሩ የማይችሉ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እ.አ.አ በ2008 ያፀደቀችው ሕግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ በመላ ሃገሪቱ የመንግሥት ተሿሚዎችን ጨምሮ ሁሉም ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በጋራ የማፅዳት መልካም ተሞክሮ አላቸው። በአካባቢ ፅዳት ዘመቻው ላይ የማይሳተፉትን እስከ አምስት ሺህ  ፍራንክ ወይም ስድስት ዶላር እንዲቀጡ ታደርጋለች። ሩዋንዳ ስለፅዳት እና አካባቢ እንክብካቤ ዜጎች ያላቸው ንቃተ ህሊና እንዲዳብር ከመሥራቷ ባለፈ ዘላቂ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን መተግበር መቻሏ ፅዱ ለመሆኗ ቀላል የማይባል ሚና ተጫውቷል። ሃገሪቱ ፅዱ መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፏ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተም  ይገኛል።

የሺህ ኮረብታማ ስፍራዎች መገኛ (The Land of a thousand hills) በሚል የምትታወቀው ሩዋንዳ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተፈጠሩ ሥፍራዎች ባለቤት ከመሆኗ በዘለለ ሃያ ሦስት ሐይቆች እና  በርካታ ወንዞች የሚፈሱባት ሃገርም ናት። እጅግ ውብ የተፈጥሮ ገፅታ ያላት ከመሆኗ በተጨማሪ ተወዳጅና ተግባቢ ዜጎቿ ለጎብኚዎች ተመራጭ ሃገር እንድትሆን አግዟታል።

ምዕራባዊው የሩዋንዳ ክፍል ከታላቁ ስምጥ ሸለቆ የሚዋሰን ሲሆን በውስጡም ብርቅዬ ዝንጀሮዎች፣ ወርቃማ ቀለም ያላቸው ጦጣዎች፣ ወፎች፣ አበባዎች እና ቢራቢሮዎች የሚገኙበት የመስሕብ ስፍራ ነው። በተፈጥሮ ውበት መዝናናት እና መደመም ለሚፈልጉ፣ የዱር እንስሳትን ማዬት ለሚወዱ ጎብኝዎች ሩዋንዳ ያላትን አራት ብሔራዊ ፓርኮች መመልከት አይረሴ ትዝታን ጥሎ የማለፍ አቅም አላቸው።

ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዋነኛ መሠረት እንደሆነ የሚነገርለትን የቡና እርሻ ልማቷን ማየትም ከሚያስገኘው ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ባሻገር ሐሴትን የሚያጎናጽፍ መስህብ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሐይቆች እና ፏፏቴዎች የሩዋንዳ የጎብኚዎች ቀልብ ማረፊያዎች አለፍ ሲልም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ምሰሶዎች ናቸው። ኒዩንግው (Nyungwe) በተባለው የሃገሪቱ ጫካ ውስጥ ከፍ ብሎ በተሠራ ተንጠልጣይ የእግረኛ መንገድ እየተጓዙ የተፈጥሮን ውበት እና ብርቅዬ ፍጥረታትን ለማየት የቱሪስቶች መዳረሻ እንደሆነ ይነገርላታል። በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ሩዋንዳ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሃገር ጎብኚዎችን አስተናግዳለች። ከዘርፉም 620 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የሩዋንዳ የልማት ቦርድ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ ከሚገኙ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታል። ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በፊት አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ ያስተናገደችው ሩዋንዳ ጥቁር ታሪኳን ለመቀየር እና ሕዝቦቿን በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ  ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።

በአጠቃላይ ሩዋንዳ በታሪኳ በእጅጉ ዘግናኝ የሚባለውን ዘር ተኮር የእርስ በርስ ጭፍጨፋ ብታስተናግድም ከገጠማት ፈተና ፈጥና በመውጣት ለበርካታ ሀገራት ምሳሌ ሆናለች። ከጦርነት ማግስትም ወደተሻለ የዕድገት ጎዳና ገብታለች።

ለዚህ ደግሞ በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠችው ልዩ ትኩረት ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንዲሆን አድርጎታል። በርካቶችም የጉብኝት መዳረሻቸው ያደርጓታል። ለአብነትም ተወዳጁ የእንግሊዙን ክለብ አርሰናልን ስፖንሰር በማድረግ ሚሊዮኖች ስለ ሀገሪቱ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ ሠርታለች።

ዘርፈ ብዙ የመስህብ ቦታዎች ባለፀጋዋ ሀገራችን ታዲያ ከሩዋንዳ ብዙ ተሞክሮዎችን ብትወስድ በእጅጉ ታተርፋለች። ለዓመታት በቀጠለው ግጭት የጎበጠውን ምጣኔ ሀብትም በቶሎ አ3እንዲያንሰራራ አይተኬ ድርሻ ይኖረዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከእኛ ሀገር በእጅጉ ያነሰ የቱሪዝም ፀጋ ያላት ሩዋንዳ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ ዕድገቷን አፋጥኖላታልና ነው።

 

 

(ደመቀ ቦጋለ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here