የሆንነው እንደዚህ ነው…

0
123

የሆነ ጊዜ አንድ ባልደረባችን እንዲህ አወራን፤ ወደ ቢሮው ሲመጣ በመንገዱ ላይ ያሉ ሁለት ጎረቤታሞች በር በራቸው ላይ ቆመው በጠዋት ድምጽ በጣም ጮክ ብለው ይሰዳደባሉ፤ አልፎ ሂያጅ ሁሉ እየሰማ ያልፋል:: ስድብ እየመረጡ አንዷ አንዷን የሚያኮስስ እና የበላይነት የሚያስገኝ ይመስል ቃላት እየመረጡ ይሰዳደባሉ:: አንዳንዱ ስቆ ያልፋል፤ አንዳንዱ ይገስጻል፤ አንዳንዱ ተዋቸው ልማዳቸው ነው ይላል፤ አንዳንዱ አይ አመል ይላል፤ አንዳንዱ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብሎ  ጉዞውን ይቀጥላል::

ወደ ምሳ ስሄድም እነዚህ ሰዎች በራቸው ላይ እንደቆሙ አሉ፤እየተሳደደቡ ነው:: ጠዋት ቆመው ነበር፤ በምሳ ሰዓት ተቀምጠዋል፤ ጠዋት ድምጻቸው በጣም ይጮህ ነበር፤ ምሳ ሰዓት የሁለቱም ድምጽ ድካም ተጭኖት ያልሸነፍ ባይነት ሲቃ ይመስላል፤ግን አሁንም የሰዳደባሉ፤ አንዷ አንዷን ትዘልፋለች:: ለምሳ ወደ ቤት አልገቡም:: አንዷ ወደ ቤት ገብታ እንዳትበላ አንደኛዋ አሸነፍኳት ልትል ነው፤ ስለዚህ ጸቡ በባዶ ሆድ ቀጥሏል::

ይህ ባልደረባችን ምሳ በልቶ ተመልሶ የከሰዓት ስራውን አጠናቆ ምሽት ወደ ቤቱ ሲመለስ ያ የጠዋት የስድብ ድምጽ የለም፤ ሰዎቹ ግን አሁንም በራቸው ላይ ቁጭ እንዳሉ ናቸው:: ያ በጠዋት እንኳን የተጣሉትን ሰው አላፊ አግዳሚውን የሚያስቀይም ጸያፍ የስድብ ናዳ ሲያወርድ የነበረ የስድብ አንደበት ተቆልፎ ስድድቡ ከቃላት ወደ ምልክት ስድብ ተቀይሮ አገኘው:: ባልበላ አንጀት ቀኑን ሙሉ ቆመው፣ ተቀምጠው ሲሰዳደቡ ውለው ወደ ማታ ሁለቱም ደከሙ፤ ቃላት ማውጣት እስኪያቅታቸው::

ምናልባት ሰው ሁሉ ዓመላቸው ነው እያለ ያለፈው፣ ምናገባኝ ወደ እኔ አይምጣ እንጅ ብሎ ችላ ያለው አንድም ከጸቡ ድግግሞሽ አሊያም ከጸበኞቹ ተመሳሳይነት ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ሰው ያለፈበትን መንገድ ድንጋይ አይወርውር ይመለስበታልና እየተባለ ያደገና የኖረ፣ አንተ ሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደርን ተሰብኮ ያደገ ግብረ ገብ ማህበረሰብ እንዴት መገላገልን ትቶ ይዋጣላቸው ብሎ ማለፍን መረጠ?

እየሆነ ያለው ይህ ነው፤ እየሆንን ያለነው እንዲህ ነው:: እንደነዚያ ሰፈር ሰዎች ስንጣላ ቆሞ የሚያየን፣ በምንጣላበት ጉዳይ እና በምንመርጠው ስድብ የሚስቅ እንዲሁም የሚያፌዝብን፣ አይ ዓመል የሚለን! ተዋቸው ይዋጣላቸው ብሎ ገላጋይ የሚያሳጣን ብዙ ነው:: አንዳንዱ የጎረቤት ጸብ ለራስ እንደሚተርፍ የዘነጋ፣ አንተ ሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር የሚለው አባባል የሚያስጠላው እና ጭር ሲል አልወድም የሚል ሁሉ እንደ ኳስ ጨዋታ ጸባችንን በጩኽት ያደምቅልናል::

በእንዲህ ዓይነት “በለው!… በለው!… ይዋጣላቸው እና ዓመላቸው ነው!…” የሚል ደማቅ ሆይ ሆይታ ሲኖር የአስታራቂ የሰላም ድምጽ ጩኽቱን ማሸነፍ ሊሳነው ይችላል:: ጉረቤቶቹ በጸብ ሲናውዙ የሱን የቤት ስራ የሚሰራ እና ጸቡ እንዲቀጥል የሚፈልግ ክፉ ጎረቤትም ይኖራል:: አንዳንዱ እንደ ኳስ ጨዋታ ክቡር ትሪቡን ላይ ሆኖ “ስጠው!… አቀብለው!…” እያለ የሚዝናና አለ:: በእንዲህ ዓይነት ከሰላም ይልቅ የጸብ ጉልበት በበረታ ጊዜ ይህን ጩኸት የሚያስቆም የጋራ የሆነ እና ሁሉም የሚያምንበት ተሰሚ እንዲሁም የሚፈራ አስታራቂ ሽማግሌ ያስፈልጋል:: ሁለቱም የሚፈሩት፣ የሚያከብሩት፣ የሚሰሙት፣ የሚስማሙበት ትልቅ ሰው ያስፈልጋል:: ካለበለዚያ እነዚህ እንደነዚህ ጎረቤታሞች ጸብ ጠዋት ቆመን ጮክ ብለን፣ ከሰዓት ቁጭ ብለን፣ ማታ በድምጽ አልባ ምልክት ደክሞን ከተሰዳደብን ሌሊቱን ደክሞን በሕይወት ለማደራችን ዋስትና የለንም::

 

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

በhttp:// www.ameco.et/Bekur

በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here