ወደ ሦስተኛዉ የዓለም ጦርነት እንዳይቀየር የተሰጋዉ

0
157

በዓለም ላይ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለውን ጠላትነት ያህል የመረረ እና የከረረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህም የተነሳ ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ እና በእጅ አዙር አንዳቸው ሌላኛውን ለመጉዳት ሲጥሩ ቆይተዋል። የኢራን መሪዎች ጠላት የሚሏት እስራኤል ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ እንደሚሹ በይፋ ከመናገር አልፈው በቅርበት እስራኤልን ሰላም የሚነሷትን ቡድኖች ሲደግፉ ቆይተዋል። የእስራኤል ፖለቲከኞችም እንደዋነኛ ስጋት የሚመለከቷትን ኢራንን ሳትቀድማቸው ለመቅደም ባገኙት አጋጣሚ ለመጉዳት ይጥራሉ።

እስራኤል ቁልፍ የምትላቸውን የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎችን እንዲሁም ባለሥልጣናትን እና ሳይንቲስቶችን አድብታ ስታጠቃ፣ ኢራን ደግሞ በእስራኤል ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ሰላም ሲነሷት ቆይተዋል።

ባለፈው ዓመት (2016 ዓ.ም) በመስከረም ወር ማብቂያ በኢራን ከሚደገፉት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሐማስ ከጋዛ የፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ኢራንን እና በዙሪያዋ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን አንድ ላይ ለማጥቃት የሚያስችላት አጋጣሚ የተፈጠረላት ይመስላል።

በጋዛ በሐማስ ተዋጊዎች እና መሪዎቹ ላይ የከፈተችው ዘመቻ ዓመት ሊሞላው ሲቃረብ ፊቷን ወደ ኃያሉ የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እና መሪዎቹ አዙራ ክፉኛ እያጠቃችው ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥም የእስራኤል ዱላ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ኢራንን አቁስሏታል። ይህንን ተከትሎ ሚያዚያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እና መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ፈጽማለች።

ምንም እንኳን ኢራን በእስራኤል ላይ የሰነዘረቻቸው ድንበር ተሻጋሪ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች ይህ ነው የሚባል ጉዳት ባያደርሱም፣ ኢራን ከርቀት በእስራኤል ላይ ጥቃት የመፈጸም ብቃት እንዳላት አሳይታለች።

ኢራን በምትደግፋቸው ቡድኖች እስራኤልን ስታስጠቃ፣ እስራኤል ደግሞ ከኢራን ጋር የሚገናኙ ዒላማዎችን ስትመታ በቀጥታ ከመጋጨት ተቆጥበው ነበር። የሰሞኑ ጥቃት ግን ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ በእጅ አዙር ሲያደርጉት የነበረው ፍልሚያ ወደ ቀጥታ ግጭት ማምራቱን ማሳያ ነው።

ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ጋር፣ ከሊባኖሱ ሂዝቦላህ ጋር ደግሞ ድንበር በሚሻገር ግጭት ውስጥ ቆይታ አሁን ወደ ሙሉ ጦርነት የገባችው እስራኤል፤ ከኢራን ጋር የቀጥታ ፍጥጫ ውስጥ ከገባች ዳፋው በሁለቱ ሀገራት ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን መካከለኛው ምሥራቅን ብሎም ዓለምን ያሰጋ ሆኗል።

ቢቢሲ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ወታደራዊ ብቃት ለማወቅ የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅሟል። ነገር ግን ሀገራቱ ከዚህም በላይ የተደበቀ ወታደራዊ አቅም ሊኖራቸው ይችላል። ዓለም አቀፉ የስትራተጂክ ጥናት ተቋም (አይ አይ ኤስ ኤስ) እስራኤል እና ኢራን ያላቸውን የጦር መሣሪያ አቅም ለመገመት የተለያዩ መንግሥታዊ እንዲሁም ማንም ሊያገኛቸው የሚችሉ የመረጃ ምንጮችን እና ዘዴዎችን ተጠቅሟል። የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ ሰላም ተቋምን የመሳሰሉ ድርጅቶችም የሀገራቱን ወታደራዊ አቅም ለማወቅ ጥናቶች አድርገዋል። ነገር ግን ትክክለኛ አሃዝ በማግኘት በኩል ሀገራት መረጃዎችን ስለማይሰጡ ልዩነቶች ይታያሉ።

የኦስሎ የሰላም ጥናት ተቋም (ፒ አር አይ ኦ) ባልደረባ ኒኮላስ ማርሽ እንደሚሉት ግን የዓለም አቀፉ የስትራተጂክ ጥናት ተቋም (አይ አይ ኤስ ኤስ) መረጃ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራትን ወታደራዊ ጥንካሬ ለማወቅ እንደ መነሻ ሊወሰድ ይችላል። ተቋሙ እንደሚለው እስራኤል ከኢራን በላይ ከፍተኛ ገንዘብ ለመከላከያ ስለምትመድብ በየትኛውም ግጭት ውስጥ ከፍተኛ ጥንካሬ እንዲኖራት ያስችላታል።

በአይ አይ ኤስ ኤስ መረጃ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2022 እና 2023 የኢራን የመከላከያ በጀት ሰባት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ የእስራኤል ግን ከእጥፍ በላይ 19 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ከምጣኔ ሃብት አንጻርም የእስራኤል አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከኢራን በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

እስራኤል የራሷ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንዳሏት ቢነገርም፣ በመንግሥት ደረጃ ግን በይፋ እንዳይገለጽ በማድረግ መሣሪያው እንዳላት በሁሉም ዘንድ ጥርጠሬ እንዲፈጠር ስታደርግ ቆይታለች። በተመሳሳይ ምንም እንኳን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አላት ተብላ ብትከሰስም ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አስካሁን የለም። ኢራን የምታካሂደው የኒውክሌር ፕሮግራም ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል ነው ብላ ትከራከራለች። እስራኤል እና ምዕራባውያን ግን ይህንን ባለመቀበል አንድ ቀን ኢራን ኒውክሌር የታጠቀች ሀገር ሆና ብቅ ትላለች የሚል ስጋት አላቸው።

በፈረንጆቹ የመስከረም ወር መጨረሻ 2024 ኢራን ፋታህ የተሰኙ ከ200 በላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች:: ሚሳኤሎቹ እስራኤል ለመድረስ 12 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል:: ሦስት የእስራኤል አየር ማረፊያዎችን እና የሞሳድ የስለላ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ ዒላማቸውን በተሳካ ሁኔታ መምታታቸውንም ኢራን አስታውቃለች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይ ዲ ኤፍ) ግን አብዛኞቹ ሚሳዔሎች “በእስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ በሚመራው የመከላከያ ጥምረት” አንዲከሽፉ ተደርገዋል ብሏል። በመካከለኛው እና በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ “አነስተኛ ጥቃቶች” እንደነበሩ ግን አልሸሸገም። የአሜሪካ መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ፓትሪክ ራይደር፣ ወደ ቴል አቪቭ የተተኮሱ ባላስቲክ ሜሳኤሎችን ለማክሸፍ አሜሪካ ብዛት ያላቸው ፀረ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን አሰማርታ እንደነበር አረጋግጠዋል::

ኢራን ቀደም ሲል 110 የባላስቲክ ሚሳኤሎችን እና 30 የመርከብ ሚሳኤሎችን ተኩሳ እንደነበር አስታውሰው፣ የአሁኑ ጥቃት ኢራን ከምንገዜውም በላይ በቁጥር በርከት ያሉ ሚሳኤሎች የተኮሰችበት መሆኑን አስታውቀዋል:: ስለ ኢራን ጥቃት ዝግጅት አሜሪካ ምንም አይነት ዕውቅና እንዳልነበራትም ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ኢራን ወደ እስራኤል የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ከጠዋት ጀምሮ በነጩ ቤተ መንግሥት በተገነባው የሁኔታ መከታተያ ክፍል ውስጥ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል:: አሜሪካ እስራኤል ላደረገችው የሚሳኤል  መከላከል ድጋፍ ማድረጓንም አረጋግጠዋል::

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን፣ ጥቃቱ የኢራንን ጥቅም እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል:: የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው ኢራን ከባድ ስህተት ፈፅማለች በማለት ጠቅሰው፣ ከበደ ያለ የአፀፋ ምላሽ እንደሚጠብቃት ዝተዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የሚሳኤል ጥቃት ማጠናቀቋን ብትገልጽም እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ዝተዋል። ዋሽንግተን እንደገለጸችው ኢራን ለፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ከረጅም ጊዜ የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሯ እስራኤል ጋር እየሠራች ነው።

ይህን ተከትሎ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ሙከራዎችን ማድረጓን ዮርክ ታይምስ ዘግቧል:: ኢራን በመሬት ውስጥ ለውስጥ የሞከረችው የኒውክሌር ቦምብ አራት ነጥብ አምስት ማግኒቲዩድ (ሬክተር ስኬል) የመሬት መንቀጥቀጥ አስከትሏል፤ ይህም ለሙከራው መሳካት ማረጋገጫ ነው ተብሏል:: ወሬው ከተሰማ በኋላ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ማብለያ ተቋማት ላይ ልትሰነዝር ያወጣችውን ዕቅድ ለማቆየት መገደዷ ተነግሯል::

ይህ የመካከለኛ ምሥራቅ ውጥረት ከሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ጋር ተደምሮ አሜሪካ እና ሌሎች ኃያላን ሀገራት እጃቸውን አስገብተውበት ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይገባ ተሰግቷል:: ዓለማችን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ መሰል ስጋት ተጋርጦባት አያውቅም::

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here