ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ጎብኝዎችን መሳብ፣ ገጽታን መገንባት፣ ገቢን ማሳደግ፣ ተምሮ ለቁም ነገር መብቃት፣ አምርቶ መመገብ እና የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን ነው። በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በቆዳ ቀለም… የሚፈጠሩ ልዩነቶች ውበት እንጂ የመለያየት ምክንያት የማይሆኑት አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው:: ለዚህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሰላም አርበኛ መሆን ይገባዋል::፡
“አንድ እንጨት አይነድም፣ አንድ ሰው አይፈርድም” የሚለው ሀገረኛው አባባል ኮትዲቯራውያን ከሰላም እና ደኅንነት የቀውስ አዙሪት ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትርጉሙ ተቃርኖ ሆኖ ተገኝቷል:: ኢትዮጵያስ ይህንን አባባል ሽራ ሰላሟን ለማረጋገጥ ከኮትዲቯር የምትማረው ምንድን ነው? ሜንስታንድ ድረ ገጽ ኮትዲቯር ከአውሮፓውያኑ 1999 ጀምሮ ሁለት መፈንቅለ መንግሥታት እንደተካሄዱባት ያትታል:: በተቃዋሚዎች እና ሎራን ባግቦ ሲመሩት በነበረው መንግሥት መካከል በነበረ ግጭትም ሀገሪቱ በሰሜን እና በደቡብ ተከፍላ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን አስተናግዳለች:: ሦስት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ኮቲዲቯር ከአራት ሺህ በላይ ሰዎቿን አጥታለች፤ ከ1 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎቿ ተፈናቅለውባታል::
ኮትዲቯር ከአስፈሪው የቀውስ አዙሪት እንድትወጣ ያስቻላት የሀገሯ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በ2006 እ.አ.አ ለዓለም ዋንጫ ድል መብቃቱን ተከትሎ የቡድኑ አጥቂ ዲድዬር ድሮግባ ያስተላለፈው መልዕክት ነው:: “በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ እና በመሐል ሀገር የምትገኙ ሁላችሁም የሀገሬ ልጆች በጋራ መኖር እና አብሮ መጫወት እንደምንችል፣ በጋራ ሆነን ከተጫወትን ማሸነፍ እንደምንችል ዛሬ አረጋግጠናል። በጋራ በመጫወታችን ብሔራዊ ቡድናች ለዓለም ዋንጫ በቅቷል፤ ይህ ድላችን ህዝቡን አንድ እንደሚያደርግ ቃል እንገባላችኋለን:: ዛሬ በፊታችሁ ተንበርክከን የምንለምናችሁ ይቅርታ ነው:: ይቅር ተባባሉ፤ ብዙ ሃብት ያላት ሀገራችን በእንዲህ ዓይነት አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መቆየት የለባትም፤ እባካችሁ ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ጥላችሁ ተቃቀፉ፤ ምርጫ በማካሄድ ለሁላችንም የሚሆን መንግሥት አቋቁሙ” አለ::
ሀገሪቷ ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር ባደረገችው የማጣሪያ ጨዋታ ደጋፊዎች መለያየታቸውን ረስተው በአንድነት ብሔራዊ ቡድናቸውን ደግፈዋል፤ ታቃቅፈውም ጨፍረዋል:: ይህ በአንድም ይሁን በሌላ ሕዝብ ከሕዝብ መቼውንም እንደማይለያይ፣ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ትርፍን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች የሚፈጥሩት ችግር እረፍት መንሳቱን የሚያሳይ ነው::
አጥቂው ያስተላለፈውን መልዕክት ተጫዋቾችም በአንድነት ተቀብለው በሀገሪቱ ያሉ ተዋጊ ኅይሎች እርስ በርሳቸው መታኮስ እንዲያቆሙ ጥሪያቸውን አስተጋብተዋል:: ለዓመታት የተደረጉ የሰላም ጥረቶች ያልተሳኩባት ኮትዲቯር በእግር ኳስ ቡድኗ ወርቃማ ዘመንን አምጥታለች:: በ2007 እ.አ.አ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በይፋ የሰላም ስምምነት በመፈራረም ጦርነቱ በይፋ ተቋጨ::
እርግጥ ጦርነት የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም:: የሰው ልጅን ወልዶ የመሳም፣ የማሳደግ እና ለቁም ነገር የማብቃት ህልምን ያከስማል:: ሚሊዮኖችን ሳይለይ ይበላል:: ከሞቀ ቤት አስወጥቶ በየዋሻው፣ በየጢሻው ብሎም ከሀገር አስወጥቶ በባዕድ ሀገር ለልመና ይዳርጋል:: በዓለም ላይ የተለያየ መነሻ ምክንያት ያላቸው በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል:: ሩዋንዳ ዘርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ሚሊዮን ሕዝቧን አጥታለች፤ ምጣኔ ሐብቷ ደቆ ቆይቷል፤ ዛሬ ላይ ግን ሁሉንም ረስተንዋል፤ ወደ ፊት መጓዝ ጀምረናል ብለው በተሻለ የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴ እና በጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ይገኛሉ::
እንደ ሰርቢያኖች የጦርነትን አስከፊነት ያየ ያለ እስከማይመስል ሌላው እንዲማርበት፣ እነሱም የደረሰውን ግፍ እያስታወሱ ከጦርነት እንዲርቁ ያደረጋቸው አባባል አለ:: “ጦርነት ሲጀምር ፓለቲከኞች ጥይት ያቀብላሉ፤ ባለጸጎችም ምግብ ይሰጣሉ፤ ድሆች ግን ልጆቻቸውን ይለግሳሉ። ጦርነቱ ሲያበቃ ግን ፖለቲከኞች የተረፈውን ጥይት ይሰበስባሉ፤ ባለጸጎችም ከጦርነቱ በተረፈው ሐብታቸው ማደግ ይጀምራሉ፤ ድሆች ግን ልጆቻቸውን በመቃብር ሥፍራ ይፈልጋሉ።”
ታሪካቸው ጦርነት የሆነ በርካታ ሀገራት ይገኛሉ:: አንዳንዶቹ ኀያልነታቸውን ከመነጠቅ ጀምሮ ሀገርነታቸውን አጥተዋል፤ ብልጦች ደግሞ ጦርነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ቀድመው በመረዳታቸው ልዩነቶቻቸውን በንግግር ቋጭተዋል::
ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በይፋዊ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በንግግር እና ድርድር የመፍታት ለጋ ልምድ አላት:: ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት የተቋጨው በንግግርና በድርድር እንደሆነ ይታወሳል:: ስምምነቱ አርሶ አደሩ መደበኛ የግብርና ሥራውን እንዲያከናውን፣ ነጋዴው የንግድ ሥራውን እንዲያስቀጥል፣ ተማሪዉ እንዲማር… አድርጓል:: ይሁን እንጂ ይሄ ልምድ በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ሳይችል ቀርቶ ግጭቶች ዛሬም እንደ አዲስ የአማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጥለዋል::
የአማራ ክልል ከሐምሌ መጨረሻ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በትጥቅ በታገዘ ግጭት ውስጥ ይገኛል:: ግጭቱ ሊያደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ ስነ ልቦናዊ ስብራት… ለመቀነስ ክልሉ ሁለት ጊዜ በተራዘመ ይፋዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጓል:: የክልሉ መንግሥት የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ከማሳወቅ ጀምሮ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ለታጣቂ ኀይሉ አስተላልፏል:: ሕዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል::
የአማራ ክልል መንግሥት በአማራ ክልል ያለውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት በይፋ የመደራደር ጥያቄ ማቅረቡም ይታወሳል:: ለዚህም የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል:: ካውንስሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጣቸው መግለጫዎች ግን እያደረገ ያለው የሰላም ጥረት ፍሬ አለማፍራቱን አስታውቋል::
የካውንስሉ ሰብሳቢ ያየህይራድ በለጠ ካውንስሉ በክልሉ ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም ማብራያ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ከሆነ ደግሞ ካውንስሉ ያገኛቸው የፋኖ አባላት መኖራቸውን አስታውቀዋል:: “በውይይት እና በድርድር የሚያምኑ በርካታ ፋኖዎች አሉ፤ እነርሱን አግኝተናል፣ ከእነርሱ ጋር ተነጋግረናል፤ ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘናል፤ እነርሱም አንድ ሆነው አመራር ፈጥረው መግለጫ እንደሚሰጡን ገልጸውልናል” ማለታቸው ይታወሳል::
ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ እንዲረጋገጥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል:: ካውንስሉ ከአሜሪካ ኤምባሲ እና ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር ውይይት ማካሄዱን ገልጸዋል፤ ካውንስሉ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል:: ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዙንም አስታውቀዋል::
መንግሥት 14ኛ ወራትን ያስቆጠረውን በትጥቅ የታገዘ ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት የሕግ ማስከበር እርምጃ ውስጥ መግባቱን ደግሞ አስታውቋል:: የአማራ ክልል መንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫ በሰጡበት ወቅት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ የገባዉ እስካሁን የተደረጉ የሰላም ጥረቶች ለውጥ ባለማምጣታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል::
የመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዓመቱን ሙሉ የተደረጉ የሰላም አማራጭ ጥሪዎች በታጣቂ ኃይሉ ተቀባይነት ማጣታቸውን አስታውቀዋል:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት “አትማሩም፤ አትሠሩም፤ አትነግዱም…” በሚል እየፈጠረ ያለውን ሁከት እና ብጥብጥ ለማስቆም ተግባራዊ የሕግ ማስከበር ርምጃ መጀመሩን መናገራቸው ይታወሳል::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄዱት የጋራ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሀገራዊ ሰላምን ለመገንባት የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተጠቁመውበታል:: መንግሥት ጦርነቶች እና ግጭቶች በዘላቂነት መቋጫ አግኝተው ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ በነጻነት ሰርቶ ምጣኔ ሐብታዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩን እንዲያስቀጥል እና እንዲያጠናክር ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች በሆደ ሰፊነት መደረጋቸውን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ አስታውሰዋል:: መንግሥት አሁንም ለሰላም ያለው ፍላጎት መቀጠሉን ጭምር ገልጸዋል:: በተናጠልም ሆነ በጋራ በሰላማዊ መንገድ ከማንኛውም ጋር ለመነጋገር የመንግሥት ዝግጁነት መኖሩን ጠቁመዋል::
ይሁን እንጂ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚደረጉ ማናቸውም እኩይ ተግባራት መንግሥት በልበ ሰፊነት የሚያልፍበት ዕድል እጅግ የጠበበ መሆኑን ገልጸዋል:: የሕዝብን የዘመናት የአብሮነት እሴት የሚያላሉ ተግባራትን በሚፈጽሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ፣ በጥላቻ ንግግር የሕዝብን አብሮነት እና ማኅበራዊ መስተጋብር አደጋ ላይ በሚጥሉ እና ሕዝብን ከሕዝብ በሚያጋጩ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል::
የተፈጠረውን ችግር በመቀራረብ፣ በመነጋገር፣ በመከራከር፣ በመግባባት እና አብሮ በመቆም መፍታትን ግብ ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል:: ለዚህም የመተማመን ዋጋ ትልቅ ትርጉም መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል::
ሀገራዊ ሰላምን ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል:: የሰላም መሠረት ይሆናል ተብሎ በትኩረት እየተሠራበት ያለውን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል:: ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ በአሁኑ ወቅት ወደ ምክክር ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውሰዋል:: ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን እና ጥያቄዎችንም ማሠባሠብ መቻሉን ጠቁመዋል:: ይህም መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት እንደሚያስችል፣ የመተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት፣ የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ለማደስ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ጠቁመዋል::
በአጠቃላይ ሀገራዊ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የራሱን ማገር እና ምሰሶ፣ ጡብ እና ውኃ፣ ምስማር እና መዶሻ እንዲያበረክት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም