የአፍሮ አሜሪካውያን ስፖርት

0
141

በአሜሪካ በቀዳሚነት ተወዳጅ ከሆኑት ስፖርቶች መካከል ቅርጫት ኳስ ስፖርት አንዱ መሆኑን የፎክስ ኒውስ መረጃ ያመለክታል። ከአጠቃላይ የአሜሪካ ሕዝብ 11 በመቶ የሚሆነው ምርጫቸው ቅርጫት ኳስ መሆኑንም መረጃው ያስነብባል። ከ26 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ደግሞ ስፖርቱን ያዘወትራል።

ስፖርቱ የተጀመረው ካናዳ ውስጥ ቢሆንም በአሜሪካ ምድር ዝነኛ እና ስመ ጥር ለመሆን ግን ጊዜ አልፈጀበትም። በአሜሪካ ከአሜሪካ እግር ኳስ (NFL) እና ቤዝቦል (MLB) ቀጥሎ ሦስተኛው ተወዳጅ ስፖርት ነው። ስፖርቱ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ውድድሮች ባልተደራጀ መልኩ ይደረጉ እንደነበር መረጃዎች አስነብበዋል። ምንም እንኳ ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር እና ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በወቅቱ በነበረው የዘር እና የቆዳ ቀለም መድሎ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚደረገው ውድድር ለመሳተፍ ብዙ መስናክሎች ገጥሟቸዋል። ቀስ በቀስ ግን በአንዳንድ ውድድሮች ተቀባይነት በማግኝታቸው በውድድሮች መሳተፍ ጀምረዋል።

ጥቁሮቹ ከሌሎች ጋር በመወዳደር ማሸነፍ እንደሚችሉ በማሳየት ለአፍሪካ አሜሪካውያን የኩራት ምንጭ ሆነዋል።  ተጫዋቾች የራሳቸውን የአጨዋወት ስልት በማዳበር የተሻሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል።  ሀሪ ቢኪይ ሌው በፕሮፌሽናል ደረጃ ቅርጫት ኳስ የተጫወተ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ የቀድሞ ስፖርተኛ ነው።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ማይክል ጆርዳን፣ ኮቢ ብሪያንት፣ ሌብሮን ጄምስ እና የመሳሰሉት በዘርፉ ደምቀዋል፤ እየደመቁም ነው። በ2023 እ.አ.አ በተደረገ ጥናት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአሜሪካን ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ጥቁር አሜሪካዊ መሆናቸውን ያትታል። ከአሰልጣኞች አምስት በመቶ የሚሆኑትም አፍሪካ አሜሪካዊ እንደሆኑ ጥናት ያሳያል።

የጥቁር ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በዘርፉ መኖር ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበትን ዘርፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማህበር ሊግ እ.አ.አ በ1946 ነው የተመሰረተው። ሊጉ እስከ 1949 እ.አ.አ ድረስ የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማህበር (BAA) የሚል ስያሜ ነበረው። እ.አ.አ በ1976 ግን አራት ሌሎች የቅርጫት ኳስ ማህበሮች በአንድ ተዋህደው የኤንቢኤ (NBA) ውድድር በተደራጀ መልኩ አሁን ድረስ እየተደረገ ይገኛል።

የቅርጫት ኳስ ስፖርት ከሌሎች ስፖርቶች በተለየ የገዘፈ ተክለ ቁመና ይጠይቃል። ፍጥነት እና ጥንካሬም ዘርፉ የሚጠይቀው ክህሎት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቅርጫት ኳስ ከሌሎች ጎልፍ፣ የአሜሪካን እግር ኳስ፣ ቤዝቦል እና ከመሳሰሉት ስፖርቶች አንፃር  ርካሽ ዋጋ የሚያስወጣ ስፖርት ነው። አነስተኛ የስፖርት ማዝወተሪያ፣ የሰው ኃይል እና ቁሳቁስ የሚጠይቅ በመሆኑ በቀደሙት ጊዜያት በታችኛው የማህበረሰብ ክፍል በስፋት ይዘወተር እንደነበር የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።

አሁን ላይ ግን ስፖርቱ የባለጸጋዎች እየሆነ መጥቷል። የኑሮ ደረጃ መለኪያም እንደሆነ ይነገራል። አሜሪካ ውስጥ ከ17 ዓመት በታች በርካታ ቡድኖች በውስጣቸው የያዟቸው ተጫዋቾች ከባለጸጋ ቤተስብ የወጡ ናቸው። የሀብታም ልጆች በሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ በርካታ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች እየወጡ እንደሆነም ተጠቅሷል።

በላይኛው መደብ የማህበረስብ ክፍል በከፍተኛ ደረጃ የሚወደድ ቢሆንም በታችኛው መደብ ባለው የማህበረሰብ ክፍልም ግን እየተዘወተረ ይገኛል።  አሁን ላይ በዓለም ላይ ለተጫዋቾች ከፍተኛ ክፍያ ከሚከፍሉ የስፖርት ዘርፎች መካከል ቅርጫት ኳስ ቀዳሚ ነው። በተለይ ከአራት ዓመታት ወዲህ የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች በስፖርቱ ዘርፍ የፕላኔታችን ከፍተኛ ተከፋይ ሆነዋል።

የ2024/25 የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ውድድር ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይጀምራል። በአጠቃላይ 30 ቡድኖች በሚሳተፉበት ውድድር 29ኙ ከአሜሪካ እና አንድ ቡድን ደግሞ ከካናዳ ይሳተፉበታል።  በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ 82 ጨዋታዎች ይደረጋል። መደበኛ ውድድሮችም ከወርሃ ጥቅምት እስከ ሚያዚያ ሲደረጉ የጥሎ ማለፉ ውድድር ግን እስከ ሰኔ ወር ይዘልቃል።

በሁለቱ የኮንፍረንስ ምድብ የተሻለ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ሰባት ሰባት ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፉ የሚሸጋገሩ ይሆናል። ከምስራቅ ኮንፍረንስ ቦስተን ሴልቲክ፣ ኒወርክ ኒክስ፣ ፊላደልፊያ 76ers፣ ኦርላንዶ ማጂክ፣ ክሊቪላንድ ካቫሌርስ፣ የሚልዋኪ ቡክስ እና ኢንዲያን ፓከርስ ዘንድሮ ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላሉ ተብሎ ግምት የተሰጣቸው ክለቦች ናቸው።

ኦክልሀማ ሲቲ፣ ሚኒሶታ ቲምበር ዎልቭስ፣ ዴንቨር ኑጌትስ፣ ዳላስ ማቭሪክስ፣ ፊኒክስ ሰንስ፤ ሜምፊስ ግሪዝልስ፣ ኒው ኦርሊንስ እና ጎልደን ስቴት ዋሪየር ከምዕራብ ኮንፍረንስ ምርጥ ሰባት ውስጥ ይገባሉ የሚል ግምት ከወዲሁ አግኝተዋል። የአዲሱን የውድድር ዓመት ዋንጫ ቦስተን ሴልቲክ እንደሚያሸንፍ የኤንቢኤ (NBA) ድረገጽ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል። የቦስተን ሴልቲክ ተጨዋች በወጣት እና ልምድ ባላቸው ኮከቦች የተሞላ ነው። የመከላከል እና የማጥቃት አዕምሮ ባላቸው ተጫዋቾች የተገነባ ጭምር መሆኑ በሊጉ ውስጥ አስፈሪ ቡድን አድርጎታል። ቡድኑ በሊጉ ምርጥ ተጫዋቾችን የሰበሰበ ቡድንም ነው። ጃይሰን ታቱም፣ ጄለን ብሮው እና ጃሩይ ሆሊጃየን የመሳሰሉትን አስደናቂ ኮከቦችን ይዟል። ታዲያ እንደ መረጃው ከሆነ 83 በመቶ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል። ኦክልሀም ሲቲ ቱንደር በሁለተኛ ደረጃ ዋንጫውን የማግኝት ዕድል እንዳለው በመረጃው የተቀመጠ ሲሆን 13 በመቶ ቅድመ ግምት መስጠቱን ድረገጹ ያስነብባል።

በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ታሪክ የቦስተን ሴልቲክን ያህል የነገሰ ክለብ የለም። ክለቡ 18 ጊዜ ዋንጫውን ደጋግሞ አሸንፏል። 18ኛውን ዋንጫ ባሳለፍነው ዓመት ከ16 ዓመታት በኋላ ዋንጫውን በማንሳት አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል። ሎስ አንጀለስ ሌከር 17 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያሳካው በ2020 በፈረንጆች መሆኑ የሚታወስ ነው። ጎልደን ስቴት ዋሪየር ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አሁን ላይ ዋንጫውን ካነሳ ግን 12 ዓመታትን ተሻግሯል።

 

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here